Tuesday, 21 April 2015 08:20

የሃኪምና ህመምተኛ ምስጢር!

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

ለመሆኑ የህክምና ባለሙያው የህሙማኖችን ምስጢር ይዞ መቆየት የሚችለው እስከምን ድረስ ነው? ምስጢሩን ለማውጣት የሚገደድባቸው አጋጣሚዎችስ አሉ? በእነዚህና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያ ፍለጋ ያገላበጥኳቸውን መረጃዎችና የባለሙያ ምላሽ አብረን እንመልከት፡፡
   ገና በሃያ ስድስት ዓመት ዕድሜው የሆስፒታሎችና የሃኪሞች ቋሚ ደንበኛ ያደረገው በሽታ ምንነት ለቤተሰቦቹና ለቅርብ ጓደኞቹ ሁሉ እንቆቅልሽ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በትምህርቱም ሆነ በሥራው የተሻለ ደረጃ ላይ የሚገኝ ቢሆም ከቅርብ አመታት ወዲህ ህይወቱ ፈጽሞ ደስታ የራቀውና በጭንቀት የተሞላ ሆኖበታል፡፡
ህክምናውን ለመከታተል በግል የህክምና ተቋሙ ውስጥ አገልግሎት ከሚሰጠው ሃኪሙ ዘንድ ቀጠሮውን ሳያዛንፍ ይመላለሳል፡፡ ስለያዘው በሽታ ምንነትም ሆነ ስለአለበት ደረጃ ሃኪሙ ለማንም እንዳይናገር ቃል ያስገባው በመሆኑ ሰው ያውቅብኛል የሚል ስጋት የለበትም፡፡ ሀኪሙ ወጣቱን የያዘው የጉበት ካንሰር ህመም 3ኛ ደረጃ ላይ መድረሱን ያውቃል፡፡ ይሄም ማለት  በአገራችን የሚሰጠው የህክምና እርዳታ ጤናውን ወደነበረበት ለመመለስ እምብዛም የሚረዳው አይደለም። እንዲያም ሆኖ ግን በቀጠሮው ሲመጣ ህመም ማስታገሻዎችንና አንዳንድ መድሃኒቶችን ከመስጠት ቦዝኖ አያውቅም።
የታማሚው ወጣት ወላጅ እናትና ታላቅ ወንድሙ ሃኪሙ ዘንድ ተመላልሰው በመሄድ ስለወጣቱ ህመምና ችግር ለማወቅ ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም፡፡ ሃኪሙ ምንም የከፋ ችግር እንደሌለ እየነገረ በተደጋጋሚ መልሷቸዋል፡፡
 ህመሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰና እየጠነከረ ሄደ፡፡ የወጣቱ ቤተሰቦች ጉትጐታና “ምንህን ነው የሚያምህ?” ጥያቄ እያየለበት መጣ፡፡ ከህመሙ ጋር እየታገለ በሽታውን ሚስጢር እንዳደረገ ለመቆየት ጥረት ቢያደርግም አልቻለም፡፡
ስለሁሉም ነገር ለቤተሰቦቹ በዝርዝር ነገራቸው፡፡ ህመሙ ተስፋ ቢስ ከሚባል ደረጃ ላይ መድረሱንም አረዳቸው፡፡ ሁኔታው ቤተሰቦቹን በእጅጉ አሳዘናቸው፡፡ ቀደም ብለው ስለችግሩ አውቀው ቢሆን ኖሮ መፍትሔ ሊያፈላልጉለት ይችሉ እንደነበር በማሰብ  ተበሳጩ፡፡ የወጣቱን ህመም ደብቆ ለከፋ ደረጃ ያደረሰው ሃኪሙ ነው ሲሉም የህክምና ባለሙያውን ወቀሱት፡፡ ለወጣቱ ህይወት ተጠያቂ አድርገው በህግ እንደሚጠይቁትም አስጠነቀቁት፡፡
ሃኪሙ በዚህ የሃያ ስድስት ዓመት ወጣት ላይ የደረሰው ችግር በእጅጉ ቢያሳዝነውም አትንገርብኝ ያለውን የህመምተኛውን ሚስጢር መጠበቅ ሙያዊ ግዴታው መሆኑን ገለፀላቸው፡፡
በህግ የመጠየቅ መብታቸውን እንደሚያከብርና ስለጉዳዩ በተጠየቀ ጊዜ በቂ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑንም ነገራቸው፡፡ በጉበት ካንሰር ህመም ተይዞ ህመሙን በሚስጢር በመያዝ ህክምናውን ይከታተል የነበረው ወጣት፤ በዚሁ ህመም ሳቢያ ህይወቱ ሲያልፍ ዶክተሩ ክፉኛ ቢያዝንም በሙያው ሊያደርግ የሚችለውን እርዳታ ሁሉ በማድረጉ ተፅናንቷል፡፡ ከሟቹ ወጣት ቤተሰቦች ዘንድ እስከአሁን የመጣበት ህጋዊ ጥያቄ አለመኖሩንም ዶክተሩ ይናገራል፡፡
ለመሆኑ የህክምና ባለሙያው የህሙማኖችን ምስጢር ይዞ መቆየት የሚችለው እስከምን ድረስ ነው? ምስጢሩን ለማውጣት የሚገደድባቸው አጋጣሚዎችስ አሉ? በእነዚህና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያ ፍለጋ ያገላበጥኳቸውን መረጃዎችና የባለሙያ ምላሽ አብረን እንመልከት፡፡ በህክምና ሙያ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠውንና የህክምና ባለሙያው “ሌላ ሰው ማወቅ የማይገባውን የህሙማኖቼን ማንኛውንም ነገር በሚስጢር እጠብቃለሁ” ሲል የሚገባውን የሒፓክራተስ ቃለ መሃላ ማክበርና መጠበቅ ከእያንዳንዱ የህክምና ባለሙያ የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡ በህክምና ሙያ ዘርፍ ከተደረጉት ታላላቅ ስምምነቶች መካከል የጄኔቫው ስምምነትም ይህንኑ ቃል በተግባር መዋል ያለበት መሆኑን የሚያስገነዝብ አንቀፅ በስምምነቱ ውስጥ አካትቷል፡፡ “ህሙማኖቼ እኔ በምስጢር እንድይዝላቸው የነገሩኝን ሁሉ በአክብሮትና በምስጢር እይዝላቸዋለሁ፡፡ ህሙማኑ ቢሞቱ እንኳን ጉዳዩ እኔው ዘንድ ሚስጢር እንደሆነ ይቀራል” ይላል የጄኔቫው ስምምነት፤ በእነዚህ ሁለት ታላላቅ የህክምናው ዘርፍ ቃለመሃላና ስምምነቶች መሠረት፤ ማንኛውም የህክምና ባለሙያ ታማሚውን የሚመለከት ከታማሚው የሚሰጠውን ማንኛውንም ዓይነት መረጃ ለሌላ ሰው አሣልፎ መስጠት አይችልም፡፡ የታማሚውን ሚስጢር ለመጠበቅም ከፍተኛ ጥንቃቄን ያደርጋል። ታማሚው እንዲደበቅለት የሚፈልገውን ሚስጢርም በታማኝነት የመጠበቅ ሙያዊ ግዴታ አለበት፡፡
ማንኛውም የህክምና ባለሙያ የታማሚ ደንበኛውን ምስጢር ለማውጣት ከሚገደድባቸው ምክንያቶች ውጪ በየትኛውም አካል ምስጢሩን እንዲያወጣ ዛቻና ማስፈራራት ሊደረግበትም ሆነ ሊገደድ እንደማይገባው Medical Ethics የተሰኘ የህክምና ጆርናል ይገልፃል፡፡ ሃኪሙ የታማሚውን ምስጢር ለማውጣት ከሚገደድባቸው ዋና ዋና ምክንያቶች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡
ምስጢሩ በሃኪሙ እንዲጠበቅለት የፈለገው ታማሚ የያዘው ህመም ለህብረተሰቡ ጤናና ደህንነት ሥጋት ሊሆን የሚችል አደገኛና ተላላፊ በሽታ ከሆነ፤
በህብረተሰቡ ላይ አደጋ ሊፈጥር የሚችል የጤና ችግር እንዳለበት እያወቀ ከሆነ ለምሳሌ የእይታ ችግር ያለበት ታማሚ ተሽከርካሪ እንደሚነዳ እያወቀ በሚስጢር ከደበቀ ወይም እንደ ታይፎይድና ኮሌራ ያሉ ተላላፊ በሽታዎች እያሉበት እንደ ሆቴል ባሉ የህብረተሰብ መገልገያ ሥፍራዎች መስራቱን ካወቀ፣
ታማሚው የፈፀመው ወንጀል ኖሮ ወንጀሉ በሌላ ሰው ላይ ጉዳት ያደረሰ ወይም የሚያደርስ መሆኑን ካወቀ፡፡
ታማሚው ራሱን የማጥፋት ፍላጐት እንዳደረበት ነግሮት፣ ይህንኑ በምስጢር እንዲይዝለት ከጠየቀው ሃኪሙ ጉዳዩን ለሚመለከተው ክፍል በማሳወቅ ታማሚውን ከአደጋው ሊታደገው ይገባል፡፡
በእነዚህ በዝርዝር በተጠቀሱ ጉዳዮች አስገዳጅነት ሃኪሙ የታማሚውን ምስጢር ሊያወጣ ይችላል፡፡ 

Read 3760 times