Saturday, 25 April 2015 10:07

የረቡዕ እለቱ ሰልፍ በአለም አቀፍ ሚዲያዎች ትኩረት ተሰጥቶታል

Written by 
Rate this item
(7 votes)

ሰማያዊ ፓርቲ ከመንግስት የቀረበበትን ውንጀላ ተቃውሟል

      በአሸባሪው ቡድን IsIs ታጣቂዎች አሰቃቂ ግድያ የተገፀመባቸው ኢትዮጵያውያን ሰማዕታትን ለመዘከርና ሽብርተኝነትን ለማውገዝ ባለፈው ረቡዕ መንግስት በጠራው ህዝባዊ ሰልፍ ላይ ተቃዋሚ ከፀጥታ ሃይሎች ጋር የፈጠሩት ግጭት የዓለም አቀፍ ሚዲጠያዎችን ትኩረት ስቧል፡፡በእለቱ በአልጀዚራ በተላለፈ ዘገባ፤ ህዝቡ በከፍተኛ ጩኸትና ቁጣ መንግስትን የሚተቹ መፈክሮችን እያሰማ ባለበት፣ በፀጥታ ሀይሎች የተወሰደው እርምጃ ታይቷል፡፡ ሰልፈኞች ሲደበደቡ የሚያሳዩ የተለያዩ ምስሎችም ተሰራጭቷል፡፡ የኢትዮጵያውያኑን በISIS ታጣቂዎች የመገደል አሰቃቂ ትዕይንት በተደጋጋሚ በምስል አስደግፎ ሲያቀርብ የነበረው ዩሮ ኒውስ፤ ረቡዕ እለት ምሽት ጀምሮ ሰልፉ ሲጀመር የነበረውን ሁኔታና በሰልፉ ማጠናቀቂያ ላይ ፖሊስ ከሰልፈኛው ጋር የተጋጨበትን ትዕይንት አሳይቷል፡፡ በዚህ አጭር የቪዲዮ ትዕይንት፤ መሬት ላይ የወደቁ ወጣት ሴቶች በፖሊስ ሲደበደቡ እንዲሁም አንድን ወጣት በርካታ ፖሊሶች መሬት ላይ በወደቀበት ሲደበድቡ ተስውሏል፡፡ ለረቡዕ እለቱ ሰላማዊ ሰልፍ ትኩረት ሰጥቶ የዘገበው ቢቢሲ በበኩሉ፤ ሰልፈኛው ያሰማውን ተቃውሞና
በመጨረሻም ፖሊስ የሃይል እርምጃ ሲወስድ የሚያሳይ ዘገባ አስተላልፏል፡፡ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን ሰልፉ ከተከናወነ ከሰአታት በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ የታሰበው ሰልፍ በስኬት መጠናቀቁን ጠቁመው አንዳንድ ህገ ወጦች በሰልፉ ላይ ረብሻ ማስነሳታቸውንና ከዚህ ጀርባም የሰማያዊ ፓርቲ እጅ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ረብሻውን ተከትሎ በ7 የፌደራል ፖሊስ አባላት ላይ የመቁሰል አደጋ መድረሱን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ በሰልፉ የተሳተፉ ሰዎች ላይ ጉዳት ስለመድረሱ የተናገሩት ነገር የለም፡፡ በእለቱ ሪፖርተራችን በመስቀል አደባባይ ተገኝቶ እንደተመለከተው፤ በተለይ በቅዱስ ዮሴፍ ት/ቤት አካባቢ በቡድን የተደራጁ ወጣቶች በከፍተኛ ጩኸት መንግስትን የሚያወግዙ መፈክሮች እያሰሙ
ሲቃወሙ እንደነበር ለመታዘብ ተችሏል፡፡ በሰላማዊ ሰልፉ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ ሽብርተኝነትን የሚያወግዘውን ንግግር እያደረጉ ሳለም ከፍተኛ ጩኸትና ተቃውሞ የተስተጋባ ሲሆን አንዳንዶችም ከፖሊስ ጋር ግጭት ፈጥረዋል፡፡ በመንግስት የተጠራውን ሰልፍ ተከትሎ፣ አብዛኞቹ የግልና የመንግስት መስሪያ ቤቶች ዝግ የነበሩ ሲሆን በከተማው አንዳንድ አካባቢዎች የታክሲ እጥረት ተፈጥሮ እንደነበርም ታውቋል፡፡  ፖሊስ ሰልፉን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ የተጠቀመ ሲሆን በርካቶች በግርግርና በትርምስ መሃል ወድቀው ለጉዳት ተዳርገዋል፡፡ የቀይ መስቀል አምቡላንሶችም ተጎጂዎችን ወደ ዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ሲያመላልሱ የነበረ ሲሆን ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው ግለሰቦች ከሰዓት በኋላ እየታከሙ

ከሆስፒታል ወጥተዋል፡፡ ፖሊስ በረብሻው መሃል ያገኛቸውን በርካታ ግለሰቦች በየቦታው በቡድን በቡድን ከሰበሰበ በኋላ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሲያመላልስ እንደነበር የአይን እማኞች ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
መንግስት ተቃውሞውን አደራጅቷል ሲል የወነጀለው ሰማያዊ ፓርቲ፤ ረቡዕ ዕለት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ፣ መንግስት የጠራውን ሰልፍ በመደገፍ አባላቱና ደጋፊዎቹ በሰልፉ ላይ እንዲገኙ ጥሪ ማስተላለፉንና ጥሪውን ተከትሎ እንደማንኛውም ዜጋ በሰልፉ ላይ የሄዱ የፓርቲው አመራሮችና አባላት ገና ወደ መስቀል አደባባይ ከመድረሳቸው በፊት እየታደኑ መታሰራቸውን አስታውቋል፡፡ ፓርቲው “መንግስታዊ ሽብር የህዝብን ቁጣ ያባብሳል እንጂ መፍትሄ አይሆንም” በሚል ባወጣው መግለጫው፤ “መንግስት በዜጎች ላይ የወሰደው የጭካኔ እርምጃ በእጅጉ የሚያሳዝንና በጥብቅ ሊወገዝ የሚገባው ነው” ብሏል፡፡ መንግስት፤ ረብሻውን ያነሳሳው ሰማያዊ ፓርቲ ነው ማለቱን አጥብቆ የተቃወመው ፓርቲው፤ “የመንግስትን ቸልተኝነት በተቃወሙ ሰዎች ላይ የተወሰደው እርምጃ ሳያንስ፣ ጉዳዩን ከአንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር አዛምዶ ተቃውሟቸውን ማጠልሸት በፍፁም ተቀባይነት የሌለው አፀያፊ ተግባር ነው፤ መንግስት ነኝ ከሚል አካል በፍፁም የማይጠበቅ ስህተት ነው” ብሏል፡፡ የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች  የተገኙት እንደማንኛውም ዜጋ በሰልፉ ለመሳተፍ እንደሆነም ፓርቲው አስታውቋል፡፡ በእለቱም 8 ያህል የአመራር አባላቱ ከሰልፉ በፊት እና በኋላ ተደብድበው መታሰራቸውን ፓርቲው አስታውቆ፤ በየፖሊስ ጣቢያውም በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መታሰራቸውን ለማረጋገጥ ችያለሁ ብሏል፡፡ሁለት የፓርቲው እጩ የምርጫ ተወዳዳሪዎችም ፖሊስ ጣቢያ ለታሰሩት የፓርቲው አመራሮች እራት ለማድረስና ለመጠየቅ በሄዱበት ወቅት መታሰራቸውን ፓርቲው አስታውቋል፡፡     


Read 5170 times