Saturday, 25 April 2015 11:06

የቀድሞው የግብጽ ፕሬዚዳንት የ20 አመት እስር ተፈረደባቸው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

22 የሙስሊም ብራዘርሁድ ደጋፊዎችም በሞት ተቀጥተዋል
የቀድሞው የግብጽ ፕሬዚዳንት ሞሃመድ ሙርሲ፣ በስልጣን ዘመናቸው ዜጎች ያለአግባብ እንዲገደሉ፣ እንዲታሰሩና እንዲሰቃዩ መመሪያ አስተላልፈዋል በሚል ተከስሰው የ20 አመት እስር እንደተፈረደባቸው ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ከሁለት አመታት በፊት በግብጽ የተቀጣጠለውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ከስልጣናቸው የወረዱት የሙስሊም ብራዘርሁድ  መሪ ሞሃመድ ሙርሲ፣ በታህሳስ ወር 2012 በቤተመንግስታቸው አቅራቢያ ለተቃውሞ የወጡ ከአስር በላይ ግብጻውያን እንዲገደሉ፣ ብዙዎችም እንዲታሰሩና ለስቃይ እንዲዳረጉ ትዕዛዝ መስጠታቸውን አረጋግጫለሁ በማለት ነው ፍርድ ቤቱ ቅጣቱን የጣለባቸው ተብሏል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ በካይሮ የዋለው ችሎት ከሙርሲ በተጨማሪ በሌሎች 12 የሙስሊም ብራዘርሁድ ባለስልጣናት ላይ ተመሳሳይ የእስራት ቅጣት እንደጣለ ዘገባው ጠቁሟል፡፡
ሙርሲ በተቃዋሚዎች ላይ ግድያ መፈጸምን ጨምሮ የሞት ቅጣት ሊያስጥሉባቸው የሚችሉ ሌሎች ክሶች በተለያዩ ፍርድ ቤቶች እንደተመሰረቱባቸው ያስታወሰው ዘገባው፤ ይሄኛው ፍርድ ቤት ግን የቀረቡለትን የግድያ ክሶች ውድቅ ማድረጉንና ለግድያና ለእስራት ትዕዛዝ መስጠት በሚለው ክስ ብቻ ቅጣቱን እንደጣለባቸው አስታውቋል፡፡
የሙስሊም ብራዘርሁድ የቀድሞ ከፍተኛ ባለስልጣን አምር ዳራግ፤ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ፍትህን ያዛባ ነው ሲሉ ተችተውታል፡፡
ባለፈው ሰኞ 22 የሙስሊም ብራዘርሁድ ደጋፊዎች በካይሮ በሚገኝ የፖሊስ ጣቢያ ላይ ጥቃት አድርሳችኋል በሚል ተከሰው የሞት ቅጣት እንደተላለፈባቸው የገለጸው ዘገባው፤ ታዋቂውን የሙስሊም ብራዘር ሁድ የቀድሞ መሪ ሞሃመድ ባዴን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ የቀድሞው የግብጽ አስተዳደር ባለስልጣናት ከዚህ በፊት የሞት ፍርድ እንደተጣለባቸውም ጨምሮ አስታውሷል፡፡

Read 1926 times