Saturday, 02 May 2015 10:39

የፖለቲካ ጥግ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

ምርጫ
በአፍሪካና በአውሮፓ
*አል ባሺር ተቃዋሚዎች በሌሉበት በዝረራ አሸነፉ
*የ71 ዓመት ባለጸጋ፤የ26 አመት ሥልጣን

    እምብዛም የማይገርማችሁን አንድ ወሬ ልንገራችሁ፡፡ ለ26 ዓመታት ሱዳንን የገዙት የ71 ዓመቱ የዕድሜ ባለፀጋ ኡመር ሃሰን አልበሽር፤ሰሞኑን በሱዳን በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ 94 በመቶ ድምጽ በማግኘት አሸንፈዋል ተባለ፡፡ ምርጫ የተባለው ወጉ እንዳይቀር ነው እንጂ አልበሽር ለብቻቸው ነው የተወዳደሩት፡፡ ዋና ዋና የአገሪቱ ተቃዋሚዎች ቀደም ብለው ነው ራሳቸውን ከምርጫው ያገለሉት፡፡  ምርጫው ነጻና ፍትሃዊ አልነበረም የሚሉት ተቃዋሚዎቹ፤ ሲቪል ማህበራትና ሚዲያው በመንግስት ታፍነው እንደነበር ይናገራሉ፡፡ በነገራችን ላይ አልበሽር በ1989 ዓ.ም በመፈንቅለ መንግስት ሥልጣን ላይ ከወጡ በኋላ ይኸው ለ26 ዓመታት ሱዳንን ሲገዙ ቆይተዋል፡፡ አልበሽር በዓለም አቀፉ የጦር ፍ/ቤት የዘር ማጥፋት እንዲፈጸም በማዘዝ ተከሰው በተገኙበት እንዲያዙ ውሳኔ ተላልፎባቸው ነበር፡፡ በኋላ ግን ዕድሜ ለአፍሪካ ህብረት! ያለመከሰስ ሬዚዳንታዊ መብት አላቸው በሚል የፍርድ ቤቱን አንቀበልም ብሏል፡፡ የሱዳንን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የአፍሪካ ህብረት ታዛቢ ቡድን የታዘበው ሲሆን አውሮፓ ህብረት፣ አሜሪካ፣እንግሊዝ፣ኖርዌይ ምርጫውን ተችተውታል፡፡ ከወዳጆቿ ጋር በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ካልሆነ በቀር በፖለቲካዊ ጉዳዮች “ጾመኛ” የሆነችው የቻይና ፕሬዚዳንት በበኩላቸው፤ ለአልበሽር የእንኳን ደስ አልዎ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡አሁንም ከምርጫ አልወጣንም፡፡ ቦታው ግን አውሮፓ ነው፡፡ ጊዜው ደግሞ የዛሬ 12 ዓመት፡፡ የኖርዌይ የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር ጄንስ ስቶልትንበርግ፤ራሳቸውን ለምርጫ ውድድር እያዘጋጁ ነበር- ለሦስተኛ ጊዜ አገራቸውን በጠ/ሚኒስትርነት ለመምራት፡፡ ከአገሪቱ ንጉስ ጋር መደበኛውን የአርብ ስብሰባ ከተሰበሰቡ በኋላ አንድ ለየት ያለ ነገር ልሞክር ብለው አሰቡ - ስቶልትንበርግ፡፡ (ማንም ሞክሮት የማያውቅ!) ምርጫ እየደረሰ ስለነበር ጠ/ሚኒስትሩ የድምጽ ሰጪውን ትክክለኛ የልብ ትርታ ለማወቅ ነበር የፈለጉት፡፡ ይሄን የት እንደሚያገኙት ደግሞ ያውቃሉ፡፡ ታክሲ ውስጥ! እናሳ? “እንደ ጠቅላይ ሚኒስትርነቴ የሰዎችን አስተያየት መስማት ይጠቅመኛል፤ ሰዎች የልባቸውን የሚናገሩበት ቦታ ቢኖር ደግሞ ታክሲ ውስጥ ነው” ብለዋል ጠ/ሚኒስትሩ፤ በወቅቱ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃለምልልስ፡፡ ም ኖርዌይን ሁለት ጊዜ በጠ/ሚኒስትርነት ያገለገሉት ስቶልትንበርግ፤ የኦስሎ ታክሲ ነጂዎችን ዩኒፎርም ለበሱና የፀሃይ መነፅራቸውን ሰክተው ታክሲ መሾፈር ጀመሩ፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ለአንድ ተሲያት በኋላ የከተማዋን ነዋሪዎች እያሳፈሩ አገልግሎት ሰጡ - እግረመንገዳቸውንም አስተያየት እያደመጡ፡፡ ከታክሲ ተሳፋሪዎቹ መካከል አንደኛዋ፤ “በዚህ በኩል በጣም ነው ስቶልትንበርግን የምትመስለው” ብላቸዋለች ጠ/ሚኒስትሩን ሹፌር፡፡ ሌላኛዋ ተሳፋሪ ደግሞ ደብዳቤ ልትልክላቸው ትፈልግ እንደነበር ጠቁማ እሳቸውን ታክሲ ውስጥ በማግኘቷ ዕድለኛነቷን ገልፃለች፡፡
ተሳፋሪዎች ከሹፌሩ ጋር የሚያደርጉት ጭውውት በአብዛኛው ወደ ፖለቲካ ያደላ ነበር፡፡ ሚ/ር ስቶልትንበርግ ከአንድ ተሳፋሪ ጋር በትምህርት ጉዳይ ላይ አውርተዋል፡፡ “ዋናው ነጥብ ጎበዝ ተማሪዎች የሚያልሙት ነገር መኖሩን ማረጋገጥና ለሚፍጨረጨሩት ደግሞ  ተጨማሪ እገዛ ማድረግ ነው” ሲሉ ጠ/ሚኒስትሩ ለተሳፋሪው ነግረውታል፡፡ ሰውየው በኦስሎ ታዋቂ ነበሩ፡፡ በዚህም የተነሳ ኋላ መመልከቻ መስተዋት በማየት ብቻ ያወቋቸው ተሳፋሪዎች ነበሩ፡፡ ሰዎች እስካላወቋቸው ድረስ ግን ማንነታቸውን አይገልጹም ነበር፡፡ እናም… የመራጩን ህዝባቸውን እውነተኛ ስሜት … ሃሳብ … እይታ የቻሉትን ያህል ተገነዘቡ፡፡ በእርግጥ ጠ/ሚኒስትሩ በምርጫው አላሸነፉም፡፡ ቁምነገሩ ግን እሱ አይደለም፡፡ ለሚመሩት ህዝብ ያላቸው   አመለካከት ነው፡፡ የአፍሪካ መሪዎች የመራጩን ህዝብ እውነተኛ ስሜት ለመረዳት --- ለማወቅ የሚጨነቁ ይመስላችኋል? (አረ ሲያልፍም አይነካቸው!) እነሱም ግን ምርጫ ሲደርስ አንድ ለየት ያለ ነገር ያደርጋሉ፡፡ (ታክሲ ባይነዱም!) ህገ
መንግስት በመደለዝ የስልጣን ዕድሜያቸውን ያራዝማሉ፡፡ (ሰው እንደየተሰጥኦው ነው!) የአፍሪካ መሪዎች ከማንም በላይ ሥልጣንን ቢወዷትም በቀጥታ ከህዝብ አይደለም የሚወስዷት፡፡ ሲመቻቸው ይነጥቃሉ፡፡ ያጭበረብራሉ፡፡ ራሳቸው ያወጡትን ህግና ህገመንግስት እስከመደለዝ ሁሉ ይደርሳሉ፡፡ የታክሲ ሹፌር ሆኖ የህዝብን የልብ ትርታ ማዳመጥ?--- የሚለውን ግን እርሱት!በነገራችን ላይ በቡሩንዲ ከወር በኋላ በሰኔ አጋማሽ ላይ ሊካሄድ በታሰበው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ወቅት ሊቀሰቀስ ይችላል ብለው ያሰቡትን ብጥብጥ በመስጋት፣ 17 ሺ ቡሩንዲያውያን ከመጋቢት አጋማሽ ጀምሮ ወደ ጎረቤት አገራት (ሩዋንዳና የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ) እንደተሰደዱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቁሟል፡፡ (በአፍሪካ ምርጫ ያሰድዳል!) የፈሩት አልቀረም፡፡ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ፒሬ ንኩሪኒዛ ፤ህገመንግስቱ ከሚፈቅደው ውጭ ለሶስተኛ ዙር ሊወዳደሩ
መዘጋጀታቸውን ተከትሎ ባለፈው እሁድ ተቃውሞ የገጠማቸው ሲሆን ፖሊስ ሰልፉ ህገወጥ ነው (ህገወጥ እኮ ፕሬዚዳንቱ ናቸው!) በሚል ከሰልፈኛ ጋር በፈጠረው ግጭት፣ ሁለት የተቃዋሚ ሰልፈኞችን የገደለ ሲሆን አራት እንደቆሰሉ የቡሩንዲ ቀይ መስቀል ማህበር ቃል አቀባይ አሌክሲስ ማኒራኪዛ ለሮይተርስ ተናግረዋል፡
በነገራችን ላይ የአፍሪካ መሪዎችና ምዕራባውያን ረብሻና ጠብ ይፈጠራል በሚል የቡሩንዲው ሬዚዳንት በምርጫው እንዳይወዳደሩ አሳስበዋቸው ነበር (“ሚስትህ ወለደች ወይ ቢሉት ማንን ወንድ ብላ” አለ አበሻ!) አሜሪካና አውሮፓም የሳቸውን ወደ ምርጫ መግባት ተከትሎ ብጥብጥ ቢነሳ እርምጃ እንደሚወስዱ ጠቁመዋል (የሰማቸው የለም እንጂ!) አያችሁልኝ አይደል … የአፍሪካን ነገር! አንድ አምባገነን በስልጣን እንዲቀጥል ሺዎች የሚገደሉባት ከንቱ  አህጉር ናት፡፡ እኔ የምለው …. ይሄ አፍሪካ ህብረት የሚባል ድርጅት ውስጡ ሰው የለም እንዴ?! (የቻይና ህንፃ ብቻ እኮ ነው የሚመስለው!)  

Read 2451 times