Saturday, 25 April 2015 10:54

አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ የዜድቲኢ አምባሳደር ሆነ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

    ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ የዜድቲኢ (ZTE) ኩባንያ የስማርት ሞባይል ስልኮች አምባሳደር ሆነ፡፡ አትሌቱ ባለፈው ረቡዕ በሸራተን አዲስ በተከናወነ ስነስርአት ዜድቲኢ ለኢትዮጵያ ገበያ ሊያቀርባቸው ላቀዳቸው የስማርት ሞባይል ስልኮች አምባሳደር መሆኑ በይፋ ታውቋል፡፡ በስነ ስርዓቱ ላይ የተገኘው አትሌቱ፤ ከዜድቲኢ ጋር በፈፀመው ውል ምን ያህል እንደተከፈለው ባይገልፅም በዚህ መልኩ መስራቱ እንዳስደሰተው ተናግሯል፡፡
የቻይናው ዜድቲኢ ኩባንያ የዘመኑን የ4G ቴክኖሎጂ የታጠቁ ስማርት ስልኮችን በቅርቡ ለሃገር ውስጥ ገበያ ማቅረብ እንደሚጀምር በሸራተን በተካሄደው ምርቶቹን የማስተዋወቅ ስራ ላይ የተገለፀ ሲሆን ኩባንያው በቅርቡ በኢትዮጵያ የሞባይል መገጣጠሚያ ፋብሪካ እንደሚያቋቁም የኩባንያው ኃላፊዎች ተናግረዋል፡
ለብዙ ኢትዮጵያውያን የሥራ እድል ይፈጥራል የተባለው የሞባይል መገጣጠሚያ ፋብሪካው፤ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተገንብቶ ወደ ስራ እንደሚገባ የኩባንያው የአፍሪካ ቢዝነስ ተርሚናል ምክትል ፕሬዚዳንት ሚስተር ዲንግ ሃዎ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡ ኩባንያው በመላው ዓለም በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ የምርቱ ተጠቃሚ ደንበኞች እንዳሉት የጠቆሙት የኩባንያው ኃላፊዎች፤ ኩባንያው የስማርት ስልክ ምርቶቹን ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ኢትዮ ቴሌኮም የ4G አገልግሎት በተጀመረበት ወቅት በመሆኑ ትክክለኛ ጊዜ ነው ብለዋል፡፡
የስማርት ስልኮቹ ለኢትዮጵያ ገበያ በተመጣጣኝ ዋጋ ቀርበዋል ያሉት የኩባንያው የምስራቅ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሚስተር ጂያ ቼን፤ ስልኮቹ የአውሮፓ እና የአሜሪካ ስታንዳርድ ያላቸው ናቸው ብለዋል፡፡ የዜድቲኢ ምርቶችን ለማከፋፈልም ህዳሴ ቴሌኮም ከኩባንያው ጋር ስምምነት እንደፈፀመ ታውቋል፡፡
ዜድቲኢ በ2014 እ.ኤ.አ በአለማቀፍ ደረጃ ከ37 የ4G ቴክኖሎጂ አቅራቢ ኩባንያዎች አንዱ የነበረ ሲሆን የገቢ ድርሻውም 24.8 በመቶ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ በዚሁ የፈረንጆች ዓመት 100 ሚሊዮን የሚባይል ቀፎዎችን ለገበያ ያቀረበ ሲሆን 48 ሚሊዮን የሚሆኑት የስማርት ቀፎዎች ናቸው ተብሏል፡፡ በ2015 እ.ኤ.አ 60 ሚሊዮን የስማርት ቀፎዎችን ለዓለም ገበያ እንደሚያቀርብም የኩባንያው አመራሮች ተናግረዋል፡፡

Read 1971 times