Print this page
Tuesday, 21 April 2015 08:16

“ረባሽ ተቃዋሚ” ፓስፖርቱን ይነጠቃል!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(3 votes)

(ማተምያ ቤት የቅዳሜ ጋዜጣን ማክሰኞ አውጥቶ ምንም አይባልም - Only in Ethiopia!)

   ባለፈው ቅዳሜ በወጣው የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዕትም ላይ አንድ ትኩረት የሚስብ ርዕስ ተመለከትኩ-“የሠማያዊ ፓርቲ ሊ/ቀመንበር--ፓስፖርት ተመለሰላቸው” ይላል፡፡ ኢንጂነሩ እንደተናገሩት፤ ለፓርቲ ስብሰባ ወደ አሜሪካ ለመሄድ ሲሞክሩ ነበር ቦሌ አየር ማረፊያ ላይ ፓስፖርታቸውን የተነጠቁት። ጎበዝ! አሁን ነው እንግዲህ መጠያየቅ፡፡ ማነው ነጣቂው? (ህግ ያለበት አገር መስሎኝ!) ወይስ እኛ ሳንሰማ--“ረባሽ ተቃዋሚ ፓስፖርት ይነጠቃል!” የሚል መመሪያ ወጥቷል? ህጉ ሳይኖር መንጠቅ ከተጀመረ ነው አደጋው (ህግ በግለሰቦች እጅ ሥር ወደቀች ማለት እኮ ነው!) እናላችሁ--ከአሜሪካ ጉዞ ተስተጓጉለው ቀሩ፡፡
አያችሁ--ዛሬ ባልተጻፈ ህግ ከአሜሪካ ጉዞ መከልከል ከተቻለ፣ ነገ ወዴት ሊያድግ እንደሚችል አስቡት፡፡ ይሄ እኮ ፍጥጥ ያለ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው፡፡ እኔ መቼም ይሄ የተፈጸመው በመንግስት ቀጭን ትዕዛዝ ነው ቢሉኝ ጨርሶ አላምንም፡፡ (መንግስት የመላዕክት ስብስብ እንዳልሆነ ባውቅም!) የእኔ ጥርጣሬ ምን መሰላችሁ? ምናልባትም የ“ጸረ-ሰላም ኃይሎች” ስውር ደባ እንዳይሆን የሚል ነው። ከ20 ዓመት በላይ አገር የመምራት ልምድ ያለው መንግስት እንዲህ ያለ ሥራ ይሰራል ብዬ አላምንማ!  
በነገራችን ላይ ለሰማያዊ ፓርቲ ወይም ለተቃዋሚዎች መብት እየተከራከርኩ እንዳይመስላችሁ፡፡ (እነሱ ለራሳቸው መች ያንሱና!) እኔ የተከራከርኩት ለራሴ ነው-- ለህገመንግስታዊ መብቴ፡፡ የተሟገትኩትም ለህግ የበላይነት ነው። (“ነግ በእኔ” አለ የሀገሬ ሰው!) በነገራችን ላይ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ሰሞኑን ወደ አሜሪካ መጓዛቸውን ምንጮቼ ነግረውኛል - በተለያዩ ስቴቶች የፓርቲያቸውን ስብሰባ ይመራሉ ተብሏል፡፡ (“ጸረ-ሰላም ኃይሎች” አልነበሩም ማለት ነው!)
ባለፈው ማክሰኞ ሌሊት ላይ ነው፡፡ አንዳንድ ነገሮችን እየሞነጫጨርኩ EBCን እመለከታለሁ። (መሞነጫጨር እንጀራዬ ነዋ!) ኢቢሲን የማየው ግን ሌላ ምርጫ አጥቼ እንዳይመስላችሁ፡፡ በአገሬ ምርት ስለምኮራ ነው (የሚያኮራ ምርት ጠፋ እንጂ!) እናላችሁ … ዜና ላይ ይመስለኛል፡፡ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ከስዊድን ተመክሮ በመውሰድ፣ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ የመጀመሪያ ዙር የከሸፈውን በሁለተኛው ዙር ለማሳካት እንቅስቃሴ መጀመሩን ሰማሁ፡፡ የመጀመሪያው ዙር የከሸፈው ለምን መሰላችሁ? እንግዲህ ከEBC እንደሰማሁት፤ የደቡብ አፍሪካ ተሞክሮ ነበር የተወሰደው። ግን አልተሳካም!!  ለምን አልተሳካም? እንዴት አልተሳካም? ምን ያህል “የግብር ከፋዮች” ገንዘብ  ውሃ በላው? (ተጠያቂዎቹ ከአገልግሎት ክልል ውጭ ናቸው!)
እኔ የምላችሁ ግን … የሰው አገር ተመክሮ ዝም ተብሎ አፈፍ ይደረጋል እንዴ? (ያለ ጥናት ማለቴ ነው!) ቀድሞ ተሞክሮ ቢሆንማ … በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ የመጀመሪያ ዙር ማጠናቀቂያ ላይ የደቡብ አፍሪካው ተሞክሮ እንደከሸፈ አይነገረንም ነበር፡፡ (አቤት የተሞከረውና የከሸፈው አበዛዙ!) በነገራችን ላይ  መቼ ይሆን የሰው አገር ተመክሮ ከመቅዳት የምንገላገለው? (ተማሪዎችን ብቻ አትኮርጁ ማለት ውጤታማ አይሆንም!) ለመሆኑ እንደ አሸን የፈሉት ዩኒቨርሲቲዎች ሥራቸው ምንድነው! (“ህንፃ እንጂ ዕውቀት መች ገነባን” እንዳትሉኝ!)
ለመንግስት ወይም ለገዢው ፓርቲ አንድ ጥያቄ ጣል አድርጌ ልለፍ፡፡ ለመሆኑ መንግስት ከሙስና ውጭ በአቅም ማነስ፣ በእንዝላልነት፣ ጥናት ላይ ባልተመሰረተ ውሳኔ፣ ወዘተ… ለደረሱ አገራዊ ጥፋቶችና ኪሳራዎች ሹማምንቱን ተጠያቂ አድርጎ ያውቃል? … እስካሁን በተጠቀሱት ጥፋቶች የተከሰሰ፣ ከኃላፊነት የተነሳ፣ በገንዘብ የተቀጣ፣ በአደባባይ የተገሰፀ … የመንግስት ባለስልጣን አለ? (አምባሳደርነት ጡረታ እንጂ ቅጣት አይደለም!)
የሆኖ ሆኖ-- የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ በስዊድን ተመክሮ በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይም ጥርጣሬ አለኝ፡፡ (ባይኖረኝ ነበር የሚገርመኝ!) ለምን መሰላችሁ? አሁንም በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ሁለተኛ ዙር ማጠናቀቂያ ላይ “አልተሳካም!!” ላለመባላችን ምንም ዋስትና የለንም፡፡ (ለነገሩ “አልተሳካም!” መባል ብርቃችን አይደለም!) ወዳጆቼ … አንድ ነገር ልንገራችሁ--- “ነገሮችን ከወትሮው በተለየ መንገድ ሳንሰራ ከወትሮው የተለየ ውጤት መጠበቅ የዋህነት ነው!!” (የእኔ ሳይሆን የኒዮሊበራሊስቶች ቃል ነው!)  
ዛሬ እንግዲህ ከአገሬ ምርት አልወጣሁም (ከEBC ማለቴ ነው!) አሁን ደግሞ ረቡዕ ሌሊት ነው፡፡ ፕሮግራሙ የህትመት ዳሰሳ ነው፡፡ (ህትመት ሳይኖር ዳሰሳ?!) በነገራችን ላይ የግሉ ፕሬስ እንዳሁኑ ዘመን ፍዳውን አይቶ አያውቅም፡፡ ከመንግስት “በትር” የተረፉት ጥቂት ፕሬሶች፣ በ“ብርሃንና ሰላም” ማተሚያ ቤት “በትር” እየተጎዱ ነው፡፡ የግል ፕሬሱ እንደ ህዝቡ ሁሉን ቻይ ሆኖ ነው እንጂ ማተሚያ ቤቱ ያላደረሰበት በደል የለም፡፡ (በብቃትና በአቅም ማነስ ጦስ!) ግን እኮ አላወቀው ይሆናል እንጂ ፍ/ቤት የሚያስገትር ጥፋት እየሰራ ነው-ማተሚያ ቤቱ።  ሌላው ቢቀር እንኳን “የህዝብን መረጃ የማግኘት መብት” እያደናቀፈ ነው፡፡
የሚገርም እኮ ነው----የቅዳሜን ጋዜጣ በራሱ ችግር በአራተኛ ቀኑ (ማክሰኞ) ሲያወጣ ማንም ምንም አይለውም፡፡ (Only in Ethiopia ማለት ይሄ ነው!) እንዲህ ያለ ነገር ከኢትዮጵያ በቀር የትም የሚቻል አይመስለኝም- በኢትዮጵያ ብቻ!! አሁን አንዳንድ የግል ፕሬሶች ምን እየተመኙ እንደሆነ ታውቃላችሁ? (ምኞቱ ባይቻልም!) የመንግስቶቹን አዲስ ዘመንን ወይም ሄራልድን---መሆን! (በቀናቸው የሚወጡ እነሱ ብቻ ናቸዋ!) ማተሚያ ቤቱ በደንበኞች መካከል የሚያደርገው አድልዎ ጨጓራ ይልጣል- በተለይ በግል ፕሬስና በመንግስት ፕሬስ መካከል፡፡ የደንበኞች አያያዝ  መመሪያው ከጆርጅ ኦርዌል ዘ አኒማል ፋርም  የተቀዳ ነው የሚመስለው፡፡ “ሁሉም ደንበኞች እኩል ናቸው፤አንዳንድ ደንበኞች ግን ከሌሎቹ የበለጠ እኩል ናቸው፡፡” ይሄን መመሪያ የማይቀበል ብዙም ምርጫ የለውም፡፡ (አገርህ ናት በቃ! አለ ገጣሚው)
ወደ ቲቪው የህትመት ዳሰሳ ልመልሳችሁ። ሁለት ልማታዊ ጋዜጠኞች ነበሩ አቅራቢዎቹ። ህትመት ስለሌለ ነው መሰለኝ በቃላቸው ነው ሲያነበንቡ የነበሩት፡፡ አጀንዳቸው ምን መሰላችሁ? ያ የፈረደበት ከምርጫ ጋር የተያያዘ “የቀለም አብዮት” ነው፡፡ በእነ ቬኔዝዌላ፣ ኢራን፣ ቡልጋርያ፣ ዩክሬን ወዘተ…  የተከሰቱ የቀለም አብዮቶችን ተነተኑ፡፡ (የመመረቂያ ጽሁፋቸውን በቀለም አብዮት ላይ ቢሰሩ “A-” ነበር የሚያመጡት!) ማይነሷ የዕውቀት ማነስ አይደለችም። ዋቢና የመረጃ ምንጭ ስለማይጠቅሱ ብቻ ነው፡፡ በየአገሩ የቀለም አብዮት ጠንሳሾቹ ተቃዋሚዎችና የውጭ ሃይሎች እንደሆኑ አስረድተውናል  - በስም እየጠቀሱ። እናም የእንግሊዝና የአሜሪካ መንግስታት በቀለም አብዮቶች ውስጥ ተሳታፊ እንደነበሩ አጋልጠዋል። (ለአፍታ የልማታዊ ጋዜጠኝነት ካባቸውን ወርውረው የኢንቨስቲጌቲቭ ጆርናሊዝም ካባ የደረቡ መስለው ነበር፡፡) ከእነ አሜሪካ ቀጥሎ እነ ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ ፍሪደም ሃውስ ወዘተ-- በቀንደኛ የቀለም አብዮት ጠንሳሽነት ተጠቀሱ፡፡ (እነ አርቲክል 19፣ሲፒጄ፣አምነስቲና ሌሎች በጊዜ እጥረት አልተጠቀሱም!)
እኔን ትንሽ ግር ያለኝ ምን መሰላችሁ? ጉዳዩ ቢያንስ እኛን በቀጥታ አይመለከተንም፡፡ (የወደፊት ስጋት ካልሆነ በቀር!) እናም ለእነቬኔዝዌላ ተብሎ ከየአገሩና ከየመንግስቱ ጋር ጠብ መጫርን ምን አመጣው? (“ጠብ ያለሽ በዳቦ” እኮ ነው!) በእርግጥ “የቀለም አብዮት” በዚህ ወቅት የተነሳው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ምርጫ በመድረሱ ነው፡፡ የሌሎች አገራት ተሞክሮ የቀለም አብዮት በቀጥታ ከምርጫ ጋር የተገናኘ እንደሆነ ይጠቁማል፡፡ እናም የኢቢሲም ሆነ የኢህአዴግ ስጋት ግልጽ ነው፡፡ (በተለይ እኔ ስጋታቸውን እጋራለሁ!) መፍትሄው ግን ከእነ አሜሪካ ወይም “ፍሪደም ሃውስ” ጋር ጠብ መጫር አይመስለኝም፡፡ (የራስን ቤት መጠበቅ ብቻ ነው!) እውነቴን ነው የምላችሁ---መፍትሄው ያለው እዚሁ ነው (ስጋት ካለ ማለቴ ነው!)
እንዳልኳችሁ--ለሁሉም ነገር መፍትሄው እኛ ጋ ነው (ህዝቡ ጋ ማለቴ ነው!) ህዝቡ ሳይፈልግ ምንም የሚደረግ ነገር የለም፡፡ ህዝብ ከፈለገ እንደ 97 ምርጫ ኢህአዴግን ሙልጩን ያወጣዋል፡፡ ወይም ደግሞ እንደ 2002 ምርጫ ተቃዋሚውን “ኢግኖር” ያደርገዋል፡፡ እናም ኢህአዴግ የቀለም አብዮትና የውጭ ኃይሎች ጉዳይ ራስ ምታት ሊሆንበት አይገባም ባይ ነኝ፡፡ ራስ ምታቱ መሆን ያለበት የህዝቡ ዘርፈ ብዙ አንገብጋቢ ጥያቄዎች ጥያቄ ነው። (ህዝቡ ተቃዋሚውንም ይጨምራል!) የመብራት--ውሃ---ትራንስፖርት---የኑሮ ውድነት--የመልካም አስተዳደር እጦት---የሰብአዊ መብት ጥሰት----የፖለቲካ ምህዳር ስስት---ኢፍትሃዊነት--ወዘተ፡፡ እኒህንና ሌሎች የህዝብ ችግሮችን ዘወትር እየሰማ መፍትሄ ካበጀ  ከስጋት ይድናል፡፡
ያኔ የቬኔዝዌላ የቀለም አብዮት የEBCም ሆነ የኢህአዴግ ስጋት መሆኑ ያከትማል፡፡ እዚያው ራሳቸው ይወጡታል፡፡  በነገራችን ላይ ኢህአዴግ የቀለም አብዮት ለተከሰተባቸው ልማታዊ መንግስታት ሁሉ ጠበቃ ሆኖ እኮ አይችለውም። (ሥራችሁ ያውጣችሁ ቢል ነው የሚሻለው!) መልካም የዳግማይ ትንሳኤ በዓል!

Read 3913 times