Saturday, 02 May 2015 11:59

ደብረብርሃን የኢንዱስትሪ ከተማ ለመሆን አኮብኩባለች

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(2 votes)

    ደብረብርሃን ዕድሜ ጠገብ ከተማ ናት። የሰሜን ከተሞች መተላለፊያ ናት፡፡ ከዕድገት ተለያይታለብዙ ዘመናት ብትቆይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያንቀላፋችበትን ጊዜ ለማካካስ፣  እየታተረች ነው፡፡
ከተማዋ ከባህር ጠለል በላይ በ2,700 ሜትር ከፍታ ላይ ስለምትገኝ ለኢንቨስትመንት አመቺ ናት። የከተማዋ አስተዳደር ይህን አጋጣሚ በመጠቀም የኢንዱስትሪ ከተማ ሊያደርጋት እየተንቀሳቀሰ ነው። ለኢንቨስትመንት ማነቆ ሆነው የቆዩ ደንቦች፣ መመሪያዎችና አሰራሮችን በማሻሻል ላይ ይገኛል፡፡ ለኢንዱስትሪ በተከለሉ አራት መንደሮች መሰረተ ልማት የተሟላለት 256 ሄክታር መሬት አዘጋጅቷል። ለማኑፋክቸሪንግ መሬት በምደባ 1 ካ.ሜ በ0.50 ሳንቲም ይሰጣል፡፡ ኢንቨስት ለማድረግ የሚፈልግ ግለሰብ ወይም ድርጅት ማስረጃዎች አሟልቶ ካቀረበ የጠየቀውን መሬት በአንድ ቀን ቢበዛ ደግሞ በሁለትና ሶስት ቀን እንደሚረከብ ተገልፆልናል፡፡
በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ 18 የአገር ውስጥና የውጭ አገር ኢንቨስተሮች ደብረ ብርሃን ከትመዋል፡፡ ፋብሪካዎቹ በተለያየ ደረጃ ያሉ ናቸው፡፡ ምርት የጀመሩ፣ በግንባታ ላይ ያሉና መሬት ተረክበው መሰረተ ድንጋይ የተቀመጠላቸው ይገኙበታል፡፡ ባለፈው ሳምንት አርብ ለ15 ኢንዱስትሪዎች የመሰረት ድንጋይ ለማኖር ቢታቀድም በጊዜ እጥረት የተነሳ የስድስቱ ብቻ ነው የተከናወነው፡፡ የሶስት ኢንዱስትሪዎች የመሰረት ድንጋይ ሲቀመጥ በስፍራው ተገኝተን ነበር፡፡
በዕለቱ የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠላቸው ሶስት ኢንዱስትሪዎች መካከል:- 1.2 ቢሊዮን ዶላር ከፍተኛ ካፒታል ያስመዘገበው የቱርኩ ጫማና የቆዳ ውጤቶች አምራች MY Shoes and Leather Manufacturing Plc ይገኙበታል፡፡ ማይ ሹዝ ፋብሪካ በቱርክ-አንካራ ትልቁ ጫማ አምራች ሲሆን በቀን 30ሺህ ጥንድ ጫማዎች እንደሚያመርት የኩባንያው ባለቤት ሚ/ር አህመት ኢሳን ባሰር ገልጸዋል፡፡
ምርታቸውን ለተለያዩ የአውሮፓ፣ የአሜሪካና እስያ አገሮች እንደሚያቀርቡ የተናገሩት ሚ/ር አህመት፣ ደንበኞቻችን በዝተው የምርት እጥረት አጋጥሞናል፤ የደንበኞቻችን ጥያቄ እየበዛ ነው። ስለዚህ ከ2010 ጀምሮ በአፍሪካ የት ኢንቨስት እንደምናደርግ ጥናት ስናደርግ ቆይተን ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገሮች የተረጋጋች፣ ለኢንቨስትመንት የሚጠየቀው ወጪ ዝቅተኛ፤ ለቢዝነስ አመቺ ሆና ስላገኘናት መረጥናት፡፡ እዚህ ስንመጣ ደግሞ የመንግሥት ድጋፍ ከጠበቅነው በላይ ሆኖ አገኘነው በማለት አስረድተዋል፡፡
የቱርክ ቀረጥ ከፍተኛ ስለሆነ በአገራቸው ካመረቱት ምርት የፈለጉትን ያህል ለአውሮፓ ህብረት አገሮች ማቅረብ እንዳልቻሉ ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያ የምትጠይቀው ቀረጥ ከቱርክ በጣም ያነሰ፣ ለሰራተኛ የሚከፈለው ዋጋ በጣም ተስማሚ፣ የኤሌክትሪክ ዋጋ ርካሽ፣ ከቱርክ ጋር ሲነፃፀር የምርት ወጪ እጅግ ዝቅተኛ ስለሆነ በማንኛውም የዓለም ገበያ መወዳደር ያስችለናል፡፡ በዓለም የሸቀጦች ዋጋ እየቀነሰ ስለሆነ በአፍሪካም ሆነ በዓለም ትልቁ ጫማ አምራች እንሆናለን ሲሉ ገልፀዋል፡፡
የደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር ለማይ ሹዝ ያስረከበው ቦታ 7 ሄክታር ሲሆን ፋብሪካው በ35ሺህ ስኩዌር ሜትር ላይ እንደሚያርፍ፣ የፋብሪካው ግንባታ ክረምቱ እንዳበቃ በመስከረም ወይም በጥቅምት ወር እንደሚጀመርና በአራት ወር ተጠናቆ በማርች 2016 ወደ ምርት እንደሚገባ ታውቋል፡፡
ግንባታውን በአራት ወር ለማጠናቀቅ የቸኮሉት ከፈረንሳይ፣ ከአሜሪካው ዎል ማርትና ከስፔይን ድርጅቶች ኮንትራት ስለተዋዋሉ ነው፡፡ የስፔይን ውላቸው ማርች 1,2016 ስለሆነ የፋብሪካው ግንባታ ባይጠናቀቅ እንኳ በከፊል ባለቀው ምርት እንደሚጀምሩ ተናግረዋል፡፡ በመጀመሪያው ምርት 30 ሺህ ሲንተቲክ (የተለያዩ ነገሮች ውህዶች) ከንፁህ ቆዳ 2ሺህ ጥንድ ጫማዎች የሚመረቱ ሲሆን እነዚህን ጫማዎች ወደ ውጭ በመላክ 26 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ እንደሚገኝ፣ ለ1ሺ 962 ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጠርና ይህ አኀዝ በ3ኛው ዓመት 3ሺህ እንደሚደርስ አብራርተዋል፡፡
ማይ ሹዝ ኤንድ ሌዘር ማኑፋክቸሪንግ በአራት አገራት በቱርክ፣ ኢትዮጵያ፣ ቻይናና በብራዚል ፋብሪካዎች ሲኖሩት፤ ትልቁ በቱርክ ዋና ከተማ አንካራ የሚገኘው ነው፡፡ ሁለተኛው ትልቅ ፋብሪካ በኢትዮጵያ የሚገነባ ሲሆን የቻይናው ፋብሪካ እዚህ የሚሰራውን ግማሽ ያህላል፡፡ በብራዚል ያለው በኢትዮጵያ ከሚሰራው በሩብ ያንሳል፡፡ “አሁን በአራት አህጉራት በአውሮፓ፣ በኤስያ፣ በደቡብ አሜሪካና በአፍሪካ ፋብሪካዎች አሉን” ብለዋል ሚ/ር አህመት ኢሳን ባሰር፡፡
ሌላው በዕለቱ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለትና የጥቁር አሜሪካዊው ኢንቨስተር የሚ/ር ብሪክስ ዋሽንግተን ንብረት የሆነው ጀኒፐር የብርጭ ጠርሙስ ፋብሪካ ነው፡፡
ጀኒፐር ጠርሙስ ፋብሪካ በ900 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመ ፋብሪካ ሲሆን በዓመት 150 ሚሊዮን ጠርሙሶች እንደሚያመርትና በሙሉ አቅሙ መንቀሳቀስ ሲጀምር በምስራቅ አፍሪካ ትልቁ ፋብሪካ እንደሚሆን የጀኒፐር ዋና ስራ አስፈፃሚና ጀነራል ማናጀር ሚ/ር ብሪክስ ዋሽንግተን ገልጸዋል፡፡
የፋብሪካው ግንባታ በ2015 አጋማሽ ተጀምሮ በ2016 አጋማሽ የሚጠናቀቅ ሲሆን ግንባታው 900 ሚሊዮን ብር ይፈጃል ተብሏል::
 የፋብሪካው ምርት ለአገር ውስጥ ፍጆታና ለውጭ አገር ገበያ ሲውል በየዓመቱ 30 ሚሊዮን ያህል ጠርሙሶች ለአፍሪካና ለሌሎች አገሮች ይሸጣሉ፡፡ ፋብሪካው ለ500 ያህል ቋሚና ጊዜያዊ ሰራተኞች የስራ ዕድል እንደሚፈጥር ታውቋል፡፡
በሁለቱ ፋብሪካዎች መካከል ለመሥራት የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት ራምስታድ የተባለ የሆላንድ ስሪት ትራክተር መገጣጠሚያ ፋብሪካ ነው፡፡
 አቶ ጥበበ ሰለሞን የቲሲቲ ኢንተርፕራይዝ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሲሆኑ፣ “በአገር ውስጥ ከግብርና ሚ/ር እና ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲ አካላት ጋር በመሆን ከ200 በላይ ገበሬዎችን በማሳተፍ ሞክረንና ተማምነንበት ወደ ምርት ልንገባ ነው” ብለዋል፡፡
 ትራክተሩ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች እንዳሉት የጠቀሱት አቶ ጥበበ፤ በ90 ሳ.ሜ 90 ኪ.ግ ክብደት ያለው 9 መከስከሻና ማረሻ እንዳለው፣ መሬቱ ለም ከሆነ በ8 ሰዓት ውስጥ 20 ሊትር በማይሞላ ነዳጅ 2 ሄክታር መሬት ለዘር እንደሚያዘጋጅ ገልጸዋል፡፡
መሬት ማረስ፣ የዘር ረድፍ ማበጀት፣ መዝራት (መትከል)፣ ቦይ ማውጣት፣ እህል መሰብሰብ፣ ማጓጓዝ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት፣ ውሃ በቱቦ መሳብ … በእጅ እየተገፋ የሚያርሰው ትራክተር ከሚሰጣቸው ጥቅሞች ጥቂቱ ናቸው፡
በስፍራው በመገኘት የመሰረት ድንጋይ ያስቀመጡት የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ የፌዴሬሽን ም/ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ካሳ ተክለብርሃንና የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ አህመድ አብተው ናቸው፡፡  

Read 4700 times