Print this page
Tuesday, 21 April 2015 08:14

የፖለቲካ ጥግ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

የአፍሪካ ፕሬዚዳንቶች 5ቱ ውድ ጀቶች

የሞሮኮ ንጉስ አውሮፕላን (ቦይንግ 747)
የሞሮኮው ንጉስ በምቾትና በድልዎት መብረር ማለት ምን ማለት እንደሆነ አሳምረው ያውቃሉ። የሚበሩት የላቀ ምቾትና ውበት እንዳለው በሚነገርለት ቦይንግ 747 ሲሆን የተገዛው በ450 ሚ. ዶላር ነው፡፡ አውሮፕላኑ ባለ ሁለት ፎቅ ነው - ዋናውና የላይኛው ፎቅ፡፡ በዋናው ፎቅ ላይ የስብሰባ ክፍሎች፣ የግል ሲኒማ አዳራሽና ሰፊ የመጫወቻ ስፍራ ይገኛል፡፡ በላይኛው ፎቅ ላይ ደግሞ የፑል መጫወቻዎችና 5 የግል መኝታዎች አሉት፡፡ በአሁኑ ሰዓት በአፍሪካ ምርጡ የፕሬዚዳንት  ጀት ነው- የሞሮኮው መሪ ቦይንግ 747፡፡
የዚምባብዌ ፕሬዚዳንት ጀት (ቦይንግ 767)
የአወዛጋቢው መሪ የሮበርት ሙጋቤ የግል አውሮፕላን፣ ከአፍሪካ ምርጥ የፕሬዚዳንት ጀቶች ዝርዝር ውስጥ መካተቱ አያስገርምም፡፡ ምንም እንኳን ዚምባቡዌ በ10ሩ የአፍሪካ ሃብታም አገራት ዝርዝር ውስጥ ባትገኝም  የፕሬዚዳንትዋ የግል ጀት ግን በአፍሪካ ምድር እጅግ ውድ ከሚባሉት አንዱ ነው፡፡ አውሮፕላኑ የዚምባቡዌ ግብር ከፋይ ዜጎችን 400 ሚ. የዚምባቡዌ ዶላር አላየሁም ብሏል፡፡ ከዚህ ውስጥ አገሪቱ 360 ሚ. ዶላር ያህል እንደምንም የከፈለች ሲሆን የ40ሚ. ዶላር እዳ ግን ይቀርባታል። የአውሮፕላኑ ከፍተኛ ፍጥነት 858 ኪ.ሜ በሰዓት ሲሆን ይሄም ከዓለማችን ፈጣን ጀቶች ተርታ ያሰልፈዋል፡፡ ምቾትና ውበት ለመፍጠር ታልሞ የተሰራው ውስጣዊ ክፍሉም ለፕሬዚዳንታዊ ቤተሰቦች ተስማሚ ያደርገዋል ተብሏል፡፡  
የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት አውሮፕላን (ቦይንግ 737)
እዩኝ እዩኝ የሚወዱት የቀድሞው የናይጄሪያ መሪ፣ በቅርቡ ከሥልጣን ከመውረዳቸው በፊት Eagle One ተብሎ በሚጠራ ቅንጡ አውሮፕላን ሲበሩ ነው የኖሩት፡፡ ቦይንግ 737 የናይጄሪያ ግብር ከፋዮችን 390 ሚ. ዶላር ፈጅቷል፡፡ አውሮፕላኑ ፕሬዚዳንቱ በአየር ላይ ሲሆኑ ደህንነታቸውን  የሚያረጋግጡ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች  እንደተገጠመለት ኤርባስ አስታውቋል፡፡  
የአልጄሪያ ፕሬዚዳንት አውሮፕላን (A340-500)
የአልጄሪያው ፕሬዚዳንት A340-500 የተሰኘውን  ባለ አራት ሞተሮች ግዙፍ የግል ጀት ነው የሚጠቀሙት፡፡ እንዲህ ያለው አውሮፕላን ለወትሮው 150 መንገደኞችን የሚያሳፍር ሲሆን ይኼኛው ለፕሬዚዳንቱ ምቾትና ቅንጦት ታልሞ የተሰራ ነው፡፡ የግል መኝታ ክፍል እንዲሁም ሁሉ ነገር የተሟላለት ሻወር አለው፡፡ A-340 አንዴም እንኳን ሳይቆም እስከ 14 ሰዓታት ድረስ በአየር ላይ መብረር ይችላል፡፡
የሊቢያ ፕሬዚዳንት ጀት (A-340)
የሊቢያ ፕሬዚዳንት ኦፊሴላዊ አውሮፕላን በአብዛኛው የሚታወቀው Afrigiyah One በሚል ስሙ ነው፡፡ አውሮፕላኑ ምቾትና ውበት የጎላበት ሲሆን ድሎት ያላቸው ክፍሎች፣ መኝታ ቤት፣ ሻወሮች፣ ዲቪዲ ማጫወቻዎችና የግል ወጥ ቤት አለው፡፡ ይሄም ትሪፖሊ ላይ ድንገተኛ ችግር ቢፈጠር ፕሬዚዳንቱ በአውሮፕላኑ ውስጥ ለበርካታ ወራት እንዲኖሩ ያስችላቸዋል፡፡ አራት ሞተሮች ያሉት ይሄው A-340 ጄት፤ 411 ሚ. ዶላር እንደፈጀ ይገመታል፡፡ ውስጡም የዘመኑ ቴክኖሎጂ ውጤት በሆኑ መሳሪያዎችና ቁሳቁሶች የተደራጀ ነው  ተብሏል፡፡
(ምንጭ፡ Africa Cradle ድረ ገጽ፤2015)

Read 3592 times
Administrator

Latest from Administrator