Saturday, 25 April 2015 10:00

እናዝናለን … እንፅናናለን … እንፀናለን!!

Written by 
Rate this item
(12 votes)

አያዩት ግፍ የለ፤
አይሰሙት ጉድ የለ!
ካራ በዕርግብ አንገት፣ ለዕርድ እየሳለ
“ሠይጣን ሰለጠነ”፣ በደም ተኳኳለ!!!
ሌላነት(Otherness) የሚሉት አዲስ ሾተል አለው
ፀረ-ሰው ለመሆን፣ ማልዶ የሞረደው፡፡
“ዕወቁኝ” ነው የሚል፣ ይህ የገዳይ ቢላ
ሌላም ቋንቋ የለው፣ ወትሮም ለሰው- በላ፡፡
(ይሄን በላዔ-ሰብ፣ ማነው ስሙ? አትበሉ
ስሙን መጥራት ለሱ፣ ነውና እኩይ ድሉ፡፡
ይሄን በላዔ - ሰብ፣ ምን ዓለመ? አትበሉ፡፡
ከጀርባው ያለው ኃይል፣ ያው ደሞ እንዳመሉ
እኔ ነኝ ይለናል፣ ሲሞላለት ውሉ!)
*       *     *
አወይ ያገሬ ልጅ!
ወገኔማ ምን ያርግ፣ አደለም በውዱ
ግድ ሆኖበት እንጂ ነጥፎበት ማዕዱ
ቀን ቢወጣ ብሎ፣ ካገር መሰደዱ፡
ነው እንጂ እንዳቅሙ፣ ጎጆ እስከሚሠራ
የጎሸ ቀን በስሎ፣ ጠሎ እስከሚጠራ
መቼ ጥሞ ያቃል፣ የስደት እንጀራ?!
ወዮ የእናቴ ልጅ! ያ ሁሉ መከራ
ጉሮሮውን ሲያስብ አንገቱን ለካራ!!
*      *     *
ያንድ ቀን አይደለም፣ የጨካኝ ጉድ ጓዙ
ቀበቶን ማጥበቅ ነው፣ የቆራጥ ሰው ደርዙ!
የዚህን ሁሉ ግፍ
የመከራ ምዕራፍ
ገፆቹን ለማጠፍ፤
ራስ በራስ ቆመን፣ ጨክነን በዕርጋታ
ችግሩን ከሥሩ፣ የነቀልን ለታ
ሞት እዬዬ ይላል፣ ሆኖ በ‘ኛ ቦታ!!
ከመቀደም መማር፣ ትልቅ ዋጋ እንዳለው
መቼም ቀን ወደፊት፣ አለመቀደም ነው!!
(በስደት ላይ ሳሉ ልጆቻቸው በአረመኔዎች ለተጨፈጨፉባቸው
ወላጆችና በሐዘን ላይ ላለው የኢትዮጵያ ህዝብ)
                                          (ሚያዚያ 13 ቀን 2007)

Read 4932 times