Saturday, 25 April 2015 10:45

“መዋጮዬ ከማንም ያልበለጠ ቢሆንም መንገዱ በሥሜ ተጠርቷል”

Written by 
Rate this item
(5 votes)

    በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ሰዎች ሥም የሚጠሩ መንደሮችና መንገዶች ጥቂት የሚባሉ አይደሉም፡፡ “ወርቁ ሠፈር፣ የሺ ደበሌ ማዞሪያ፣ አባ ቦራ ቅያስ፣ ሞላ ማሩ አካባቢ፣ አባ ኮራን መንደር…” የሚባሉትን በማሳያነት ማንሳት      ይቻላል፡፡ የመንደርና የመንገዶቹ ስሞች በመንግስት የሚሰጡበት ጊዜ አለ፤ እንደ፣ “ቸርች ል ጎዳና”፡፡ በአካባቢው ታዋቂ ሥራ ከሚሰራ ተቋም ወይም ግለሰብ ጋር በተያያዘ ስያሜውን ያገኘ ይኖራል፤ እንደ “ባሻ ወልዴ ችሎት”፡፡ ህብረተሰቡም አብረውት ከሚኖሩት መሐል የተለየ አክብሮ ለለገሰው ሰው መጠሪያ እንዲሆን ዕውቅና የሚሰጠው አለ፤ እንደ “ዘውዴ ብራቱ መንገድ፡፡”
ከክፍለ ሀገር አውቶቢስ ተራ ወደ አብነት በሚያስኬደው አውራ ጎዳና ወደ አዲስ ከተማ መንደሮች ከሚያስገቡት ቅያሶች አንዱ በስማቸው የሚጠራው ቀኛዝማች ዘውዴ ብራቱ፤ መንገዱ እንዴት በስማቸው ሊጠራ እንደቻለ “የሕይወቴ ጉዞ” በሚል ርዕስ ካዘጋጁት የሕይወት ታሪክ  ጥቂቱን ለጋዜጣ በሚያመች መልኩ አሳጥረን አቅርበነዋል፡፡

  ወላጅ አባቴ ፊውራሪ ብራቱ ደጋጋ በተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች በተለያዩ ቦታዎች ህዝብና አገራቸውን አገልግለዋል፡፡ በማይጨው ጦርነት ተሳትፈዋል፡፡ የራስ አበበ አረጋይ ንብረት እንደራሴ ባለ አደራ ሆነው ነበር፡፡ ለራስ ሙሉጌታ ድረው በወንበርነት ሰርተዋል፡፡ “ወንበር” ማለት በፍርድ ቤት ወይም በአስተዳዳሪ ተሰይሞ የሚሰራ ሹመኛ ማለት ነው፡፡ በዚህ ሹመት በተለያዩ ክፍላጸ ሀገራት በመዘዋወር አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡ ከፍርድ ሚኒስቴር የጥብቅና ፈቃድ በመውሰድ በሙያው ሰርተዋል፡፡ በትውልድ መንደራቸው በአይመለል ክስታኔ ጉራጌ ዞን በግብርና ሥራ የተዳደሩበት ታሪክም አላቸው። እናቴ እመት ግምጃ ኢላላ የቤት እቤት ነበሩ፡፡ ወላጆቼ በትዳራቸው ካፈሯቸው ሸባጽ ልጆች እኔ ሦስተኛው ልጅ ነኝ፡፡
የተወለድኩት በአዲስ አበባ ከተማ፣ ሰባ ደረጃ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ፣ ከራስ መኮንን ከፍ ብሎ ከሚገኘው “አባታችን ሰፈር” ውስጥ ሲሆን ዕለቱ ሚያዚያ 23 ቀን 1920 ዓ.ም ነው፡፡ በአሁን ወቅት በ87 ዓመት ዕድሜ ላይ እገኛለሁ፡፡ የተወለድኩበት መንደር “አባታችን ሰፈር” የሚል መጠሪያ ያገኘው የጳጳሳት መኖሪያ አካባቢ በመሆኑ ነበር፡፡
ትውልዴ አዲስ አበባ ቢሆንም በአባቴ አገር ሚልኮ የቤተክህነት ትምህርት መከታተሉን በ7 ዓመቴ ጀምሬ በተለያዩ ደረጃዎች በማለፍ 12 ዓመት ሲሞላኝ በሚልኮ ጥንታዊት ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን በድቁና ማገልገል ጀመርኩ፡፡
ከድቁና አገልግሎቴ ጎን ለጎን ቤተሰቦቼን በስራ እረዳ ነበር፡፡ የ17 ዓመት ወጣት ሳለሁ ከዛሬዋ ባለቤቴ ከወ/ሮ ትክክልወርቅ ሞጆ ጋር ጥር 7 ቀን 1937 ዓ.ም ትዳር መሰረትኩ። ትዳራችን 70 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ አባቴ በሰጠኝ መሬት ላይ የራሴን ጎጆ ቀልሼ ትዳሬን ማስተዳደር ብችልም ተጨማሪ ትምህርትና ዕውቀት ማግኘት ስለምችልበት ሁኔታ ዘወትር በማሰብ እተጋ ነበር፡፡
በ1941 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሆኜ ዘመናዊ ትምሀርት እንድማር እንዲፈቅዱልኝ አባቴን በሽማግሌ ሳስጠይቃቸው፤ “ሚስቱን የት አድርጎ ነው የሚማረው?” ብለው ተቃውሞ አቅርበው ነበር፡፡ ባለቤቴ ወ/ሮ ትክክልወርቅ ሞጆ፤ አዲስ አበባ መጥታ መኖር ትፈልግ ስለነበር፣ የአባቴን ተቃውሞ ስትሰማ “ይማር እኔ እናቱ ጋ አገር ቤት እቀመጣለሁ” በማለቷ ትምህርት ቤት የመግባት ፍላጎቴ ተሳካ፡፡
በአዲስ አበባ ትምህርት የጀመርኩት በሊሴ ገብረ ማርያም ትምህርት ቤት ሲሆን በወር 5 ብር እከፍል ነበር፡፡ በዕድሜዬ፣ በቁመቴና በዕውቀቴ ተገምግሜ ሁለተኛ ክፍል በመመደብ ነበር ትምህርት የጀመርኩት፡፡ በቀኑ ክፍለ ጊዜ በሊሴ ገብረ ማርያም ፈረንሳይኛ እየተማርኩ፣ በማታው ክፍለ ጊዜ እንግሊዝኛ ቋንቋ ለመማር ካቴድራል ትምህርት ቤት ገባሁ፡፡ በቀጣዩ ዓመት ልዑል ወሰንሰገድ ትምህርት ቤት 3ኛ ክፍል በመግባት የዕውቀት ጥሜን ለማርካት ጥረቴን ቀጠልኩ፡፡ ከክፍል ወደ ክፍል በደብል እያለፍኩ በ1944 ዓ.ም 8ኛ ክፍል ደረስኩ፡፡
እኔ በአዲስ አበባ ሆኜ ትምህርቴን እንድከታተል ፈቃደኛ የሆነችው ባለቤቴ ወ/ሮ ትክክልወርቅ ሞጆን ማገዝ እንዳለብኝ ስለተሰማኝና አብረን መኖር እንዳለብን ስለወሰንኩ የአገር ግዛት ሚኒስቴር ባወጣው ማስታወቂያ ተወዳድሬ በስታቲስቲክ ክፍል ተቀጥሬ በወር 40 ብር እየተከፈለኝ መስራት ጀመርኩ፡፡ ከዚህ በኋላ ባለቤቴም አዲስ አበባ መጥታ አብረን መኖር ጀመርን፡፡
ከአገር ግዛት ሚኒስቴር በኋላ በቡታጅራ፣ በሱሉልታ፣ በአዲስ ኣለም፣ በአቃቂ በሰቃ፣ በሆለታ ገነትና መሰል ቦታዎች በመዘዋወር በተለያየ የኃላፊነት ቦታ እስከ 1957 ዓ.ም ድረስ ካገለገልኩ በኋላ በግል የጥብቅና ሙያ ለመሰማራት ስለወሰንኩ፤ እራሴን ከቅጥር ሥራ አሰናብቼ በ1958 ዓ.ም ከፍርድ ሚኒስቴር የጥብቅና ፈቃድ ወስጄ መስራት ጀመርኩ፡፡ በዚህ ዘርፍ ያለኝን ዕውቀት ለማሻሻልም ወደ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የህግ ፋኩልቲ በመግባት የህግ ትምህርት ተከታትዬ፣ ሐምሌ 8 ቀን 1961 ዓ.ም ከግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ እጅ በህግ ሰርተፍኬት ተቀብያለሁ፡፡
በ1962 ዓ.ም ፓርላማ መግባት የቻልኩት ምዕራብ አዲስ አበባን ወክዬ በመወዳደር በአንደኛ ደረጃ ማሸነፍ ስለቻልኩ ነበር፡፡ በውድድር ወቅት ለህብረተሰቡ ቃል በገባሁት መሰረት የህዝቡ ችግሮች ናቸው ያልኳቸውን ጉዳዮች በተደጋጋሚ ለፓርላማው አቅርቤያለሁ። ለምሳሌ በየጎዳናው ላይ ሱቅ በደረቴ የሚሰሩ ነጋዴዎች፤ ያለ አማራጭ የሥራ ቦታ በየዕለቱ እንዲባረሩ መደረጉ ስህተት መሆኑን ለፓርላማው አሳውቄ፣ ፓርላማውም አቤቱታውን ተቀብሎ መፍትሔ ይፈለግለት ብሎ አጽድቆታል፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ ዳቦ ሳይጠግብ በቁማር ሱስ እንዲጠመድ እየተደረገ ነው በማለት በአዲስ አበባ ከተማ የተስፋፋውን የቁማር ማጫወቻ ቤቶችና ማሽን ብዛት በማመልከት ለፓርላማው ያቀረብኩት አቤቱታም ምክር ቤቱ የጉዳዩን አስከፊነት ከተቸበት በኋላ የቁማር መጫወቻ ማሽኖች በ24 ሰዓት ውስጥ ከኢትዮጵያ እንዲወጣ ያሳለፈውን ውሳኔ የመወሰኛ ምክር ቤትም ተቀብሎ አጽድቆታል፡፡
በ1963 ዓ.ም ህዝቡን አስተባብሬ ኮሚቴ በማቋቋም ከአዲስ ከተማ ሰፈር እስከ አማኑኤል ቶታል እና ወደ ኮካኮላ የሚያስኬደው መንገድ ድረስ በማገኛኘት አስፓልት ሆኖ የተሰራ ሲሆን፡፡ የአዲስ አበባ ከንቲባ የነበሩት ዶ/ር ኃይለጊዮርጊስ ወርቅነህ እንዲመርቁልን አድርገናል፡፡ ህዝቡ በዚህ የመንገድ ስራ ወቅት አደርግ የነበረውን ጥረት አይቶ ወጪ ወራጁ ሁሉ “ዘውዴ ብራቱ መንገድ” ብሎ ሰይሞታል፡፡ መዋጮዬ ከማንም ያልበለጠ ቢሆንም፤ መንገዱ በስሜ ሲጠራ ስሰማ ደስ ይለኛል፡፡
የደርግ መንግስት በስልጣን ማብቂያው ዋዜማ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ጠርቶ በኢሰፓ አዳራሽ ሀገር አቀፍ ስብሰባ ባደረገበት ወቅት፤ ማን እንደጠቆመኝ ባላውቅም ምዕራብ አዲስ አበባን ወክዬ በኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ሰብሳቢነት በተካሄደው ጉባኤ ለአራት ቀናት ተሳትፌያለሁ፡፡
ኢህአዴግ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላም የሰላም እና መረጋጋት ኮሚቴ ሲቋቋም፣ የኮሚቴው ሊቀመንበር ሆኜ እንዳገለግል ህዝብ ስለመረጠኝ የተደረገልኝን ጥሪ ተቀብዬ በኃላፊነት የተሳተፍኩ ሲሆን ሰላምና መረጋጋት ሲረጋገጥ ወደ ተለመደው የሙያ ሥራዬ ተመልሻለሁ፡፡
በደቡብ ክልላዊ መንግሥት በጉራጌ ዞን ለሚገኘው የአይመለል ክስታኔ ህዝብ በልማት ዙሪያ የተለያዩ አስተዋጽኦዎች ለማድረግ ሞክሬያለሁ፡፡ የክስታኔ ጉራጌ ህዝብ የጎርዳና ሸንጎ ሊቀመንበር ሆኜ አገልግያለሁ፡፡ በመንገድ ሥራ፣ በጤና ጣቢያ ግንባታ፣ በአብያተ ክርስቲያናት ህንፃ ግንባታ፣ በትምህርት ቤት ማስፋፋት ሥራ ላደረግሁት አስተዋጽኦም ህዝቡ የቀኛዝማችነት ማዕረግ የሰጠኝ ሲሆን የልማት ስራዎቹን የረዱ የተለያዩ ተቋማትም የምስጋና የምስክር ወረቀት ሰጥተውኛል፡፡
በማህበራዊ ተሳትፎም አባል በሆንኩባቸው የተለያዩ ዕድሮች ውስጥ በኃላፊነት በመመረጥ አገልግያለሁ፡፡ ለዕድሮቹ ዕድገትም በህግ እውቀቴ ያለኝን ልምድ በማካፈል ለመርዳት ሞክሬያለሁ። የጥብቅና ሙያን መተዳደሪያዬ አድርጌ እስከ 1998 ድረስ በመስራት እኔንና ቤተሰቤን ብቻ ሳይሆን አገርና ሕዝብን ጠቅሜበታለሁ፡፡
በ1937 ዓ.ም ተመስርቶ 70 ዓመታት ባስቆጠረው ትዳራችንም 14 ልጆችን ያፈራን ሲሆን በርካታ የዘመድ ልጆችንም አሳድገናል። የልጅ ልጆችንም አይተናል፡፡ ልጆቻችን ተምረው ዶክተር፣ አካውንታንት፣ ነርስ፣ ፀሐፊ፣ ማርኬቲንግ ኦፊሰር… ሆነዋል፡፡ በህይወቴ የገጠመኝ መሪር ሀዘን ቢኖር በልጄ ቢኒያም ዘውዴ ሞት የደረሰብኝ ስቃይ ነው፡፡ በህክምና ትምህርት በዶክትሬት ለመመረቅ ሁለት ወር ሲቀረው ሚያዚያ 5 ቀን 1998 ዓ.ም በሞት ስለተለየኝ ጥልቅ ሀዘን ተሰምቶኛል፡፡
በአሁኑ ጊዜ እኔም ሆንኩ ባለቤቴ በአንፃራዊነት ጤናማ በሆነ ሁኔታ ላይ ነው የምንገኘው፡፡ ለዚህ የበቃሁትና ይህንን የታደልኩት ባለቤቴ ወ/ሮ ትክክልወርቅ ሞጆን ከመሰለች መልካም ጠባይና የዋህ ተፈጥሮ ካላት ሴት ጋር እግዚአብሔር ስላገናኘኝ ነው፡፡ 70 ዓመታት አብሮ መኖር መቻል ከእግዚአብሔር እንጂ ከሰው የሚገኝ ዕድል አይደለም፡፡ እኔም ኑሮዬ ተሟልቶ የመገኘቱ ምክንያት የባለቤቴ መልካም መሆን አስተዋጽኦ እንዳለበት እገነዘባለሁ፡፡ “መልካም ሴት ለባሏ ዘውድ ናት” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል በተግባር አሳይታኛለች፡፡
ከባለቤቴ ከወ/ሮ ትክክልወርቅ ሞጆ ጋር ለመንፈሳዊ ጉዞ ከአገር ውጭ ኢየሩሳሌም ቅዱስ መድኀኒዓለም ቤተክርስቲያን የሄድን ሲሆን በአገር ውስጥም በአራቱም ማዕዘን ወደተለያዩ አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት ተጉዘናል። ልጆቻችን ወዳሉበት የአሜሪካን የተለያዩ ግዛቶች በመሄድ ለመጎብኘት ዕድል አግኝተናል።
የወር ደሞዝተኛ በነበርኩበት ጊዜ ሆነ በግል ሥራም ተሰማርቼ ስሰራ በየዕለቱ የሚገኘውን ገቢ በእቅድ የመምራት ችሎታ ስለነበረኝ፤ ኑሮዬ ሳይዛባ ለዛሬ ደርሻለሁ፡፡ በትዳር አጋሬ ብቻ ሳይሆን በልጆቼም ተባርኬያለሁ፡፡ ልጆቼ አስቀይመውኝ አያውቁም፤ ልጆቻቸውም የተባረኩ እንዲሆኑላቸው እመኝላቸዋለሁ። እኔንና ቤተሰቤን ጠብቆ ለዚህ ያደረሰን እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ህዝቧንም ይባርክ!!”  

Read 4136 times