Saturday, 02 May 2015 11:57

ሆቴሎች ኮከብ ለማግኘት እየተመዘኑ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

መመዘኛዎቹ ምን ምን ያካትታሉ?
“አንዳንድ ሆቴሎች ከምዘናው እያፈገፈጉ ነው”

     ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ቱሪስቶች እንደ ፍላጐታቸው አለማቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የሆቴል አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል የተባለው የሆቴሎች ኮከብ ምዘና በአዲስ አበባ ከተጀመረ አንስቶ ወደ 40 የሚጠጉ ሆቴሎች ተመዝነው የኮከብ ደረጃ ወጥቶላቸዋል፡፡ የሁሉም ሆቴሎች የኮከብ ደረጃ ተዘጋጅቶ ከተጠናቀቀ በኋላ የትኛው ባለ 5፣ ባለ 4፣ ባለ 3 እና ባለ 2 ኮከብ እንደሆነ ይፋ ይደረጋል ተብሏል፡፡
በዋነኛነት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሚያከናውነው የሆቴሎች የኮከብ ደረጃ ምዘና፣ በአለማቀፍ የሆቴል ኤክስፐርቶች የሚከናወን ሲሆን ምዘናው በየ3 አመቱ ይከለሣል፡፡ ያኔ የሆቴሎች የኮከብ ደረጃ እንደሚያስመዘግቡት ውጤት ከፍና ዝቅ ሊል እንደሚችልም ተጠቁሟል፡፡
እስካሁን ባለው ምዘና ሂደት ተግዳሮቶች ማጋጠማቸውን የጠቆመው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፤ አንዳንድ ሆቴሎች ከግንዛቤ እጥረት የተነሳ የተለያዩ ሰበቦችን እያስቀመጡ ከምዘናው ለመውጣት እየሞከሩ ነው ብሏል፡፡ “ግማሾቹ ገና እድሣት ላይ ነን” የሚል ምክንያት ያቀርባሉ ያሉት የምዘናው አስተባባሪ የስራ ሃላፊዎች፤ አንዳንዶቹም የሠራተኞቻቸውን ብቃት ለማስመዘን ዳተኝነት ታይቶባቸዋል ብለዋል፡፡ ለእንደነዚህ አይነቶቹ ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እየተሠራ ነውም ተብሏል፡፡ በቢሾፍቱ ከተማ በጉዳዩ ላይ በተደረገው የባለ ድርሻ አካላት ውይይት ላይ ሆቴሎች በተገቢው መንገድ ተፈትሸውና ተመዝነው የኮከብ ደረጃ ማግኘታቸው ለሀገር ገጽታ ካለው መልካም ፋይዳ አንፃር ምዘናው ግዴታ እንዲሆን የሚጠይቁ አስተያየቶችም ተሠንዝረዋል፡፡
ባለሙያዎችን በቢሾፍቱ ከተማ ያከራከረው የሆቴሎች የኮከብ ደረጃ ምዘና፣ በተለይ በክልል የሚገኙትን ሆቴሎች ከመሠረተ ልማት ተደራሽነት አንፃር በአዲስ አበባ ከሚገኙት ነጥሎ እንዲመለከት ከአንዳንድ የውይይቱ ተሳታፊዎች ጥያቄና አስተያየት የቀረበበት ቢሆንም ምዘናው አለማቀፍ እንደመሆኑ፣ በግልፅ የተቀመጡ የምዘና ዝርዝር መስፈርቶችም በመዘጋጀታቸው ያለምንም የተለየ ድጋፍና ልዩነት በክልል ያሉ ሆቴሎች ከአዲስ አበባ ካሉት እኩል ይመዘናሉ ሲሉ የምዘና ሂደቱ አስተባባሪዎች ምላሽ ሠጥተዋል፡፡
እስከ ዓመቱ ማጠናቀቂያ ድረስ ወደ 500 የሚጠጉ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ሆቴሎች እንደሚመዘኑ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ አሚን አብዱል ቃድር የጠቆሙ ሲሆን ሆቴሎቹ በተለያዩ አካላት እንደሚመዘኑም ገልፀዋል፡፡
የእሣትና ድንገተኛ አደጋን የመከላከል አቅምን በተመለከተ በአዲስ አበባ ከተማ ያሉትን ሆቴሎች የአዲስ አበባ እሣትና ድንገተኛ መከላከልና መቆጣጠር ባለስልጣን የሚመዝን ሲሆን በተለይ በኦሮሚያ ክልል እና በሌሎች ክልሎች የሚገኙ ሆቴሎችን ለመመዘን የሚያስችል የእሣትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከያ ባለስልጣን አለመኖሩ አነጋጋሪ ነበር፡፡ ክልሎች የራሣቸው የእሣትና ድንገተኛ መከላከያ አደረጃጀት እንደሌላቸውም በውይይቱ ተጠቅሷል፡፡
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አሠፋ ከሲቶ፤ ሃገሪቱ በፌደራል ደረጃ የተዋቀረ የእሣትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከያ ተቋም እንደሌላት ጠቅሰው ተቋሙን ለማቋቋም የተለያዩ ሠነዶች እየተዘጋጁና ውይይት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በቀጣይም የፌደራል እሣትና አደጋ መከላከያ ሲኖር ክልሎችም በየደረጃው የተጠናከረ መሰል ተቋም ይኖራቸዋል ተብሎ እንደሚታሰብ ሃላፊው ጠቁመዋል፡፡ ለጊዜው ግን በክልሎች በተለይ በኦሮሚያ ክልል ሆቴሎችን ከእሣትና ድንገተኛ አደጋዎች አንፃር የሚመዝን አካል ማን ይሁን የሚለው ተጨማሪ ውይይት ያስፈልገዋል ተብሏል፡፡
ሆቴሎች የኮከብ ደረጃ ምዘና ውስጥ ለመግባት የእሣትና ድንገተኛ መከላከያ አቅማቸው አስተማማኝነት ተረጋግጦ ሠርተፊኬት የሚሠጣቸው ሲሆን ከጤናና የስነምግብ መድሃኒት አስተዳደር ቢሮዎች አጠቃላይ የጤና እና የንፅህና አጠባበቅ ሠርተፍኬት ባለቤት መሆን ይጠበቅባቸዋል ተብሏል፡፡
በዋናነነት ከ1-5 የኮከብ ደረጃ ባለቤት የሚያደርጋቸው ደግሞ የአለማቀፉ የቴክኒክ ኮሚቴ ለአጠቃላይ አገልግሎታቸውና የህንፃ ውስጣዊና ውጫዊ ገጽታ እንዲሁም ለተለያዩ አገልግሎት አይነቶች በወጣው የፍተሻ ዝርዝር ነጥቦች ላይ አመርቂ ውጤት ሲያስመዘግቡ ብቻ ይሆናል፡፡
ዝርዝር መመዘኛው ያካተታቸው ዋና ዋና ጉዳዮች
የኮከብ ደረጃ ለማግኘት የሚመዘን ሆቴል ቢያንስ 10 የአልጋ ክፍሎች ያሉት መሆን ይጠበቅበታል፤ ባርና ሬስቶራንት ከቁርስ፣ ምሣ እና እራት አቅርቦት ጋር ሊኖረው ይገባል፤ ከአደጋ ደህንነት፣ ከጤና እና ከቆሻሻ አወጋገድ ጋር በተያያዘ ከተቆጣጣሪ አካላት ሠርተፊኬት ማግኘት ይጠበቅበታል፤ የእንግዳ መቀበያ ክፍል (ሪሴፕሽን) ሊኖረው ይገባል፤ እንዲሁም  እያንዳንዱ ክፍል የራሱ መታጠቢያ እና መፀዳጃ ቤት እንዲኖረው ይጠበቃል፡፡
እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት መሟላታቸው ተረጋግጦ በኋላ ወደ ዋናው ምዘና ከተገባ በኋላ የህንፃው የውጭኛው ክፍል የግንባታ ጥራትና ለግንባታ ግብአት የዋሉ ቁሶች የጥራትና የውበት ደረጃ ይገመገማል፡፡
 የግድግዳ ቀለም ውበት፣ ግድግዳው ከስንጥቅ ነፃ ስለመሆኑን የንፅህና ደረጃው እንዲሁም የመስታወት ጥራትና አጠቃቀሙ ነጥቦች ይሰጣቸዋል፡፡
ከውጫዊ የግድግዳና የህንፃ ውበት ጋር ተያይዞ የግቢው የአረንጓዴ ቦታ ይዞታ እና የመናፈሻ ቦታም ይዘትና ጥራት ይገመገማል፤ የመኪና ማቆሚያ ቦታ፣ የውጪና የውስጥ የደህንነት ጥበቃ ሁኔታም በዝርዝር ይታያል፡፡
ወደ መኝታ ክፍሎች ሲገባ ደግሞ የቤቱ የውስጥ ቅብ፣ ዲኮር፣ የፈርኒቸር ውጤቶች ጥራትና አይነት፣ ቴሌቪዥን፣ ስልክ፣ የፀጉር ማድረቂያ፣ የኤሌክትሪክ ሶኬት ደረጃ እና የቮልቴጅ አቅም ይገመገማል፡፡ በተለይ ባለኮከብ ለመሆን ያሰቡ ሆቴሎች በእያንዳንዱ የመኝታ ክፍል ፍላት ስክሪን ቴሌቪዥንና የwi-fi ኢንተርኔት አገልግሎት እንዲሁም የአነስተኛ ባር አገልግሎት በመኝታ ክፍሉ ማሟላት ይጠበቅባቸዋል፡፡
የውስጥ መስኮት መጋረጃዎች ጥራትና የውበት ደረጃም ይመዘናል፤ የጣራው ርቀት 2.86 ሜትር መሆን እንዳለበት የወጣው መስፈርት ጠቅሷል፡፡
 የአልጋ ስፋትን በተመለከተ ከ1 እስከ 3 ኮከብ የሚሰጣቸው ሆቴሎች የአልጋ ስፋታቸው ከ0.90 ሜትር በ1.90 ሜትር እስከ 1.35 ሜትር በ1.90 ሜትር አልጋ መዘርጋት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ባለ 4 እና 5 ኮከብ ሆቴሎች ደግሞ 1.40 ሜትር በ2 ሜትር የሆኑ አልጋዎችን መዘርጋት ይኖርባቸዋል፡፡ በተጨማሪም እንደሆቴሎቹ አቅም የኪንግ እና ኪዊን መጠነ አልጋዎችን ጥራት ካላቸው ፍራሾች እና አንሶላዎች ጋር መዘርጋት ይጠበቅባቸዋል፡፡
ሆቴሎች ለሚረብሹ ድምፆች የመጋለጥ እድላቸው ዝቅተኛ መሆን እንዳለበት ያስቀመጠው መስፈርቱ፤ በአካባቢ የሚኖር ድምፅ ከ40 ዲሴብል በታች መሆን እንዳለበት አስቀምጧል፡፡ ሆቴሎቹም ለድምፅ ብክለት ያላቸው ተጋላጭነት በዚህ ተገምግሞ ውጤት ይሰጣቸዋል፡፡
በእያንዳንዱ መኝታ ክፍል የመልበሻ መስታወቶች፣ የንባብ መፅሃፍትና ጋዜጣን ጨምሮ የተለያዩ ለእንግዳው ጠቃሚ የሆኑ ቁሳቁሶች መኖራቸውም የበለጠ ኮከብ ያስገኛል፡፡
 ከ3 እስከ 5 እና ከዚያ በላይ ኮከብ ማግኘት የሚፈልጉ ሆቴሎች የግዴታ የተለየ የሲጋራ ማጨሻ ክፍል ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል፡፡
ለሁሉም ዓይነት ተጠቃሚዎች የሚውሉ አገልግሎቶችን በማቅረብ ረገድ ለኮከብ ደረጃ የሚወዳደሩ ሆቴሎች የውበት ሳሎኖች፣ የስጦታ እቃ መሸጫ ሱቆች፣ አበባ መሸጫ እንዲሁም ኬክ ቤቶች ሊኖራቸው የሚገባ ሲሆን የውጭ ገንዘብ ምንዛሬ አገልግሎት፣ የጉብኝት አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች እና የታክሲ አገልግሎት ምን ያህል ፐርሰንት አሟልተዋል? የሚለው ተገምግሞ የኮከብ ማዕረጉ እንደነጥባቸው ይሰጣቸዋል፡፡
ከምግብ አቅርቦት ጋር በተገናኘም በዝርዝር የሚያቀርቡት የምግብ ዓይነትና ጥራት ተገምግሞ ነጥብ የሚሰጥ ሲሆን ባለ ኮከብ ሆቴሎች ሁሉም ቁርስ በነፃ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡
የሻወር አገልግሎት በዓይነትና በጥራት፣ ሳውናና ጃኩዚ፣ የልብስ ማጠቢያ ማሽን አገልግሎት በተለይ ለባለ 4 እና 5 ኮከብ ሆቴሎች የግዴታ ይሆናል፡፡
የመስፈርቱ መመዘኛ ነጥቦች ላይ በዝርዝር የቀረቡ የፍተሻ መጠይቆች የተካተቱ ሲሆን በዋናነት አንድ ሆቴል በሚያገኘው ውጤት መሰረት የኮከብ ደረጃ ለማግኘት የውጪ የህንፃ አካሉና አጠቃላይ የግቢ ገፅታው፣ የአልጋ ክፍሎቹ ጥራት፣ የመታጠቢያና ሽንት ቤት ጥራት፣ የህዝባዊ አገልግሎት መስጫ ቦታዎች የአገልግሎት አይነት በጥራት መሟላት እንዲሁም የባር እና ምግብ አገልግሎቱ፣ የቤት ንፅህና አያያዝና ጥገና፣ የደህንነት አስተማማኝነቱና ብቁ ሰራተኞችና የስራ ኃላፊዎች መኖራቸው ይገመገማል፡፡
በአጠቃላይ ከተቀመጡት ነጥቦች ከ90 በመቶ በላይ ያገኘ ሆቴል ባለ 5 ኮከብ ሌግዠሪ ደረጃ ይሠጠዋል፡፡ ከ80 በመቶ በላይ ያገኘ 5 ኮከብ፣ ከ70 በመቶ በላይ 4 ኮከብ፣ ከ60 በመቶ በላይ 3 ኮከብ፣ ከ50 በመቶ በላይ 2 ኮከብ እንዲሁም ከ30 በመቶ በላይ ውጤት ያመጣ ባለ 1 ኮከብ ደረጃ ይሰጠዋል፡፡
የሆቴሎች የኮከብ ደረጃ ምደባ ውጤት (ማን ምን ደረጃ አገኘ የሚለው) በሰኔ መጨረሻ ይፋ እንደሚደረግ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የገለፀ ሲሆን አንዳንድ ሆቴሎች ምዘናውን የተለያዩ ምክንያቶች በመደርደር እያፈገፈጉ ከመሆናቸው በስተቀር ስራው በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡   

Read 2667 times