Saturday, 25 April 2015 10:07

የ“ቆንጆ” መፅሄት ባለቤት ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ካሳ አገር ጥሎ ተሰደደ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(6 votes)

     ላለፉት አራት ዓመታት ለንባብ ሊበቃ የቆየው የ“ቆንጆ” መፅሄት ባለቤትና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ካሳ ባለፈው ረቡዕ አገር ጥሎ መሰደዱን ምንጮች አዲስ ለአድማስ ገለፁ፡፡ ጋዜጠኛው በተለያዩ ጊዜያት የመንግስት ደህንነቶች ቢሮው ድረስ በመሄድ ዛቻና ማስፈራራት ስላደረሱበትና ጉዳዩ ከአቅሙ በላይ በመሆኑ አገሩን ጥሎ ለመሰደድ መገደዱን እንደነገራቸው ምንጮቹ ገልፀዋል፡፡ የደህንነት ኃይሎች በየጊዜው ወደ ቢሮው እየሄዱ “ክስና እስር ይጠብቅሃል” እያሉ ያስፈራሩት እንደነበር የገለፁት ምንጮች፤ ፕሬሱን የሚወነጅል ዘጋቢ ፊልም በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እየተሰራ ስለመሆኑ፣ ዘጋቢ ፊልሙ ከሚሰራባቸው የህትመት ውጤቶች አንዱ “ቆንጆ” መጽሄት እንደሆነ መረጃ እንደደረሰውና ደህንነቶቹ በየጊዜው እየተመላለሱ የሚያደርሱበትን ጫና መቋቋም ባለመቻሉ ባለፈው ረቡዕ አገር ጥሎ መሰደዱን ምንጮቹ ጠቅሰዋል፡፡ ከመፅሄቱ ሰራተኞች መካከል አንዱም፤ ደህንነቶች በቅርቡ መጥተው ፍላሽ እና ሌሎች ነገሮችን ቀምተውና አስደንግጠውት መሄዳቸውን ተናግሯል፡፡ ምንም ነገር ቢመጣ ከአገሩ ሳይወጣ በፅናት ለመቆየት እንደሚፈልግ ይነግራቸው እንደነበር የገለፁት ምንጮች፤ በአሁኑ ሰዓት በቀደመው ፅናቱ የሚያስቀጥል ሁኔታ ስላላገኘ አገሩን ጥሎ መሄዱን ነግሮናል ብለዋል፡፡ መፅሄቱ ከተመሰረተ አራት ዓመታት የሞላው ሲሆን የዛሬ ሳምንት ቅዳሜ 100ኛ እትሙ ለንባብ መብቃቱንም ምንጮች ገልፀዋል፡፡ ጋዜጠኛው ላለፉት 13 ዓመታት በጋዜጠኝነት ሙያ ላይ መቆየቱን ለማወቅ ችለናል፡፡  

Read 5643 times