Saturday, 25 April 2015 11:06

አውሮፓ በሊቢያ ህገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ልትፈጽም እየተዘጋጀች ነው
  በዚህ ወር ብቻ ከ1 ሺህ በላይ ስደተኞች በሜዲትራኒያን ባህር ሞተዋል
በእሁዱ የጀልባ አደጋ የተጠረጠሩ ፍርድ ቤት ቀርበዋል
       የሜዲትራኒያን ባህርን አቋርጠው ወደ አውሮፓ አገራት ለመግባት ሲሞክሩ ለህልፈተ ህይወት በሚዳረጉ ስደተኞች ዙሪያ ለመምከር ከትናንት በስቲያ በብራስልስ አስቸኳይ ስብሰባ የጠሩት የአውሮፓ አገራት መሪዎች፣ ሊቢያውያን ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን ለማጥቃትና አካባቢውን ለማረጋጋት የሚያስችል ወታደራዊ ዘመቻ ለማካሄድ ዝግጅት እያደረጉ እንደሆነ አልጀዚራ ዘገበ፡፡
በዚህ አመት ብቻ 36 ሺህ ያህል የተለያዩ አገራት ዜጎች ባህር አቋርጠው በስደት ወደ ጣሊያን፣ ማልታ እና ግሪክ እንደገቡ የጠቆመው ዘገባው፣ የአውሮፓ መሪዎች ስደተኞችን በህገወጥ መንገድ የሚያጓጉዙ ጀልባዎችን ተከታትሎ በመለየት በቁጥጥር ስር የሚያውልና በሊቢያውያን ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ላይ እርምጃ የሚወስድ የአውሮፓ ጥምር ወታደራዊ ዘመቻ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል ብሏል፡፡
ባለፈው እሁድ ከሊቢያ በመነሳት ሜዲትራኒያን ባህርን አቋርጣ ወደ ጣሊያን ስትቃረብ በሰመጠችው ጀልባ ከ800 በላይ የተለያዩ አገራት ዜጎች ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውን ተከትሎ አስቸኳይ ስብሰባ ያደረጉት መሪዎቹ፣ በሜዲትራኒያን ባህር ስደተኞችን ለማዳን ለሚከናወኑ ተግባራት የሚሰጡትን የገንዘብ ድጋፍ በሶስት እጥፍ ለማሳደግ የተስማሙ ሲሆን በወር በድምሩ 9.7 ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል ገብተዋል፡፡
የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን ስደተኞችን ለመታደግ የሚሰሩ ስራዎችን ለማገዝ የሚውሉ ሶስት ሄሊኮፕተሮችንና ሁለት መርከቦችን ለመስጠት ቃል ሲገቡ፣ ጀርመንና ፈረንሳይም እያንዳንዳቸው ሁለት መርከቦችን ለመስጠት ቃል መግባታቸውን ዘገባው ገልጧል፡፡
የውሮፓ አገራት መሪዎች በህገወጥ ስደት ለህልፈተ ህይወት የሚዳረጉ ዜጎችን ጥፋት ለመቀነስና ዜጎቻቸው ከሚሰደዱባቸው አገራትና የስደተኞች መተላለፊያ ከሆኑ አገራት ጋር በትብብር መስራትን ጨምሮ፣ ለስደት ምክንያት የሆኑ ችግሮችን የመቅረፍ ስራ በስፋት ለመስራት ተስማምተዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት በበኩሉ ባለፈው ሰኞ በሜዲትራንያን ባህር የሚከሰተውን የስደተኞች ሞት ለመቀነስና ቀጣይ ጥፋቶችን ለመቀነስ የሚያስችል ባለ 10 ነጥብ የድርጊት መርሃ ግብር ቢያወጣም፣ መርሃግብሩ ጥፋትን ከመቀነስ ይልቅ የሚያባብስና ተጨማሪ ስደተኞችን ለስደት የሚያበረታታ ነው በሚል እየተተቸ እንደሚገኝ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡  
በዘንድሮው አመት ብቻ ሜዲትራኒያን ባህርን አቋርጠው ወደ አውሮፓ አገራት ለመግባት ሲሞክሩ ለህልፈተ ህይወት የተዳረጉ ስደተኞች ቁጥር ከ1 ሺህ 700 በላይ መድረሱን የዘገበው ቴሌግራፍ በበኩሉ፣ ይህ የሞት መጠን ባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ከተመዘገበው ጋር ሲነጻጸር በ30 እጥፍ እንደሚበልጥም ገልጧል፡፡
አሶሼትድ ፕሬስ በበኩሉ የተመድ የስደተኞች ድርጅትን ጠቅሶ ከትናንት በስቲያ ባወጣው ዘገባ፣ ባለፈው አመት ብቻ 219 ሺህ ያህል ስደተኞች ሜዲትራኒያን ባህርን አቋርጠው በህገወጥ መንገድ ወደ አውሮፓ አገራት መግባታቸውንና ከ3 ሺህ 500 በላይ የሚሆኑም በጉዞ ላይ ሳሉ ለሞት መዳረጋቸውን አስነብቧል፡፡ ከእነዚህ መካከልም ከ1ሺህ በላይ የሚሆኑት በዚህ ወር ብቻ መሞታቸውንም አስታውቋል፡፡
ጣሊያን ባህር አቋርጠው የሚመጡ ስደተኞችን ከአደጋ ለመታደግ በሊቢያ ድንበር አቅራቢያ ታደርግ የነበረውን እንቅስቃሴ በጥቅምት ወር 2014 ማቋረጧ፣ ለሟቾች ቁጥር ማሻቀብ ምክንያት ሆኗል ብለው የሚተቹ አስተያየት ሰጪዎች መኖራቸውንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡  
ባለፈው እሁድ ከደረሰውና በአካባቢው ከደረሱ መሰል አደጋዎች ሁሉ የከፋ ጥፋት የደረሰበት ነው በተባለው አደጋ ከ800 በላይ ሰዎች መሞታቸውንና ስደተኞቹ ኤርትራ፣ ሶማሊያና ሶሪያን ጨምሮ የ20 የተለያዩ አገራት ዜጎች እንደሆኑም ሲ ኤን ኤን ዘግቧል፡፡
ከእሁዱ የስደተኞች ጀልባ አደጋ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው ሲሲሊ ውስጥ በፖሊሰ ቁጥጥር ስር የዋሉት የጀልባዋ ካፒቴንና አንድ የህገወጥ የሰዎች ዝውውሩ ተሳታፊ ትናንት ፍርድ ቤት ቀርበው ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡

Read 2549 times