Saturday, 02 May 2015 11:22

የ‘መሀል ጣት እብሪት’…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(5 votes)

እንዴት ከረማችሁሳ!
ስሙኝማ…አውራ ጣት ለ‘ፊርማም’ ቢሆን ታገለግላለች፣ አመልካች ጣት…አለ አይደል… ያው ታመለክታለች፣ (“ትጠቁማለች…” “ታስበላለች…” ማለት ይቻላል፣) ቀለበት ጣት ጣጣ የላትም፣ ትንሸኛዋ ጣት ደግሞ ጥፍር ሲያድግባት ‘ጌጥ’ ትሆናለች (ቂ…ቂ…ቂ…)፡፡ እናላችሁ… እኛ አሁን ግራ የገባን የመሀል ጣት በየመኪናው መስኮት የምትሰቀለው “ጌጥ አላደረጉኝም… የቀለበት ጣት አላደረጉኝም...ጥፍሬን አላሳደጉልኝም…” ምናምን ነገር ብላ ነው እንዴ! አሀ… ግራ ገባና! ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…እነኚህ ‘ሲክስቲ፣’ ‘ሰቨንቲ’ ምናምኗን አልፈው እንኳን በመኪና መስኮት ‘እብሪተኛ’ መሀል ጣታቸውን የሚቀስሩትን ስታዩ… “ታዲያ ይሄኛው ትውልድ
ምን ይፈረድበታል!” አያሰኛችሁም?
ከ‘መሀል ጣት እብሪት’ ይሰውረንማ!  
ሀሳብ አለን… ለአቅመ አዳምና ለአቅመ ሔዋን የደረሱ ሰዎች ‘እብሪተኛ’ መሀል ጣታቸውን በመስኮት ብቅ አድርገው ‘ሰንደቃቸውን’ ሲተክሉ ፎቶ ብልጭ አድርጎ ለልጆቻቸው…. “እየውልህ፣ አባትህ አንዲህ አይነት ሰው ነው…” “የእናትሽን ጉድ ተመልከቺ…” የሚባል ቢሆን ሳይሻል አይቀርም። ልክ ነዋ… ሌላው ላይ በተነጣጠረች ‘እብሪተኛ’ መሀል ጣት እኛም ለምን እንሳቀቃለን!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… የ‘እብሪተኛ’ መሀል ጣት ነገርን ካነሳን አይቀር ምን መሰላችሁ…ብዙ ቦታዎች ከ‘መሀል ጣት እብሪት’ የማይተናነሱ ነገሮች እያየን ነው፡፡ የምር ግን…እዚህ አገር የሞራል እሴቶቻችንን፣ የ‘ጨዋነት’ ምልክቶቻችንን ሁሉ ቀርጥፎ የበላብን ነገር ምን እንደሆነ እሱ ይወቀው፡፡
ከ‘መሀል ጣት እብሪት’ ይሰውረንማ!  
ስብሰባ የጠራ ‘ጉልቤ ነገር’ ሥራ አስኪያጅ ወይ የምናምን ተጠሪ ተሰብሳቢዎቹን በቅጡ እንኳን…

“እንደምን አደራችሁ…የጎን ውጋት አስቸገረን ያላችሁት ጠበሉ ሠራላችሁ ወይ…” ምናምን ነገር ሳይል… አለ አይደል… “አንዳንድ ሠራተኞች የድርጅቱን ምርታማነት ለማዳከም ሆነ ብለው…” ምናምን ብሎ ስብሰባውን በ‘መሀል ጣት እብሪት’ አይነት ይጀምረዋል፡፡ ጉዳይ ማስፈጸሚያ መሥሪያ ቤት በር ላይ ያለው ‘ሴኪዩሪቲ ጋርድ’  (በ‘ፈረንጅ አፍ’ ሲሆን ሞቅ ያደርገዋል ብዬ ነው) መጀመሪያ ከእግር እስከ ራሳችሁ ይገላምጣችኋል፡፡ ከዛማ ‘ከመጤፍም ስለማይቆጥራችሁ’… አይደለም በስነ ስርአት መልስ ሊሰጣችሁ… ጀርባውን ያዞርባችኋል፡፡
(እንትና…ያቺ ሰሞኑን ጎንህ አድርገህ የምትዞራት ግድንግዷ እሷዬዋ፣ ‘ሴኪዩሪቲ ጋርድህ’ ነች እንዴ!…ነው ወይስ በአንድ በኩል ‘ለጥበቃ’፣ በሌላ በኩል ‘ለእነሆ በረከት’ ሁለት ወፍ በአንድ ድንጋይ መምታትህ ነው! ቂ…ቂ…ቂ…) እናላችሁ… ‘ሴኪዩሪቲ ጋርዱ’ ምንም ቃል ሳይተነፍስ በግልምጫ ብቻ የ‘መሀል ጣት እብሪት’  ያሳይችኋል፡፡የዕድሩ ዳኛ…ገና እንቅልፋቸው ሳይለቃቸው እየተንጠራሩ “በስንት ልፋት የተቋቋመውን ዕድር
ለማፍረስ አንዳንድ አባላት ወርሀዊ መዋጮአቸውን ባለመከፈል ችግር እየፈጠሩብን ነው…” ምናምን
ይሉና ነገርዬውን… አለ አይደል… የ‘መሀል ጣት እብሪት’ አይነት ያደርጉታል፡፡‘ሰማይ ጥግ’ ያለው ባለስልጣን መልካም ሥራ ከሚሠሩት ብዙኃኑ ይልቅ፣ እሱ “እኩይ ተግባራት ይፈጽማሉ…” የሚላቸውን ‘ጥቂት ሰዎች’ እየጠቀሰ… “አንዳንድ ዕድገታችን ያልተዋጠላቸው…” ምናምን ብሎ የ‘መሀል ጣት እብሪት’ ነገር ያደርገዋል፡፡
ከ‘መሀል ጣት እብሪት’ ይሰውረንማ!  እግረ መንገዴን ይቺን ስሙኝማ…ለማኙ የሆነች ሸላይ ሴትዮ ‘ቶርታ’ ምናምን ነገር ጠቅልላ ስትሄድ ትገጥመዋለች፡፡ እናማ… “የእኔ እመቤት እንደው ኬክ ብትመጸውቺኝ…” ይላል፡፡ እሷዬም በሸላይኛ በዓይኗ እንትን ታየውና… “ኬክ! ደሞ ለራበው ሰው ዳቦ አነሰው እንዴ!” ትለዋለች፡፡ እሱዬው ምን ቢል ጥሩ ነው…“ምን መሰለሽ ዛሬ ልደቴ ነው፡፡” እንዲህም ይለመናል፡፡ ልክ እኮ… አለ አይደል…በፊት ጊዜ... “የሰው ጥርስ አውልቄ አስተክል ስለተባልኩ የተቻላችሁን እርዱኝ..” እንደሚሏት አይነት አለማመን ነች፡፡. እናላችሁ…ዛሬ ኬክ መጽውቱኝ ያለ ሰው ነገ ደግሞ ‘ሜኑ’ ይዞ ቢመጣ አትገረሙ፡፡
እኔ የምለው…እንደ ማኦ ዜዱንግ ዘመን ‘የባህል አብዮት’ ምናምን ሊያስፈልገን ነው እንዴ! አሀ…ነገርዬው ሁሉ ግራ ከመጋባትም እያለፈ ነዋ! የ‘መሀል ጣት እብሪት’ በተለያየ መልኩ ይከሰታል፡፡ ተናጋሪው ሁሉ፣ መግለጫ ሰጪው ሁሉ… የ‘መሀል ጣት እብሪት’ ስትራቴጂን ‘የሚተገብርበት’ (ቂ…ቂ…ቂ…) ጠላት ማግኘቱ ‘ኮምፐልሰሪ’ ምናምን የሚሉት አይነት ነገር ‘የጋራ ግንዛቤ የተወሰደ’ ይመስላል፡፡
ከ‘መሀል ጣት እብሪት’ ይሰውረንማ!  
የምር ግን ‘የባህል አብዮት’ ምናምን አይነት ነገር ቢፈጠር አንዳንድ ወዳጆቻችን ታዩኝ፡፡ እዚህ አገር እኮ የዕድሜ ልዩነት…ጉርምስና፣ አቅመ ዓዳም፣ አቅመ ሔዋን ቅብጥርስዮ ምናምን የሚል ነገር የቀረ ይመስላል፡፡ ልክ ነዋ…ለምሳሌ ጉርምስና ምናምን የሚባለው ነገር በአሥራ አንድም፣ በሠላሳ አንድም፣ በስድሳ አንድም ሊሆን ይችላል፡፡ አቅመ ሔዋን ምናምን የሚባለውም በአሥራዎቹ ወደታች እየወረደ… አለ አይደል…‘ማሙሽ’
‘ማሚቱ’ ማለት የሚቻለው የትኛው ዕድሜ ላይ እንደሆነ ግራ እየገባን ነው፡፡እናላችሁ…‘የባህል አብዮት’ የሚባለውን ነገር ቻይኖቹ ሹክ ያሉን ቀን ‘ሶሻል ሜዲያ’ ቀለጠ ማለት ነው፡፡… ስሙኝማ…የቻይናን ነገር ካነሳን አይቀር…አንዳንድ ቦታ በቻይንኛ ብቻ የተጻፉ ምልክቶች ምናምን እያየን ነው፡፡ ነገ ደግሞ ምናምን በሆነ ሬዲዮ ላይ የቻይንኛ ዝግጅት ክፍል የሚባል በቀን የአራት ሰዓት ምናምን ፕሮግራም ይጀመር ይሆናል፡፡ የምር ግን… የቀለጠ ፍቅራችንን ክፉ ዓይኖች እንዳያዩብን እዛው ይያዝልን፡፡ ልክ ነዋ…በኋላ ነገርዬው “ፍቅሬ ፍቅሬ በዛ፣ እኔ አላማረኝም…” ምናምን ነገር ያመጣላ! ከዛማ ያው የማይቀረው የ‘መሀል ጣት እብሪት’ ይመጣል! “ድሮስ እነሱን ብሎ ወዳጅ! የምንተነፍስውን ኦክሲጅን እንኳን ቢመቻቸው በ‘ፎርጀሪ’ ይሠሩት ነበር!”“ሀበሻ ሆዱ አይታወቅ፣ ልቡ አይታወቅ…ምስር ወጣቸውን በላንላቸው፣ ካቲካላቸውን ጠጣንላቸው!
እንትናዬዎቻቸው የቱሪስት ሂሳብ የሚጠይቁን ለምንድነው!”
ምናምን መባባል ይመጣል፡፡ ይህ “ዓይናችሁ ለአፈር…” ምናምን መባባል ደግሞ ‘ታሪካዊ ሀቅ’
ምናምን ነው ማለትም ይቻላል፡፡ ከስንቱ ጋር… “እኛም አንድ ሰሞን እንዲህ አርጎን ነበር…” ስንባባል

ኖረን የለ!
ከ‘መሀል ጣት እብሪት’ ይሰውረንማ!  ሀሳብ አለን… “ቅዳሜ ለእነሆ በረከት ይመችሻል ወይ…” “ሰውዬሽ ፊልድ የሚወጣው መቼ ነው…”
“የጓደኛዬ አክስት አርፈው የሠልስት አዳር አለብኝ ብለሽ ውጪ…” ምናምን አይነት ነገሮች በቻይንኛ
ምን እንደሚባሉ በ‘ዩቲዩብ’ ይለቀቅልንማ! እኛ ‘የቸገሩንን’ ነገሮች መች አጣናቸው! (የምር ግን…
ይሄኔ በቻይንኛ የ‘መሀል ጣት እብሪት’ ቃላትን የሚያውቅ መአት ሰው ይኖራል፡፡) እናላችሁ…የባህል አብዮት ምናምን የሚል ነገር ቢመጣ ‘ስታንድ አፕ’ ኮሜዲ በአዳራሽና በምሽት ክበብ ሳይሆን በየመንገዱ ይሆን ነበር፡፡ እናላችሁ…እኛ መሬት የሚጠርግ ሱሪ አጥልቀን እነሱ የዋናተኛ ሙታንቲ ልታክል ምንም ባልቀራት ቁምጣ ሲሄዱ ያላሰብነውን የሚያሳስቡን መአት ናቸው! ልክ ነዋ… አንድ አገር ተመሥርታ መካከለኛ ገቢ የምታልፍበት ዘመንን ያህል ‘ፉት’ አድርገው እንደ ‘ቲንኤጀር’ ሲያደርጋቸው የእኛ ኪሎ በመሳቀቅ መቀነሱ እየቀረ ነው! የምር እኮ…ቀለም እየተቀቡ ‘ዩዝ’ ምናምን ለመምሰል መሞከር ‘ያለፈበት ስትራቴጂ’ እየሆነ ነው፡፡ እናላችሁ…‘መሀል ጣት እብሪት’ ነገርም የሁላችን የጋራ መለያ ነገር እየሆነ ነው!   ከ‘መሀል ጣት እብሪት’ ይሰውረንማ!   ‘ባለፈው ስርአት’ ጊዜ በሥራ ሰዓት ጠጅ ሲጠጣ የተገኘ ሰው ጭንቅሌው ላይ ብርሌ ተሸክሞ በየመንደሩ እየዞረ… “እኔን ያያህ ተቀጣ!” እያለ ይዞር ነበር፡፡ እናላችሁ… የ‘መሀል ጣት እብሪት’ ነገር
እየበዛ “እኔን ያያህ ተቀጣ!” ምናምን የሚያሰኙ ነገሮች በዝተዋል፡፡ እናማ… ምን ይመስለኛል መሰላችሁ… የ‘መሀል ጣት እብሪት’ ከመብዛቱ የተነሳ ትንሽ ቆይቶ በምንም ነገር ላይ መግባባት ሁሉ ያቅተናል፡፡ እንኳን ሌላ ተጨምሮብን አሁንም መግባባት አቅቶናል፡፡ ይቺን ስሙኝማ…ልጁ አባቱን ይሄን ያህል አይወደውም ነበር፡፡ እናማ…አንድ ቀን ለአባቱ እንዲህ ይለዋል፡፡“አባዬ፣ ውሻዬን ሼክስፒር ብዬ ልጠራው ፈልጌ እማዬ ከለከለችኝ…” ይለዋል፡፡ አባትዬውም…“ለምን ከለከለችህ?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡“ሼክስፒርን መስደብ ይሆናል አለችኝ፡፡” “እና ምን አሰብክ?”“በአንተ ስም ልጠራው ፈልጌ እማዬ ከለከለችኝ።”“ለምንድነው የከለከለችህ?”
“የአንተን ስም መስጠቱ ውሻውን መስደብ ይሆናል አለችኝ፡፡” አሪፍ አይደል!... የ‘መሀል ጣት እብሪት’ ይሏችኋል እንዲህ ነው፡፡
ከ‘መሀል ጣት እብሪት’ ይሰውረንማ!  
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 4127 times