Saturday, 02 May 2015 10:26

ነዋይና ጎሳዬ ለሰማዕታቱ የመታሰቢያ ዜማዎች ሰሩ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

   ታዋቂዎቹ ድምፃዊያን ነዋይ ደበበ እና ጎሳዬ ተስፋዬ በሊቢያ አሰቃቂ ግድያ ለተፈፀመባቸው   ኢትዮጵያውያን ሰማዕታት መታሰቢያ የሚሆኑ ዜማዎችን እንደሰሩ ለአዲስ አድማስ ገለፁ፡፡
ኢትዮጵያውያን ለገጠማቸው ብሄራዊ ሃዘን ከማንም በላይ የጥበብ ሰዎች ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው ያለው ነዋይ፤ ህዝቡ አንደበታችን ብሎ የጥበብ ሰዎችን ስለሚወክል እኔም  የተሰማኝን ጥልቅ ሀዘን ለመግለፅ ሙዚቃውን ሰርቻለሁ ብሏል፡፡ “በኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን ላይ የተፈፀመው ግፍ መቆም አለበት ብለን ዛሬ ካልወሰንን ነገ የባሰ እንዳይመጣ ያሰጋኛል” ያለው ድምፃዊ፤ ሙዚቃውን ህዝቡን ለማፅናናትና መልዕክት ለማስተላለፍ እንደሰራው ተናግሯል፡፡
“ሁሉም ያልፋል እስኪያልፍ ግን ያለፋል” በሚል ስያሜ የሰራሁት ሙዚቃ እንደ መዝሙር ሊታይ የሚችልና ዜማዊ ማስተማሪያ የሚሆን ነው ያለው ድምፃዊው፤ ግጥምና ዜማውን ራሱ እንደሰራው ገልፆ ሙዚቃውን ያቀናበረለት ወደፊት በሚያወጣው አልበሙ ከአምስት በላይ ዘፈኖችን የሰራለት ታምራት አማረ በቀና እንደሆነ ገልጿል፡፡ ሙዚቃው ከትናንት ጀምሮ በተለያዩ የኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች መሰማት እንደጀመረ ጠቁሞ፤ ለሙዚቃው ክሊፕ ለመስራት በሳምሶን ስቱዲዮ በኩል እየተንቀሳቀስን ነው ብሏል፡፡  
እንዲህ ያለ መሪር ሀዘን ሲያጋጥም ቅስም ይሰብራል ያለው ጐሳዬ በበኩሉ፤ በወገኖቻችን ላይ የተፈፀመው ግፍ ከተወለድኩበት ጊዜ ጀምሮ ተሰምቶኝ የማያውቅ ጥልቅ ሀዘን ፈጥሮብኛል ብሏል፡፡ ሀዘኑን የሰማሁት አዳዲስ ስራዎችን እያዘጋጀሁ ባለሁበት ሰዓት ነው ያለው ጎሳዬ፤ እንደ ድምፃዊነቴ ሀዘኔን የምገልፀው በጉሮሮዬ በመሆኑ “አኬልዳማ” የሚል የመታሰቢያ ሙዚቃ ሰርቻለሁ ብሏል፡፡ አገሪቱን በገጠማት ሀዘን ኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆኑ የኢትዮጵያ ደም ያላቸው የዓለም ህዝቦች ሁሉ ክፉኛ ማዘናቸው ልቤን ነክቶታል ያለው ወጣቱ ድምፃዊ፤ በሙያው ያለውን ለማበርከት ማቀንቀኑን ተናግሯል፡፡
የመታሰቢያ ሙዚቃውን ግጥም፣ ዜማና ቅንብር የሰራው መኮንን ለማ (ዶክተሬ) እንደሆነ የገለፀው ጎሳዬ፤ ጌታቸው ኃይለማርያም አብሮት እንደተጫወተ፣ አሌክስ ባሪያው ደግሞ ካጀቡት ድምፃዊያን አንዱ እንደሆነ ተናግሯል፡፡
 የጎሳዬ “አኬልዳማ” ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በተለያዩ የሬዲዮ ጣቢያዎች እየተሰማ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በድሬደዋ የጎርፍ አደጋ ባጋጠመበት ወቅት የመታሰቢያ ሙዚቃ ሰርቼ ነበር ሲል ያስታወሰው ጎሳዬ፤ ማህበራዊ ሃላፊነቴን ለመወጣት ምንጊዜም ከኢትዮጵያዊያን ወገኖቼ ጎን እቆማለሁ ብሏል፡፡       

Read 3873 times