Saturday, 25 April 2015 10:52

ንግድና ኢኮኖሚ 10 ምርጥ የአፍሪካ አዳዲስ ቴክኖሎጂ አፍላቂ ኩባንያዎች

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

    አፍሪካ የራሷ ብቻ በሆኑ ችግሮች የተተበተበች አህጉር ናት፡፡ በተለይ የገጠር አፍሪካዊ ሕይወት በተለያዩ ችግሮች የተወሳሰበ ነው፡፡ የተለያዩ ኩባንያዎች ለእነዚህ ችግሮች መፍትሔ ይሆናል ባሉት የፈጠራ ውጤት የገጠር ነዋሪውን ሕይወት ቀላልና ምቹ ለማድረግ እየጣሩ ነው፡፡ ቀጥሎ 10ሩን ምርጥ ችግር ፈቺ የተባሉ የፈጠራ ውጤቶች እንቃኛለን፡፡
አይ ሃብ (I Hab):- የአፍሪካን ማኅበረሰቦች በቴክኖሎጂ ለማገናኘትና ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማድረስ የሚሰራ ለትርፍ ያልተቋቋመ ግብረ ሰናይ ኩባንያ ነው፡፡
ኤሪክ ሄርስማን አይ ሃብ (I Hab) ለኬንያ ማኅበረሰብ በጣም ጠቃሚ የቴክኖሎጂ ምንጭ ሆኗል፡፡ ይህ ሁለት ነገሮችን በማዋሃድ የሚሰራው ግብረሰናይ ድርጅት፤ ከዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ጋር ተቀናጅቶ የሚሰራ ሲሆን በሶስት ዓመት ብቻ ከ10 ሺህ በላይ አባላት አፍርቷል፡፡ ድርጅቱ 150 ኩባንያዎች እንዲቋቋሙ ያደረገ ሲሆን አብዛኞቹ ድርጅቶች በተለይ የአፍሪካ ብቻ በሆኑ ችግሮች ላይ በማነጣጠር የቴክኖሎጂ መፍትሔ በመፍጠር ያተኮሩ ናቸው፡፡  
ሰነርጂ (Sanergy):- ከሰሐራ በታች ላሉ የአፍሪካ አገሮች ቋሚ የጤና ሽፋን ለማምጣት የሚሰራ ድርጅት ነው፡፡
የሰነርጂ ቋሚ ሞዴል ምስጋና ይግባውና ሽንት ቤት በሌላቸው፣ ቆሻሻና ብዙ ሰዎች በሚኖሩባቸው የኬንያ ሰፈሮች ከ12ሺህ በላይ ነዋሪዎች በየቀኑ የመፀዳጃ ቤት ወረቀትና ደቃቅ ሰጋቱራ፣ ሳሙናና ውሃ እንዲሁም ተንቀሳቃሽ መፀዳጃ ቤት እያገኙ ነው፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎች በጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት በመደራጀት፣ ተንቀሳቃሹን መፀዳጃ ቤትና መገልገያዎቹን ገዝተው ይጠቀሙባቸዋል፡፡ ሰገራው በየቀኑ እየተሰበሰበ መንግሥት ባወጣው የጥራት ደረጃ የተለያዩ ኬሚካሎች ተጨምሮበት ወደ ሚጣራበት ማዕከል ይወሰድና ማዳበሪያ ይሆናል፡፡ ማዳበሪያውን ከፍተኛ ዋጋ ከፍለው በፋብሪካ የተመረተውን ማዳበሪያ መግዛት የማይችሉ የምስራቅ አፍሪካ ገበሬዎች ገዝተው ይጠቀሙበታል፡፡  
ዋን ኤከር ፈንድ (One Acre Fund)፡- የአዲሱን ትውልድ የአፍሪካ ገበሬዎች ለመደገፍ የተቋቋመ ነው፡፡ ይህ ዘዴ፣ ሞዴሉ ቀላል፣ ጥቅሙ ግን ግዙፍ ነው፡፡ በጥቂት ዓመት ብቻ የአፍሪካ አነስተኛ ገበሬዎች ትልቁ ኔትዎርክ ከግማሽ ሄክታር በታች እንደሚሆን ዋን ኤከር ፈንድ ገምቷል፡፡
ኩባንያው ለገበሬዎቹ ዘርና ማዳበሪያ በዱቤ ይሰጣል፡፡ ምርታቸውን የሚሰበስቡበት መሳሪያዎችና የሚጭኑበት መኪና ያቀርባል፣ በመሳሪያዎች እንዴት እንደሚጠቀሙ ያሰለጥናል፤ እንዲሁም ምርታቸውን ለመሸጥ ይረዳቸዋል፡፡ ዋን ኤከር ፈንድ ከ10 ዓመት በፊት በ2006 በኬንያ ከተመሰረተ ወዲህ ወደ አጎራባች አገሮች ዩጋንዳ፣ ታንዛንያና ብሩንዲ በመዛመት 180ሺህ አባል ገበሬዎች ሲኖሩት ይህን ቁጥር በ2014 ዓ.ም መጨረሻ 200ሺህ ለማድረስ አቅዷል፡፡
ሮኬት ኢንተርኔት (Rocket Internet)፡- ዓላማው የአሜሪካ ዓይነት ንግድ በአፍሪካ ማቋቋም ነው፡፡ በአሜሪካ፣ አውሮፓ፣ በእስያ… የተለመዱ ዘመናዊ የኢንተርኔት ግብይቶችን በአፍሪካ ማስተዋወቅ ነው፡፡ በአፍሪካ ሥራ ከጀመረ ከ2007 ወዲህ ከ100 በላይ ኩባንያዎች አቋቁሟል፡፡ በፉድ ፓንዳ በኢንተርኔት ምግብ ማቅረብ፣ በላማንዲ (Lamundi) ሪል ኢስቴት፣ በጃርጎ (Jarogo) ሆቴል መያዝ፣ እንዲሁም በጁሚያ (Jumia) በመጠቀም በአህጉሩ ተወዳጅና ተዋቂ ከሆነው የኢንተርኔት መረብ ከአማዞን ሊንክ ጋር ግንኙነት በመፍጠር መገበያየት የሮኬት ኢንተርኔት ያስገኘው ውጤት ነው፡፡
ኩባንያው ጀርመን - በርሊን ከሚገኘው ዋና መ/ቤቱ የሚመራው ቢዝነስ አብዛኛው ተመሳሳይ ነው፡፡ በአፍሪካ አዲስ የቢዝነስ አሰራርና አመራር ለማምጣት የሚያደርገው እንቅስቃሴ ለአህጉሩ ዕድገት ወሳኝ ነው፡፡
ኮንጋ (Konga):- የኢንተርኔት ሸመታን ደህንነት የበለጠ አስተማማኝ ለማድረግ የሚሠራ ነው። ኩባንያው በቅርቡ ባስተዋወቀው የገበያ ስፍራ፣ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች፣ ‹አልባሳት፣ የቤት ዕቃዎች፣ … በአጠቃላይ ከ200 ሺህ በላይ ምርቶች ያለ ስጋት በኢንተርኔት መግዛት ያስችላል፡፡ የዕቃዎቹ ሻጮች ደግሞ ከናይጄሪያ ትናንሽ የመንደር ነጋዴዎች አንስቶ ትላልቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችን ያጠቃልላል፡፡
የገዢዎችንና የሻጮችን ደህንነት በተመለከተ፣ ናይጄሪያውያን ብሮድባንድ ኢንተርኔት መጠቀማቸውን እስቀጠሉ ድረስ በኢንተርኔት መገበያየት እንደሚጀምሩ ኮንጋ እምነቱ መሆኑን ገልጿል፡፡
ስቴሪዮ ዶት ሚ (Sterio.me):- መሰረተ ልማትን ከትምህርት ውስጥ ማውጣት ወይም መንገድ፣ ትራንስፖርት፣ የትምህርት ተቋም፡… ሳይኖር በኢንተርኔት ማስተማር ነው ዓላማው።
ይህ በጅምር ላይ ያለ ተቋም ለሙከራ፣ በሞባይል ኢንተርኔት ለማስተማር (ኢ-ለርንግ) በናይጄሪያ 75 ት/ቤቶች ተመዝግበው እየተማሩ ያሉ ልጆችን ከት/ቤት አስወጥቶ ትምህርቱን የሚሰጠው በኤስኤምኤስ (SMS) መልዕክት ነው፡፡ ከክፍል ውጭ ሆነው ለመማር ለተመዘገቡት የትምህርት መጻህፍትና ደጋፊ ጽሑፎችን በሞባይል እንዲያገኙ ያደርጋል፡፡
ትምህርቶቹ ቀደም ብለው በአስተማሪዎቹ የተቀረፁ ስለሆነ ተማሪው እንደ ነፃ ድምፅ ጥሪ (Free Voice Call) በልዩ የኤስኤምኤስ መልዕክት ይልካል፡፡ አስተማሪዎቹ ወዲያውኑ የትኛው ተማሪ ትምህርቱን ጨርሶ እንደላከና እንዴት እንዳዘጋጁት ይረዳሉ፡፡ ይህም ለማረሚያና ቀጣዩን ትምህርት ለማዘጋጀት ጊዜ ይሰጣቸዋል፡፡
አፕ ኢነርጂ (UP energy)፡- በገጠሪቷ አፍሪካ ያለሥጋት ምግብ ለማዘጋጀት ይረዳል፡፡
በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ በገጠሪቷ ዩጋንዳ የሚኖሩ ሰዎች እስካሁንም ድረስ በሶስት ጉልቻና ናፍጣ ብቃት በሌለውና ለጤና አደገኛ በሆነ ዘዴ ምግብ እያዘጋጁ ነው፡፡ አፕ ኢነርጂ ሰዎቹንም ሆነ አካባቢውን የማይጎዳ ዘዴ አዘጋጅቷል፡፡
ድርጅቱ ለትላልቅ ቢዝነሶች የካርቦን ዱቤ ድጋፍ የሚያገኝበትን መንገድ ያመቻቻል፡- ለአካባቢው ቸርቻሪዎች ደግሞ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ አረንጓዴና ብቃቱ የበለጠ የተረጋገጠ የማብሰያ ምድጃ፣ የውሃ ማጣሪያ ቴክኖሎጂና የፀሐይ ብርሃን በማቅረብ በቀጥታ እንዲገዙ ድጋፍ ያደርጋል፣ ስለአጠቃቀሙ መመሪያም ይሰጣል፡፡
ዳፕቲዮ (Daptio):- አዲሱን ትምህርት የመቀበል ዘዴ ተመራጭ ማድረግ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የኢንተርኔት ቀጥታ ትምህርት የበለጠ እየተለመደ ስለሆነ ቀጣዩ እርምጃ፣ የተለመደውን የሌክቸር የትምህርት አሰጣጥ ዘዴ ተመራጭና ተቀባይነት ባለው የማስተማር ዘዴ (Adaptive Learning) መተካት ነው፡፡
የዚህ ትምህርት ዘዴ ግብ፣ ተማሪዎች፣ የሚማሩትን ትምህርት በከፍተኛ ደረጃ የሚረዱበትንና የተሻለ ውጤት የሚያገኙበትን ትክክለኛ የትምህርት ማውጫና ትክክለኛ ጊዜ የሚያገኙበትን ሞዴል መቅረፅ ነው፡፡
አፍሪካ ወደፊት የኢንተርኔት ሞባይል ትምህርት የሚስፋፋባት አህጉር ናት፡፡ ስለዚህ በቀጣይ 5 ዓመታት በአፍሪካ የሞባይል ትምህርት 39 በመቶ ሲያድግ ከኢንተርኔት የሞባይል ትምህርት የሚገኘው ገቢም በ2017 ወደ 530 ሚሊዮን ዶላር ያድጋል፡፡ የዳፕቲዮ አስፈላጊነት ይህን እውነታ ማረጋገጥ ነው፡፡
ፕሪፕ ክላስ (Prep)፡- ቀጣዩን ትውልድ ለማጀት ፕሪፕ ክላስ፣ የናይጄሪያ ተማሪዎች ደረጃውን ለጠበቀ ፈተና የሚያዘጋጅ ተንቀሳቃሽ የኢንተርኔት ድርጅት ነው፡ ተማሪዎቹ ለኢንተርኔት ወይም ለወረቀት ፈተና ለመዘጋጃ ልምምድ ይከፍሉና ለፈተናው ቀን ማሻሻል ያለባቸው ነገር ይነገራቸዋል፡፡ ይህን የኢንተርኔት ትምህርት በቀላሉ ማግኘት እንዲቻል ፕሪፕ ክላስ በናይጄሪ ከ1000 በላይ ከሆኑ ሳይበር ካፌዎች ጋር እየሰራ ነው፡፡  
አውዛ (Aweza):- የተበታተነ ኅብረተሰብ ለማገናኘት በደቡብ አፍሪካ ከ11 በላይ ቋንቋዎች አሉ፡፡ አውዛ በእነዚህ የተለያዩ ማህበረሰቦች ውስጥ ያለውን የቋንቋ ክፍተት ለማጥበብና የቋንቋ ልዩነቶችን ለመቀነስ የሚሰራ ድርጅት ነው፡፡ የአጠቃቀም መመሪያው ተጠቃሚዎች በትናንሽ ፓኬጆች ያሉ ቃላት ወይም ሐረጎችን ወደሌላ ቋንቋ መተርጎም የሚያስችሉ ናቸው፡፡
 

Read 2871 times