Saturday, 25 April 2015 10:28

ኢትዮጵያም ስለ ልጆቿ አለቀሰች!

Written by  በዲ/ን ተረፈ ወርቁ nikodimos.wise7@gmail.com
Rate this item
(6 votes)

የለቅሶና የዋይታ ድምፅ በደቡብ አፍሪካ፣ በየመን፣ በሊቢያ…

‹‹. . . ዓይኔ በእንባ ደከመ፣ አንጀቴም ታወከ። ስለ ወገኔ ሴት ልጅ ቅጥቃጤ አንጀቴ በምድር ላይ ተዘረገፈ፡፡ አቤቱ የሆነብንን አስብ፣ ተመልከት ስድባችንንም እይ . . .፡፡››  (ሰቆ. ፪፣፲፩ ፤ ፭፣፩)ይህን ቃል የተናገረው በመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ዘንድ ‹‹አልቃሻው፣ ባለ ሙሾው ነቢይ›› በመባል የሚታወቀው አይሁዳዊው ነቢዩ ኤርምያስ ነው፡፡ ይህንን ነቢይ እንዲህ እንደ ርኁሩኋ እናት አንጀቱን ያላወሰው፣ እንባው እንደ ክረምት ጎርፍ እንዲፈስ ያደረገውና ነፍሱ ድረስ ዘልቆ ብርቱ ኀዘንና ቅጥቃጤን የፈጠረበት ምክንያቱም፡- ኢየሩሳሌም በጠላቶቿ ተማርካ፣ ሕዝቦቿም ተዋርደው፣ ከአገራቸውና ከምድረ ርስታቸው ተነቅለው፣ ያ እጅጉን ያከብሩትና ይፈሩት የነበረው መቅደሳቸው ፈርሶ፣ በግዞት ውስጥ የነበሩትን የሕዝቡን ሰቆቃና መከራ በዓይኑ በማየትና የመከራቸውም ተካፋይ በመሆኑ ነበር፡፡፡ጸሎተኛውና ኀዘንተኛው ኤርምያስ ስለ ኢየሩሳሌም ኃጢአትና በደል፣ በዚህም ስለደረሰባት ከባድ ውርደትና መከራ፣ ዓይኔ ምነው የእንባ ምንጮች ፈሳሽ በሆኑልኝ በማለት የተመኘ፣ በብርቱ የጸለየ፣ የተማጸነና የማለደ የሀገሩ፣ የሕዝቡ ውርደትና ጭንቀት፣ መከራና አበሳ፣ ሰቆቃና ዋይታ እንቅልፍ፣ እረፍት የነሳው ብርቱ የእግዚአብሔር ነቢይ ነበር፡፡ከረሃብ የተነሳ እናቶች የአብራካቸውን ክፋይ ልጆቻቸውን የበሉበትን፣ በቅምጥልነት የኖሩ የኢየሩሳሌም ቆነጃጅትና ደናግል በጠላቶቻቸው ብርቱና ጨካኝ ክንድ ከሰውነት ክብር ተዋርደው፣ ከመፈራትና ከመወደድ የክብር ሰገነት ላይ ተሽቀንጥረው፣ ተንቀውና ተጥለው በጎዳና ያለ ምንም ተስፋ ሲንከራተቱና የሁሉም መጫወቻና ማላገጫ ሲሆኑ ሕፃናት በእናቶቻቸው ደረቅ ጡት ላይ አፋቸው ተጣብቆ በጣእረ ሞት ተይዘው ሲጨነቁ፣ አባቶችና እናቶች የጥንቱን የበረከትና የድሎት ኑሮአቸውን እያሰቡ እንባ ሲቀድማቸው፣ ከክፉ ጠኔ የተነሳ ወላዶች የማኅፀናቸውን ፍሬ እንኳን
ለመብላት ያስጨከናቸውን ያን ክፉ ቀናት የታዘበ ነቢዩ፤ ስለ ቅድስት ምድሩና ሕዝቡ ሰቆቃና መከራ እንዲህ ጸለየ፡- ‹‹እግዚአብሔር ከሰማይ እስኪጎበኝና እስኪመለከት ድረስ ዓይኔ ሳታቋርጥ ዝም ሳትል እንባን ታፈሳለች፡፡›› (ሰቆ ፫፣፵፱፣፶) በማለት በመጮኽና በመቃተት ስለ አገሩ ውርደት፣ ስለ ሕዝቡ መከራ
ሌት ተቀን በእንባ ባሕር እንደዋኘ ውሎ የሚያድር ኀዘንተኛና ሙሾ የሚደረድር ነቢይ ነበር፤ አይሁዳዊው የእግዚአብሔር ሰው ኤርምያስ።ሰሞኑን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ሁሉ እንደ አይሁዳዊው ነቢይ ኤርምያስ አንገታችንን የሚያስደፋና በሃፍረት የሚያሸማቅቅ፣ ጆሮን ጭው የሚደርግ፣ የወላድ እናቶችን አንጀት
የሚያላውስና በእንባ ጎርፍ እንዲታጠቡ የሚያደርግ ሌላ የሞት፣ ሌላ የውርደት፣ መሪር መርዶ፣ ሰቅጣጭና ክፉ ዜና ለእናት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ምድር፣ ከሊቢያ፣ ከደቡብ አፍሪካ፣ ከሀገረ የመን ተሰምቷል፡፡በእርግጥ የአገራችንና የወገናችን ውርደትና መከራ ገና ዛሬ የተጀመረ አይደለም። በርካታ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ዓለምን ሁሉ እግዚኦ ካሰኘ ድርቅ፣ የረሃብ/የጠኔ እልቂት እስከ የወንድማማቾች የእርስ በርስ ደም መፋሰስ፣ ዘግናኝ ጦርነትና ፍጅት ድረስ የሕዝባችን ስደት፣ መከራና ውርደት የአገራችን ዋንኛ መለያ ሆኖ አብሮን ለዓመታት ዘልቋል። በዓለም ሁሉ ፊት ኢትዮጵያዊነት ብዙዎችን እንዲሳቀቁ ያደረጋቸው “አሳፋሪ” ማንነት የሆነበትን ጥቁር ታሪካችንን ዛሬም ገና በቅጡ ልንላቀቀው እንዳልቻልን እያየን፣ እያስተዋልን ነው፡፡ስደትና ውርደት፣ መከራና ሞት የሕዝባችን ዕጣ ፈንታ እንዲሆን የተፈረደበት ይመስል ዛሬም ምስኪን ሕዝባችን በሚሰቀጥጥ ሁኔታ የአውሬ፣ የበረሃና የባሕር ሲሳይ እየሆነ ነው፡፡ በለስ ቀንቶት ወደ ባዕድ ምድር የገባው ሕዝባችንም ከእንስሳ በወረደ ሁኔታ ሰብአዊ ክብሩ ተደፍሮና ተዋርዶ፣ የሞት ሞት እንዲሞት የተደረገበትን አጋጣሚዎችንም ደግመን ደጋግመን ታዝበናል፡፡ በሳውዲ አረቢያ ሊያውም በአገራችን ኤምባሲ ፊት ለፊት አስክሬኗ በመኪና መሬት ለመሬት እንዲጎተት የተደረገበትን ያን አንገታችንን ያስደፋንን የወገናችንን ውርደት መርሳት እንዴት ይቻለናል?!በመካከለኛው ምሥራቅ ከፎቅ ላይ የሚወረወሩ፣ የፈላ ውሃ የሚደፋባቸው፣ አሰቃቂ የሆነ ግፍና ውርደት የሚፈጸምባቸው… የእህቶቻችን ሰቆቃና መከራ ዛሬም ማብቂያ የተገኘለት አይመስልም። በኬንያ፣ በታንዛንያ፣ በማላዊና በሞዛምቢክ እንዲሁም በመካከለኛው ምሥራቅ “ሕገ ወጥ” ናችሁ በሚል ሰበብ በእስር ቤት ታጉረው ፍዳ መከራቸውን እየቆጠሩና “የወገን ያለህ ደረሱልን” እያሉ
የሚገኙ ወገኖቻችን ቁጥርም ቀላል አይደለም።በቅርቡም በደቡብ አፍሪካ ምድር ወገኖቻችን በቁማቸው በእሳት እንዲጋዩ፣ በቆንጨራና በጥይት ተደብድበው እንዲገደሉ ተፈረደባቸው። ጥረው ግረው፣ ለፍተውና ደክመው ያከማቹት ሀብት ንብረታቸውም የዘራፊዎች ሲሳይ ሆነ። ይሄ ያደረሰብንን ጥልቅ ሃዘን በቅጡ ሳንወጣ ዳግመኛ ልባችንን በኀዘን ጦር የወጋ፣ ጆሮን ጭው የሚያደርግ ክፉ ወሬ ከወደ ሊቢያ ምድር ሰማን፡፡ 28
የሚሆኑ ወገኖቻችን በሊቢያ በረሃ ዘግናኝ በሆነ አኳኋን በግፍ ታርደው ሰማዕትነትን መቀበላቸውን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን አረዱን፡፡በንጉሥ ሄሮድስ ዘመን ለተፈጁት 14 ሺ አይሁዳውያን ሕፃናት ነቢዩ ኤርምያስ፡- ‹‹የጩኸት፣ የጣርና ሰቆቃ ድምፅ በራማ ተሰማ፣ ራሄል ስለ ልጆቿ አለቀሰች የሉምና፡፡›› እንዳለው ዛሬም ከመካከለኛው ምሥራቅ፣ ከየመን፣ ከደቡብ አፍሪካ፣ ከሊቢያ… ምድር የልጆቿን ጩኸት፣ ሰቆቃና ዋይታ የሰማች እማማ ኢትዮጵያም ማቅ ለብሳ፣ ትቢያ ነስንሳ ሙሾን እያወረደች ነው፡፡ የልጆቿ ኀዘን፣ ሰቆቃና ዋይታ ገና በቅጡ ያልታበሰላት ምድር፤ ዛሬም ዕጣ ፈንታዋ ዕንባና ደም፣ ሰቆቃና ዋይታ ሆኗል፡፡መንግሥት ሕዳሴዋ በደጅ ነው፣ ልማቷና ዕድገቷም እየተፋጠነ ነው ቢልም አገራችን ዛሬም ለልጆቿ ጥላና ከለላ ለመሆን የቻለች አይመስልም። ከሳዑዲ አረቢያ ውጡልን ተብለው ወደ እናት አገራቸው ተመልሰው ከነበሩ እህቶቻችን መካከል “ከዚህስ ኑሮ ብንሞትም ብንድንም እዚያው አረብ አገር ይሻለናል” በሚል ተስፋ ቆርጠው ዳግመኛ በመጡበት እግራቸው ሲመለሱ ታዘበናል፡፡የብዙዎች ወገኖቻችን እንባና ደምም ለለውጥና ለአዲስ ተስፋ በሀገራችን ተራሮችና ሸንተረሮች እንደ ውሃ ፈሷል፡፡ የአንድ ማኅፀን አብራክ ክፋዮች እርስ በርሳቸው ተራርደዋል፣ ተላልቀዋል። ብዙዎቻችንም ነፍሳችን እስክትዝል ለሀገራችን ለውጥ በብዙ አንብተናል፣ ወጥተናል ወርደናል፡፡
የለውጥ ያለህ በሚል፣ ከልብ በሆነ ናፍቆትም ነደናል፣ ተቃጥለናልም፡፡ ዛሬም በናፍቆት እንደተቃጠልን፣ እንደ ሽንብራ እንደተርገበገብን፣ በናፍቆት ነፍሳችን እንደዛለች መሽቶ ይነጋል፡፡ይህችን በለውጥ ናፍቆት፣ የተስፋ ጭላንጭል ያለህ በሚል የዛለች ነፍሳችንን አይዞሽ የሚሏት፣ የውስጣችንን ጩኸት የሚመልሱ፣ ስብራታችንን የሚጠግኑልን፤ ታሪካችንን፣ የሚያድሱልንና ለነገ ብሩህ ተስፋ ሊያሳዩን የሚችሉ ደጋግ፣ ሁሉን በፍቅር የሚያዩ መሪዎች፣ ፖለቲከኞች፣ የሃይማኖት መሪዎችና መንፈሳዊ አባቶች እንዲኖሩን ደጋግመን ተመኝተናል፡፡ ግና እምብዛም አልተሳካልንም፡፡ ተስፋችን ያዝነው ስንለው እያመለጠን፣ ጉልበታችን ዝሎ ከዚሁ የዘመናት እንቆቅልሾቻችን፣ ያለ ቅጥ ከረዘመው የጨለማው ዘመን ዥንጉርጉር ታሪካችን፣ ጉስቁልናና ውርደት ከተሞላው አስከፊ ገጽታችን ጋር አብረን እየተጓዝን እዚህ ደርሰናል፡፡“አቤቱ እባክህ የሆነብንን አስብ፣ ተመልከት ስድባችንንም እይ . . .፡፡››
ሰላም! ሻሎም!

Read 4130 times