Saturday, 25 April 2015 10:46

የፖለቲካ ጥግ

Written by 
Rate this item
(9 votes)

በመንግሥት በጀት ትዳራቸውን የሚያስተዳድሩ ፕሬዚዳንቶች
በየዓመቱ አንድ ድንግል የሚያገባው መሪ

ምስዋቲ
የስዋዚላንዱ ንጉስ ምስዋቲ አስገራሚ ባህላዊ መሪ ናቸው - እንግሊዝ የተማሩ! በጐሳቸው ባህል መሰረት ብዙ ሚስቶችን ማግባት ይችላሉ (እችላለሁ ስላሉ ነው!) ለዚህም ነው 14 ሚስቶች አግብተው 24 ልጆችን ያፈሩት፡፡ ይሄ ብቻ ግን አይደለም፡፡ (ቢሆንማ በማን እድላችን!) በየዓመቱ በሚካሄደው የደናግል ኮረዶች ዳንስ፣ ንጉሡ አንድ ድንግል መርጠው ያገባሉ፡፡ ሚስቶቻቸው በ14 የተንደላቀቁ ቤተመንግስቶች ውስጥ የሚኖሩ ሲሆን እነሱን ለማስተዳደርም ከድሃዋ አገራቸው ዓመታዊ በጀት ላይ 31.7 ሚ. ፓውንድ ይወስዳሉ (ትዳር በመንግስት በጀት ይመቻል!)
ሁሉም ሚስቶቻቸው ደስተኛ ናቸው ለማለት ያዳግታል፡፡ (የንጉስ ወህኒ ቤት እኮ ነው!) ለምሳሌ ሦስቱ ሚስቶቻቸው (ለስሙ ንግስቶች ናቸው!) አካላዊና ስነልቦናዊ ጥቃት ደርሶብናል በማለት የንጉሱን ቤተመንግስት ጥለው ወጥተዋል፡፡ ለንጉስ ምስዋቲ በዓመት አንዴ የሚካሄደው የኮረዶች ባህላዊ የዳንስ ትርኢት ሁሌም በጉጉት የሚጠበቅ ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ2012 ዓ.ም 80ሺ ደናግል ኮረዶች (እርቃነ-ጡታቸውን) ሆነው ለስዋዚላንዱ ንጉስ የዳንስ ትርኢት አሳይተዋል - በስቴዲየም። በዚህ ትርኢት ንጉሱ ይዝናናሉ፡፡ አንድ ድንግል መርጠውም ያገባሉ፡፡ አንዳንዶቹን ልጃገረዶች ደግሞ አልፎ አልፎ ለመቅበጥ ይፈልጓቸዋል፡፡
በንጉሡ ተመርጣ ሚስት የሆነች ኮረዳ ወዲያውኑ አንድ ቤተመንግስትና BMW አውቶሞቢል ይበረከትላታል፡፡ ለአንዲት ምስኪን የገጠር ኮረዳ ይሄ ምን ማለት እንደሆነ አስቡት! (ግን ድንግልናዋን ብቻ ሳይሆን ነፃነቷንም ተነጥቃ ነው!) ያለንጉሱ ፈቃድ የትም ንቅንቅ አትልም፡፡ (እስር በሉት!) በዓመት አንዴ ግን ሁሉም ሚስቶቹ አሜሪካ ሄደው እቃ እንዲሸምቱ ንጉሱ ገንዘብ ይሰጧቸዋል፡፡ በነገራችን ላይ አባታቸው ንጉስ ሶብሁዛ (ሁለተኛው) 70 ሚስቶች ነበሯቸው፤ 400 ልጆችም ወልደዋል፡፡ (የዘር ነዋ!)
ንጉስ ምስዋቲ የመጨረሻ ሚስታቸውን ያገቧት በ19 ዓመቷ ሲሆን በዳንስ ትርኢቱ ላይ ነው የመረጧት፡፡ ንጉሱ የሚያስተዳድሯት ስዋዚላንድ በጣም ትንሽ አገር ስትሆን የህዝቧ ቁር 2 ሚሊዮን እንኳን አይሞላም፡፡ 70 በመቶ ህዝቧ ግን ከድህነት ወለል በታች ነው የሚኖረው፡፡ የአፍሪካ የመጨረሻው ንጉስ ናቸው የሚባሉት ምስዋቲ ደግሞ የጠገቡ ሃብታም ናቸው - የ200 ሚ. ዶላር ጌታ! በአፍሪካ ቀዳሚ “ሴት አውል” ፕሬዚዳንት በሚል በአንደኝነት ተመርጠዋል፡፡
ጃኮብ ዙማ
ጃኮብ ዙማ የደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ካገለገሉ በኋላና የአገሪቱም ሆነ የአፍሪካ ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲ ፕሬዚዳንት ከመሆናቸው በፊት በአስገድዶ መድፈር ተከሰው ነበር፡፡ ዙማ ዘመናዊ መሪ (ድንቄም ዘመናዊ!) ቢመስሉም አራት ሚስቶች አሏቸው፡፡ ፕሬዚዳንት ጃኮብ እ.ኤ.አ በ2014 ዓ.ም “ውሃ አጣጪ” አምስተኛ ሚስታቸውን (ለእርጅና ዘመኔ ብለዋል!) ለማግባት ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመው ነበር፡፡ የ72 ዓመቱ ዙማ፤ (በደቡብ አፍሪካ በስንት ዓመት ነው አረጀሁ የሚባለው?) “ሚስቶች አሉኝ፤ ነገር ግን የመጨረሻይቱን በቅርቡ አገባለሁ” ብለዋል፡፡ (ለምን የመጨረሻ እንዳሉ አልገባኝም!!)
ለፕሬዚዳንቱ ቅርብ የሆኑ ሰዎች እንደመሰከሩት፤ ሰውየው ከሴት ሌላ ወሬ የላቸውም፡፡ 20 ገደማ ልጆች ያሏቸው ዙማ፤ ስድስት ጊዜ ያገቡ ሲሆን በእርግጥ አሁን በመንግስት በጀት የሚያስተዳድሯቸው አራት ሚስቶች ብቻ ናቸው ያሏቸው፡፡ (ሰውየው መደበኛ ትምህርት አልዘለቃቸውም ይባላል!) ጃኮብ አንድ ጊዜ በአስገድዶ መድፈርና በትዳር ላይ በመማገጥ ተከሰው ነበር - “አፍሪካ ክራድል” እንደዘገበው፡፡
ጋዳፊ
ሊቢያን ከ30 ዓመታት በላይ አንቀጥቅጠው የገዟት ኮሎኔል ሙአመር ጋዳፊ (መሬት ይቅለላቸውና!) ሁለት ሚስቶች ነበሯቸው - ሳፍያ ፋርካሽ እና ፋቲሃ አል-ኑሪ፡፡ ለብዙዎች የጋዳፊ ሞት የእሳቸው ዘመን ማብቃቱን ያረጋግጥላቸዋል። ለ5 ዓመት አስገድዶ ደፍሮኛል ለምትለው ሳፍያ ግን የኮሎኔሉ መንፈስ እድሜልኳን ሲያስበረግጋት ይኖራል፡፡ የፕሬዚዳንቱን በድን ምስል ባየችበት ወቅት የተደበላለቁ ስሜቶች እንደተሰማት ተናግራለች - ከደስታ እስከ ንዴት፡፡
እሷ ብቻ ግን አይደለችም የተደፈረችው፡፡ ጋዳፊ ሴት ጠባቂዎቻቸውንም (Body guards) አስገድደው ይደፍሩ ነበር፡፡ ይሄ ብቻ አይደለም። ይደበድቧቸውና በመድሃኒትም ያደነዝዟቸዋል፡፡ ከእኒሁ ሴት ጠባቂዎቻቸው ጋር በፕሬዚዳንታዊ መኖርያ ቤታቸው ውስጥ የቡድን ወሲብ ይፈፅሙ እንደነበርም “አፍሪካ ክራድል” ዘግቧል፡፡
ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት፤ ሌሎች ልጃገረዶችም የኮሎኔሉን “አፈንጋጭ የወሲብ ፍላጐቶች” ለማርካት የቦዲጋርዶቻቸውን ያህል ተሰቃይተዋል፡፡ የአፍሪካና የአውሮፓ በተለይ የጣልያንና ቤልጂየም ልዕለ ሞዴሎች ዘወትር እየተመለመሉ የፕሬዚዳንቱን ፍላጐት በቡድን ያረኩ ነበር ተብሏል፡፡
”ሴቶቹ ስራቸውን ሲያጠናቅቁም ቦርሳቸውን በገንዘብ አጭቀው ይወጣሉ፤ የወሲብ ባሪያ ላደረጓቸው የሊቢያ ሴቶች ግን ጨርሶ ገንዘብ ሰጥተዋቸው አያውቁም” ይላሉ - ምንጮች። በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች የተነሳ ጋዳፊ 3ኛው “ሴት አውል” (ሴሰኛ ይሻላል!) የአፍሪካ መሪ በሚል ተመርጠዋል፡፡ (ቤተመንግስቱን የዝሙት ቤተ አድርገው ነበር!)
ጆን ማሃማ
የጋናው ፕሬዚዳንት ጆን ማሃማ “ሴት አውል” አይደለሁም ሲሉ ያስተባብላሉ፡፡ ነገር ግን ከትዳራቸው ውጭ መቅበጣቸውን አይክዱም!!” ልካድ ቢሉም አይችሉም፡፡ በርካታ ከትዳር ውጭ የተወለዱ ልጆች አሏቸው፡፡
“እኔን ሴት አውል አድርጐ የማሰብ ሁኔታ አለ፤ ይሄ ፈፅሞ እውነት አይደለም፡፡ በእርግጥ ከትዳሬ ውጭ ልጆች ወልጄአለሁ፡፡ ይሄን በተመለከተም ከሚስቴ ጋር ሰላም ፈጥሬአለሁ፡፡ እሷ ነገሩ የተከሰተበትን ሁኔታ በደንብ ተረድታለች፡፡ እኔም ለልጆቼ ሃላፊነት የሚሰማው አባት ነኝ፡፡” ብለዋል - ፕሬዚዳንቱ፡፡
ማሃማ ከትዳር ውጭ የተወለዱት ልጆች ቁጥር “ሰባት” መሆናቸውን በይፋ ገልፀዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ከሌላ ያልታወቀች ሴት (እሳቸውማ ያውቋታል!) የወለዷቸው ልጆች እንዳሉም ይታወቃል፡፡ ከአሁኑ ባለቤታቸው ከሎርዲና ጋር ከመጋባታቸው በፊት የወለዱት አንድ ወንድ ልጅም አላቸው፡፡ ምንጮች እንደሚጠቁሙት ግን ማሃማ ቢያንስ 5 ከትዳር ውጭ ግንኙነቶች ሲኖራቸው የልጆቹ ቁጥርም ከሰባት በላይ ነው (20 እንኳን አልሞላም እኮ!) እነዚህ ሁሉ ታይተው ጆን ማሃማ 4ኛው “ሴት አውል” ኛ የአፍሪካ ፕሬዚዳንት ተብለዋል፡፡
ያህያ ጃሜህ
የጋምቢያው ፕሬዚዳንት ያህያ ጃሜህ ሦስት ሚስቶች አሏቸው - አሊማ ሳላህ፣ ዘይነብ ሱማ ጃሜህ እና ቱቲ ፋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ፤ የነፃ ትምህርት እድል አሸናፊ ከነበረችው ፋቶ ጃሮል - ጃሜህ ጋር በነበራቸው ግንኙነት አስረግዘዋት ነበር፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ግን ህፃኑ “ዳውን ሲንድሮም” (የአዕምሮ እድገት ዝግመት) እንዳለበት በምርመራ በመታወቁ ፅንሱን እንድታቋርጠው ተደረገ። በነገራችን ላይ የፕሬዚዳንቱ ሁለት ልጆችም በተመሳሳይ የጤና ችግር የተጠቁ ናቸው፡፡
ያህያ ጃሜህ የሰው ሚስት በመመንተፍ ይታማሉ፡፡ ከትዳራቸው ውጭም ልጆች ወልደዋል። እድሜ ለሃብታቸውና ለስልጣናቸው! ከወጣት ሴቶችና ኮረዳዎች ጋር እንዳሻቸው ይቀብጣሉ፡፡ ሰውየው በአፍሪካ 5ኛው “ሴት አውል” ፕሬዚዳንት ተብለው ተመርጠዋል፡፡
ወዳጆቼ፤ እንዳያችሁት የአንዳንድ የአፍሪካ መሪዎች ታሪክ በሴትና በወሲብ ገድል የተሞላ ነው። ስልጣን የሙጥኝ የሚሉት እኮ ወደው አይደለም፡፡ ለእነሱ ከኤደን ገነት እንደመባረር ነው - ከቤተ መንግስት መውጣት! ምስኪኑ የአፍሪካ ህዝብ ግን በድህነት ተቆራምዶ ኑሮውን ይገፋል፡፡ (“ወይ መዓልቲ!” አለ ትግሬ!)

Read 4954 times