Saturday, 25 April 2015 11:04

“ልብ ብዬ ሳየው የሚያስቀኝ መፅሐፍ አለኝ”

Written by  ዓለማየሁ ገላጋይ
Rate this item
(4 votes)

“ትክ ብዬ ሳያት የምታስቀኝ ሚስት አገባሁ” ያለ አንድ የአገሬ ሰው አለ፡፡ ይሄ ግለሰባዊ መትከንከን ምሳሌያዊ አነጋገር የሆነው ለብዙ ሰዎች በቀጥታ አለያም በተዘዋዋሪ ተተርጓሚነት ስላለው ነው፡፡ ይሄኔ ምሳሌያዊ አነጋገሩ በተወለደበት ዘመን “…አለ፣ አያ እከሌ” እየተባለ ይነገር የነበረ ይሆናል። ከጊዜ ብዛት፣ ከበባታ መስፋት “አያ እከሌ” ተዘንግቶ፣ ምሳሌው እርቃኑን ቀርቶ ይሆናል፡፡ (እንዲያም አለ እንዲህ) ምሳሌው እኔ ጋ ደርሶ ዛሬ መግቢያ አድርጌዋለሁ፡፡ መግቢያ ብቻ ሳይሆን እንግዳ ስሜቴን ቅልብጭ አድርጐ የሚያሳይ ዘዴ ሆኖ አገልግሎኛል፡፡ እንዲህ፡-
“ልብ ብዬ ሳያቸው የሚያስቁኝ መፅሐፍት ገዛሁ” እንዴ? ያሰኛል፡፡ መልሱ እንዲህ ነው፡-
አንዳንድ መፅሐፍት አሉ፤ የአንባቢን ድክመት መሰረት አድርገው የሚዘጋጁ፡፡ እነዚህ መፃህፍት በተለይ ከሰው በስጦታ መልክ ከቀረቡ እንደ ስድብም የሚቆጠሩ አይነት ናቸው፡፡ ለምሳሌ እኔ‘ጋ ካሉትና ልብ ብዬ ሳያቸው ከሚያስቁኝ መፅሐፍት አንዱን ልጥቀስ - “The Complete IDIOT’s Guide” (የተሟላ የደደቦች መመሪያ) የሚል ርእስ አለው፡፡ ይሄን መፅሐፍ አንድ የቅርብ ሰው በስጦታ መልክ ካቀረበልዎ አንድም እርስዎ፣ አለበለዚያም እርሱ (ከሁለት አንዳችሁ) ደደቦች ናችሁ፡፡ ‘እንዴት?‘ ያሰኛል፡፡ ‘እንዲህ‘ ነው፡፡
ሰውየው ይሄን መፅሐፍ የሰጥዎ ሆን ብሎ ከሆነ ድድብናዎን ወይም ጅልነትዎን አለያም ፉዞነትዎን አይቶ ያዘነልዎ፣ ወይም ቀርቦ የተማረረብዎ፣ ካልሆነም ተመራምሮ የደረሰብዎ ሰው ነው ማለት ነው፡፡ ፍቺ በሌለው መንገድ፣ ያለምክንያት፣ በእንዝህላልነት ይሄን መፅሐፍ ገዝቶ ከሰጥዎ ደግሞ ሰውየው እራሱ ደደብ፣ ወይም ጅል አለበለዚያም ፉዞ ነው ማለት ነው፡፡
ይሄ መፅሐፍ የተበረከተበት አግባብ እንዴት ነው? ብሎ ማጤን ደግሞ ደግ ነው፡፡ መፅሐፉ እቤትዎ ድረስ ወይም ብቻዎን ሳሉ ተሸፋፍኖ ከተሰጥዎ “ምክር” ነው፡፡ በአደባባይ ተገላልጦ ከተበረከተልዎ ደግሞ “ስድብ” ነው፡፡ እንዴት? ቢሉ ይሄንን ነባር ምሳሌ ያጤናሉ፡፡ “ለብቻዬ የሰደበኝ - መከረኝ፤ በሰው መካከል የመከረኝ - ሰደበኝ”
“The Complete IDIOT’s Guide” ሦስተኛው እትም (2003 ዓ.ም) እኔ‘ጋ አለ፡፡ ይሄ መፅሐፍ ከያዛቸው ርእሰ ጉዳዮች መካከል እኔ “ደደብ” የሆንኩበትን የቤት አያያዝ መርጬ በማስቀደም አነበብኩ፡፡ አከፋፋይ ቦታ ላይ ቆሞ በመምከር ይጀምራል፡፡ ቤትዎ ጭንቅላትዎ ውስጥ እንዳለው ህልምዎ አድርገው ማደራጀትና መሰደር ከቻሉ፣ ከዚህ ምስቅልቅል አለም የሚሸሹበትን ብቸኛ ቦታ በድል አድራጊነት መመሥረት ችለዋል ይላል፡፡ ጐጆ‘ኮ “ከራስ በላይ ኮርኒስ” ተብሎ የሚጠቃለል ጉዳይ አይደለም፡፡ (Your home doesn’t have to mean just a roof over your head) ይልና ስለቤት አያያዝ ወሳኝነት ይመክራል። ምክሩን አንብቤ እንዲህ እደመድማለሁ፡፡
ያልተደራጀና የተመሰቃቀለ ቤት እንቅፋት እንደበዛበት የባህር ቀዘፋ እንግልት የሞላበት መንፈስ ፈጥሮ ይደክማል፡፡ ሰው በጠዋቱ ከቤቱ ሲወጣ ከደከመው ፉክክር በበዛበት ዓለም ውስጥ ምኑን ተወዳደረው? በአግባቡ የተያዘ መኖሪያ ግን ለልዩ ተልእኮ ማዕከል እንደሚያደርጉት ወታደራዊ ቤዝ ነው…
….ወደ እኔ እውነታ ስመጣ ግን እንደዚያ አይደለም፡፡ ቤቴ በሰዎች “ሥርዓት” ሲይዝ ይዞርብኛል፡፡ ከምስቅልቅሎሹ ጋር ተግባቦት አለኝ። ስላልተሰደረ ደክሞኝ ከቤቴ አልወጣም፣ ቤቴን አልጠላም፣ የፈለኩትን ከቤቴ አላጣም፣ መንፈሴ በቤቴ ላይ አይጐሽም… ለመሆኑ “ከ’Idiot’ እነቴ” ጋር ተስማምቼ ኖርኩ? ወይስ Idiot አይደለሁም? ደግሞስ ምስቅልቅሎሹ ካልተሰማኝና ካልረበሸኝ መፅሐፉ ለምን አስፈለገኝ? እንዴትስ አብሮኝ ለአመታት ቆየ?... እያልኩ ልብ ብዬ ሳየው ከሚያስቀኝ መፅሐፍ ጋር አለሁ፡፡
እኔ ጋ ካሉትና ልብ ብዬ ሳያቸው ከሚያስቁኝ መፅሐፍት ሌላኛው “Bathroom Reader” (ለመታጠቢያ ቤት አንባቢ) የሚል ጠቅላይ ርእስ ያለው ነው፡፡ በ“Bathroom Reader” ኢንስቲትዩት እየተዘጋጀ የሚቀርብ ተከታታይነት ያለው መፅሐፍ ነው፡፡ ለትህትና መታጠቢያ ቤት ይባል እንጂ አላማው መፀዳጃ ቤት ነው፡፡ ሽፋኑ ላይ የመፀዳጃ ቤት ወረቀት፣ የመፀዳጃ ቤት ውሃ መልቀቂያ ይታያል፡፡ ከመፀዳጃ ቤት ወረቀቱ ጋር መፅሐፉ ቦታ ተጋርቷል፡፡ የመፅሐፉ አላማ በመፀዳጃ ቤት ቆይታ ወቅት የተመጠነ እውቀት ማስተላለፍ እንደሆነ ከርዕሱ እና ከሽፋን ምስሉ እንረዳለን፡፡ የፅሁፎቹ መጠን እንደ መፀዳጃ ቤት ቆይታችን እንድንመርጣቸው ሆነው የተዘጋጁ ናቸው፡፡ አጭር (Short)፣ መካከለኛ (Medium)፣ ረጅም (Long) እና ሰፋ ያለ (Extended) በሚል ተከፋፍለዋል፡፡ ይሄን መፅሐፍ ልብ ብዬ ባየሁ ቁጥር አንድ ቀልድ ትዝ ይለኛል፡፡
መፀዳጃ ቤቱ የጋራ የሆነበት መንደር ውስጥ ነው፡፡ ልጁ ገብቶ ብዙ የቆየባቸው ተጠቃሚዎች እየተነጫነጩ ነው፡፡ ከመካከላቸው አንዱ አዛውንት ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ልጁን ያናግሩታል፤
“ሰማህ አንተ ልጅ”
“አቤት”
“ሽንት ቤቱን ብቻህን ያዝከው‘ኮ፡፡ እኛም መጠቀም እንፈልጋለን፣ ለምን አትወጣም?”
ልጁ ውስጥ እንዳለ ይመልሳል፡-
“ቢወጣስ የት ይኬዳል?”
እኛ ከምናውቀው የጋራ መፀዳጃ ሽታ በላይ የከረፋ የሥራ አጥነት አለም ልጁን ይጠብቀዋልና ተደበቀበት፡፡ ቀልድ ይመስላል እንጂ መራር እውነት ነው፡፡
…እና (በእኛ ዓይን) የቀበጡቱ ፈረንጆች መፀዳጃ ቤት ተቀምጦ የሚባክን ጊዜን ሥራ ላይ ለማዋል “Bathroom Reader” አቀዱና ተገበሩ። መፅሐፉ ግን “መፅሐፍ” ነው፡፡ ታሪክ፣ አስቂኝ ገጠመኝ፣ ፖለቲካ፣ ሥነ-ፅሁፍ፣ ጥያቄና መልስ፣ ሥነ-ልቦና… ያልያዘው ነገር የለም፡፡ ያለ መፅሐፉ አላማ መኖሪያ ቤት ውስጥ እያነበብኩት ነው፡፡ እንኳን መፀዳጃችን ከተማችን እንደ ጋራ ሽንት ቤት በከረፋችበት አግባብ ሌላ ምን አማራጭ አለ?
ሦስተኛው ሳየው የሚያስቀኝ መፅሐፍ “100 MISTAKES THAT CHANGED HISTORY” (ታሪክ የቀየሩ መቶ ስህተቶች) የሚል ርእስ አለው። መግቢያው እንኳን “History Making Mistake” (ታሪክ ሰሪው ስህተት) የሚል ንዑስ ርዕስ ተሰጥቶታል፡፡ ታዲያ እኛ ምን ሆነን ነው “ታሪክ ሰሪው ሰፊው ህዝብ ነው” እያልን የከረምነው? ከዚህ መፅሐፍ አንፃር “ቆራጡ” (ምናምን) የሚባል መሪ የለም፡፡ ወይም ይቺ አለም እዚህ የደረሰችው በታቀደላት ቀጥተኛ መንገድ ተጉዛ ሳይሆን መሪዎችና ሌሎች ተሳስተው በፈጠሩት ክስተት ነው፡፡ ስለዚህ “Your Kingdom, or your life is a mistake” ይላል መፅሐፉ፡፡ ይሄንንም ለማስረገጥ መቶ ስህተቶች እንዴት የዓለምን ታሪክና ገፅታ እንደቀየሩት ያስነብባል፡፡
2500 ዓመታት ወደኋላ ተጉዞ የአይኦኒያን ከተማ ከሆነችው ከሚሊተስ (Miletus) መሪ አሪስታጐራስ (Aristagoras) ስህተት ይጀምራል። የአሪስታጐራስ ስህተት ምዕራብ አውሮፓ አሁን ባለችበት ሁኔታ እንድትገኝ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ አሪስታጐራስ የፐርሺያውን ንጉስ ቀዳማዊ ዳሪየስ አስደስቶ ለመሾም ለመሸለም ሲል ያመፀችውን የናክሶስ ከተማ ለመውረር ተነሳ፡፡ ድል ሳይቀናው ቀርቶ ተሸነፈ፡፡ ለመሸነፉ ከባቢሎን ንጉስ የሚደርስበትን ቅጣት ያውቃልና የአካባቢውን ከተሞች በባህል ስም ለአመፅ አስተባበረ፡፡ “ቋንቋችንና ባህላችን ለግሪክ እንጂ ለፔርሺያ ባእድ ነው፡፡ ስለዚህ ባቢሎናውያንን አንቀበልም” አለ። የአቴንስንና የመላው ግሪኮችን ድጋፍ አግኝቶ ቢዋጋም ከፔርሺያዎች ሽንፈት አላመለጠም፡፡ በዚህ ስህተት አውሮፓ ከግሪክ ግለሰብን ማዕከል ካደረገ ባህል ባሻገር ጠንካራ ማዕከላዊነት ያለውን የፔርሺያ ባህል ለማካተት ተገደደች፡፡ በዚህም አሁን ያለችውን ሆነች፡፡
ይሄ የመፅሐፉ ጅማሬ እስከ 2008 ዓ.ም የአውሮፓ የኢኮኖሚ ድቀት ድረስ ይጓዛል፡፡ እና ብዙ የፖለቲካ፣ የሳይንስ፣ የማህበራዊ ህይወት ስህተቶች የቀየሩትን ታሪክ ያሳየናል፡፡ እንዲህ ያለው ምርምር ከታሪክ ጋር በባላንጣነት ከመኖርና እሱኑ ከማመንዠግ አይገላግልም ትላላችሁ፡፡
አራተኛውን ልብ ብዬ ሳየው የሚያስቀኝን ያገኘሁት ከወደ ሩሲያ ነው፡፡ ሊያኪሚንኮ (LYAKIMENKO) የተሰኘ የሥነ ፅሁፍ ተመራማሪ፣ ሾሎሆቭ (Sholokhov) የተሰኘ ደራሲ ሥራዎች ላይ ጥናት ያካሄደበት መፅሐፍ ነው፡፡ ርእሱ “Sholokhov፡ A Critical Appreciation” (ቮሎሆቭ፡ የማድነቅ ሂስ) ይሰኛል፡፡ ማድነቅ ብቻ ከሆነ ምኑን ሂስ ሆነ? ስህተት ፈልጐ ማጣት አንድ ነገር ነው፤ ስህተትን ወዲያ ብሎ ማድነቅን ብቻ በማነፍነፍ እንዴት ሂስ ይሰራል? እያልኩ መፅሐፉን ሳየው ያስቀኛል፡፡
ሌላኛው መፅሐፍ የማርክ ክሪክ ነው፡፡ “The Household Tips of the Great Writers” ይሰኛል፡፡ መፅሐፉ በቤት አያያዝና በአትክልት ቦታ እንክብካቤ ውስጥ አጣማጅ አድርጐ ያላነሳቸው ደራሲዎች የሉም፡፡ ፍራንዝ ካፍካ፣ ጄን ሀውስቲን፣ ማርሲል ፕሩስት፣ ኤርነስት ሔሚንግዌይ፣ ቬርጂንያ ዎልፍ፣ ቶማስማን፣ ሆሜር፣ ቻርልስ ዲከንስ፣ ሐሮልድ ፒንተር፣ ጆን ስቴንቤክ፣ ሚለን ኩንዴራ፣ ኤሚል ዞላ፣ ዤን ፖውል ሳርት፣ ኤድጋር አለን ፖ… የሚገርመው ግን አንዱም የሉም፡፡ ደራሲው በፀሐፊዎቹ ስታይልና የሥነ ፅሁፍ አይነት የቤት አያያዙን፣ የመታጠቢያ ቤት እንክብካቤውንና የአትክልት ስፍራ አያያዙን ፅፎ አቅርቧል፡፡ አሁን ይሄ ማታለል ነው ወይስ…?
እንዲህ ያሉ “ግራ” ሥራዎችን ወደፊት እየመላለስን እንዳመቸን እንመለከታለን፡፡ 

Read 3182 times