Print this page
Saturday, 02 May 2015 11:18

መንግስት፤ “ዜጐቼ ለምን ይሰደዳሉ?” ብሎ ይጠይቅ!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(13 votes)

“አሁንም እንሄዳለን፤ምንም ተስፋ የሚሰጥ ነገር የለም”
ኢህአዴግ ከስንት አንዴ ፕሮፓጋንዳው ቢቀርበትስ?

  መንግስት አይኤስ የተባለውን ጨካኝና አሸባሪ ቡድን ለማውገዝ የጠራው የተቃውሞ ሰልፍ እንደ አጀማመሩ አልተጠናቀቀም፡፡ (ለተቃውሞ ወጥቶ ተቃውሞ ገጥሞታል!) በሰላም የተጀመረው ተቃውሞ በረብሻና በብጥብጥ ተቋጨ፡፡ (መንግስትን መቃወም እኮ መብት ነው!) ትንሽ ቅር ያለኝ ግን ምን መሰላችሁ? ሁለት ተቃውሞዎች በአንድ ቀን፣ በአንድ ቦታ፣ መደረጋቸው ነው፡፡ እንደኔ ቢሆን ሁለቱ ተቃውሞዎች ባይደባለቁ እመርጥ ነበር (የሚያስመርጥ ሲኖር አይደል!) አንዳንዴ ተቃውሞ ፋታ አይሰጥም መሰለኝ፡፡ ተቃውሞ የነበራቸው ወገኖች የዚያኑ ዕለት መቃወሙን ግን ለምን ፈለጉት? ምናልባት ሌላ ቀን የሰልፍ ፈቃድ የሚሰጠን የለም ብለው ይሆናል (በስጋት ማለት ነው!) ወይም ደግሞ ጠ/ሚኒስትሩን ጨምሮ ትላልቅ ባለስልጣናትን መስቀል አደባባይ ሲያዩ፣ መንግስትን ለመቃወም ከዚህ የተሻለ ቀን ሊኖር አይችልም ብለውም ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ዕድሉን ተጠቀሙበት ማለት ነው፡፡ ግን እኮ---መንግስት የጠራውን ሰልፍ ረቡዕ፣ መንግስትን ለመቃወም ደግሞ ሐሙስን መጠቀም ይቻል ነበር (“ፈቃድ” ይገኛል በሚል ተስፋ ማለት ነው!) ያውም ደግሞ ያለ ወከባና ያለ ድንጋይ ውርወራ--! ግን በቃ የመሰላቸውን አደረጉ፡፡ ሌላው ጥያቄ ምን መሰላችሁ? ተቃውሟቸው በትክክል መንግስት ጋ ደርሷል? በነገራችን ላይ ፖሊስ ሰልፉን ለመበተን ጥይት ከመጠቀም ይልቅ አስለቃሽ ጭስ መጠቀሙ ሥልጣኔ ነው፡፡ (ጭሱ በእርዳታ ነው በግዢ?) የአንዳንዶቹ ፖሊሶች ድብደባ ግን ከጥይት አይተናነስም ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ ለማንኛውም በፖሊስ እጅ ገብታችሁ ዱላ ከበዛባችሁ፤ “ወገን ነን!” ማለቱን እንዳትረሱ፡፡(በሥራ ብዛት ልትረሱ ትችላላችሁ!) ሰሞኑን በጫማ ጥፊ የሚማታ ፖሊስ ፌስ ቡክ
ላይ ተለጥፎ አይቼ ክፉኛ ደንግጬ ነበር፡፡ (“ተስፋ የለንም!” በሚል) የተረጋጋሁት  የኔፓል ፖሊስ መሆኑን ስሰማ ነው፡፡ (አደራ የኔፓል ፖሊስን ተመክሮ እንዳትወስዱ!) እኔ የምለው-- በረቡዕ ሰልፍ ላይ የተነሳው ተቃውሞ ምን ነበር ? (የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ትንፍሽ አላለም ብዬ ነው!) እንግዲህ እስካሁን የሰማነው “የተቃውሞው አደራጅ ሰማያዊ ፓርቲ ነው” የሚል ክስ ብቻ ነው፡፡ (ፓርቲው በበኩሉ፤መንግስት ስሜን እያጠፋ ነው፤እከሳለሁ ብሏል!) በዚህ አጋጣሚ ግን ለመንግስትም ሆነ ለኢህዴግ አንድ ምክር በወንድምነት ብለግሳቸው እወዳለሁ፡፡ ከወገኖቻችን ግድያና ስደት ጋር በተገናኘ መንግስት ላይ የተሰነዘሩ ትችቶችና ተቃውሞዎች ካሉ (እሱማ የት ይጠፋሉ!) ሸፋፍኖ ማለፍ አይመክርም፡፡ ይልቁንም “ጉዱን” በደንብ
ሰምቶ፣ እሱም የራሱን በደንብ አስረድቶ፣ ወደ መፍትሄ መግባት ብልህነት ነው፡፡ ይሄ የስደት ጉዳይ በጊዜ መላ ካልተበጀለት ጊዜ ጠብቆ የሚፈነዳ ቦንብ ነው፡፡ (ደሞ ጀማምሮታል!) መንግስት ዜጎች ዘንድ “ብዥታ” አለ ብሎ የሚያምን ከሆነ፣ ማጥራት የሱ ሃላፊነት ነው፡፡ የአመለካከት ችግር ነው የሚል ከሆነም አመለካከት ላይ መሥራት ይኖርበታል፡፡ እንደ እስከዛሬው  ነገሩን ሁሉ በ“ህገወጥ ደላላ” ላይ አሸክሞ መቀመጥ አያዋጣም፡፡ (አዝማሚያው እንደዛ ይመስላል!) በነገራችን ላይ ባለፈው እሁድ አርቲስቶች በግፍ ለተገደሉ ወገኖቻችንን መታሰቢያ በብሔራዊ ቴአትር ባዘጋጁት ፕሮግራም “ህገወጥ ደላሎች” ላይ የእርግማን መዓት ሲያወርዱ ነበር (እርግማን እንደ ግጥም ጽፈው!) እውነቱን ለመናገር ግን አሁን የሚያስፈልገው እርግማን ሳይሆን እርምጃ ነው!
እኔ የምለው ግን----እስካሁን የተያዘ አንድ እንኳን ህገወጥ ደላላ አለ ወይስ ዝም ብለን ነው እርግማን  የምናወርደው? (እርግማን እኮ ውጤት ተኮር አይደለም!)  በነገራችን ላይ አንዳንድ የማይገቡን ወይም እንዳይገቡን የተደረጉ ነገሮች ያሉ ይመስለኛል፡፡ የናንተን ባላውቅም----እኔ ግን ይሄ የስደት ጉዳይ ሁሌም ግራ እንዳጋባኝ ነው፡፡ የስደት ጉዳይ በተነሳ ቁጥር መንግስት ለአፍታ እንኳን ማሰብ ሳያስፈልገው መልስ ይሰጣል - “ዜጎች በአገራቸው ሰርተው መክበር እየቻሉ ነው ስደት የሚሄዱት” በማለት በቀላሉ ይዘጋዋል፡፡ እኔና እናንተ ግን ግራ ይገባናል፡፡ ዜጎች እንደጉድ መሰደዳቸው፣ ባህር ውስጥ እየተጣሉ የዓሳ ነባሪ እራት መሆናቸው፣ በደላሎች መሰቃየት መታለላቸው፣ በረሃብና በጥማት በየበረሃው መቅረታቸው---እነዚህን ሁሉ መከራዎች የሰሙ ዜጎች  ምንም እንዳልሰሙ ሆነው ለስደት ሲነሱ -- ለሞት ሲዘጋጁ፣ ግራ ያጋባል፡፡ ማናችን ነን የተሳሳትነው? እኔና እናንተ? እነሱ? ወይስ መንግስት?  ሰሞኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት በድረገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ፤በአሁን ሰዓት የኢትዮጵያውያን ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ ወደ 630 ዶላር ግድም መሆኑን ጠቁሞ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ወደ 1ሺ ዶላር እንደሚደርስ አስታውቋል፡፡ (መንግስት ቁጥሩን በኑሮ እየመነዘረ ይንገረን!) ለምሳሌ የነፍስ ወከፍ ገቢያችን 630 ዶላር በመሆኑ፣ በህይወታችን ላይ ከበፊቱ ምን
ጨመርን? ወደ 1ሺ ዶላር ስንገባስ ለውጣችን ምን ይሆናል? (ቁጥሩ ቀርቶ ተጨባጩ ኑሮ ብቻ!) መንግስት ስደትን በተመለከተ በዜጎች ዘንድ የአመለካከት ለውጥ እንደሚያስፈልግ በተደጋጋሚ ሲናገር እንሰማለን፡፡ ስህተት የለውም፡፡ በእርግጥም የአመለካከት ለውጥ ያስፈልጋል፡፡ አሁን ሳስበው መጀመሪያ የአመለካከት ለውጡ የሚያስፈልገው ለራሱ ለመንግስት ነው፡፡ አንዳንዴ ምን እላለሁ መሰላችሁ? “መንግስት የሚነግረን የሚመኘውን ነው ወይስ መሬት ላይ ያለውን እውነታ?” ቆይ እሱ እንደሚለው ዜጐች በአገራቸው ሰርተው መክበር የሚችሉ ከሆነ፣ ለምንድነው ወደ ሰው አገር የሚጎርፉት? ለምንድነው ወደ ሞት የሚጋፉት? ለምንድነው የበረሃ ሲሳይ ለመሆን የሚጣደፉት? መቼም ምክንያት መኖር አለበት፡፡ መንግስት ይሄን ጉዳይ ከፖለቲካና ፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ውጭ በጥልቀት አጥንቶና አስጠንቶ ወደ መፍትሄው ለመቅረብ መትጋት አለበት፡፡   ባለፈው እሁድ በወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ያነበብኩት ነገር ክፉኛ አስደንግጦኛል፡፡ ጓደኞቻቸው ሊቢያ በሚገኘው አሸባሪ ቡድን በግፍ የተቀሉባቸው የጨርቆስ ወጣቶች፣ አሁንም የስደት ሃሳባቸውን እንዳልቀየሩ ለጋዜጣው ተናግረዋል፡፡ አንደኛው ወጣት፤ “አሁንም እንሄዳለን፤ምንም ተስፋ የሚሰጥ ነገር የለም፤እድላችንን እንሞክራለን”፣ሁለተኛወ ወጣት፤ “ህገወጥ ስደተኞች አትበሉ፤ ልጆቹ ህገወጥ አይደሉም፤እንጀራ ፈላጊ ናቸው”ሦስተኛው ወጣት፤ “ስብሰባ ጠርተው ሃምሳ ሃምሳ ብር ሰጥተው፣ ወጣቱ እየሰራ ነው የሚል ፕሮፓጋንዳ ከሚሰሩብን ምን አለ ስራ ቢፈጥሩልን?” (ወጣቶቹን ያነጋገረው የሪፖርተር ጋዜጠኛ፤ሁሉም በተስፋ መቁረጥ መንፈስ ውስጥ እንዳሉ ነው የገለጸው፡፡) ለማንኛው ግን መንግስት ለስደት ጉዳይ መፍትሄ ለማበጀት ከመነሳቱ በፊት ራሱን እንዲህ ብሎ ይጠይቅ፤  “ዜጐቼ ከገዛ አገራቸው የሚሰደዱት ለምንድን ነው?”  

Read 3675 times