Monday, 20 April 2015 15:37

‘ቺክን’ እንኳን በአቅሟ “ሦስት መቶ ሀምሳ…!”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(5 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እንኳን ለዳግማይ ትንሳኤው በሰላም አደረሳችሁማ!
ስሙኝማ… ‘ቺክን’ እንኳን በአቅሟ “ሦስት መቶ ሀምሳ ብር!” የዘንድሮውማ በዛና ግራ አጋባን፡፡ እኔ የምለው…እንዴት ነው እዚህ አገር ነገሩ ሁሉ መላ ቅጡ እንዲህ የጠፋው!
‘ቺክን’ እንኳን በአቅሟ “ሦስት መቶ ሀምሳ ብር!”
እኔ የምለው… የማይጨምር ምንም ነገር ላይኖር ነው!…የእንትናዬ ንጭንጭ ጨምሯል፣ የእንትና አረቄ ግልበጣ ጨምሯል፣ የአለቆች “በብጣሽ ወረቀት እንዳላባርርህ!” ጨምሯል፣ የቦሶች “እኛ ባንሆን ጠኔ ይገድልህ ነበር…” አይነት ነገር ጨምሯል፣ ከእኛ ‘ከትንሾቹ’ እስከ እነሱ ‘ትልልቆቹ’ እብሪት ጨምሯል፣ የኮንዶሚኒየም ዋጋ ጨምሯል…ያልጨመረን ነገር መዘርዘሩ ሳይቀል አይቀርም፡፡
‘ቺክን’ እንኳን በአቅሟ ጨምራ “ሦስት መቶ ሀምሳ ብር!”
ይቺን አሪፍ ቀልድ ስሙኝማ…የዶሮ እርባታ ነው፡፡ እናማ… ሌላ ቦታ የተመታ ሙሉ ለሙሉ ነጭ የእግር ኳስ ግቢው ውስጥ ያርፋል፡፡
ይሄን ጊዜ አንድ አውራ ዶሮ በጩኸት ሴት ዶሮዎችን ይሰበስብና ምን ቢላቸው ጥሩ ነው… “እኔ አቤቱታ እያቀረብኩ አይደለሁም፡፡ ግን በሌሎች የዶሮ እርባታዎች የሚጥሉት ዕንቁላል ምን እንደሚያካክል ራሳችሁ ተመልከቱ…” ብሎ እርፍ፡፡
‘ቺክን’ እንኳን በአቅሟ “ሦስት መቶ ሀምሳ ብር!”
ስሙኝማ…ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…ከጊዜ ጋርና ወደድንም ጠላንም ከሚመጡ የአኗኗር ለውጦች ጋር የሆኑ ነገሮች መለወጥ ያለብን አይመስላችሁም! ቢያንስ፣ ቢያንስ የማንም መጫወቻ ከመሆን እንተርፋለና! እንደ ኮንዶሚኒየም አይነት አኗኗር እየተስፋፋ ሲሄድ… አለ አይደል… የተለመደው ዶሮ መበለት፣ በግ ‘ሸክ ማድረግ፣’ አገር ምድሩን በወይራና በኢራን ዕጣን መሙላት… ምናምን አስቸጋሪ ስለሚሆኑ ባንወድም ልንለውጣቸው የሚገቡ ነገሮች አሉ፡፡
‘ቺክን’ እንኳን በአቅሟ “ሦስት መቶ ሀምሳ ብር!”
እንደኛዋ ጦቢያ… አለ አይደል… በሁሉም ነገር ‘እንደ ልብ’ የሚኮንባቸው አገሮች ምን ያህል እንደሆኑ ይጣራልንማ! ምን ላድርግ… ‘ማነካካት’ ለምዶብን የለ!… ‘መነካካቱ’ ለ“እነሆ በረከት” ነገርዬ ቢሆን እኮ አሪፍ ነው፡፡ ሰውየው…
ሳናረጅ፣ ሳናፈጅ ልጅነት እያለን
መቅረታችን ነው ወይ እንዲህ ተነካክተን፣
አለ አሉ፡፡ ሳታረጁ፣ ሳታፈጁ እንዲሁ ‘ተነካክታችሁ’ አትቅሩማ!
እናላችሁ…ነገረ ሥራችን ሁሉ እየጠፋብን ነው፡፡ ለሰሞኑ የበዓል ዋዜማ የዋጋ መናር (ለአብዛኛዎቹ ነገሮች) ምንም ምክንያት የለውም። ግን መላዋ በጠፋ አገር ‘ምክንያት’ የሚባለውም ነገር ከመዝገበ ቃላት የተፋቀ ነው የሚመስለው፡፡ ሲጮህ… አይደለም ጐረቤት ሊሰማ፣ “ምነው ይሄ በግ እንዳይጮህ ማዕቀብ ተጥሎበታል እንዴ!” የሚያሰኘው ‘በግ ተብዬ’ (ቂ…ቂ…ቂ…) ሁለት ሺህ ስምንት መቶ ብር! በሁለት ሺህ ስምንት መቶ ብር እኮ ለስንት ሳምንት በ‘ባላንስድ ዳየት’ ሰውነትን እፎይ ማሰኘት ይቻላል፡፡
እናላችሁ…ምንም እንኳን እንደ ትንሳኤ አይነቱ ባብዛኛው ከምግብ ጋር የተያያዘ በዓል ቢሆንም…በበዓላት ላይ የሥጋን ነገር ቀነስ አድርገን እየነዳ የመጣውን በግና ፍየል እንደገና እየነዳ እንዲመለስ ማድረግ እስካልቻልን አስቸጋሪ ነው፡፡
‘ቺክን’ እንኳን በአቅሟ “ሦስት መቶ ሀምሳ ብር!” በነገራችን ላይ…ወይ ጥሩ ነገር አይግባህ ብሎኝ እንደሆነ አላውቅም…በዘንድሮ ትንሳኤ በዓል በተለያዩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የቀረቡ ‘ልዩ ፕሮግራሞች’ የጠበቅሁትን ያህል አላገኘሁትም። ምን ይደረግ “አይጣምህ…” ያለኝ ዕድለ…በዓል አልፎ በዓል ሲመጣ ‘ዘ ሴም ኦልድ ስቶሪ’ ሲሆን… አለ አይደል…ትንሽ ይደብራል፡፡
እኔ የምለው…‘ክሬቲቪቲ’ ምን ውሀ በላው! ዘንድሮ ‘ለኩረጃ’ ስንት የሚያመች ነገር ባለበት ያው የተለመደው “ምን ገጠመኝ አለዎት?” አይነት ነገር…አለ አይደል…ይሰለቻል፡፡ እናላችሁ…የልዩ ፕሮግራም አዘጋጆች አዳዲስ ፈጠራ ይዛችሁ ኑልንማ! ‘ስፖንሰር እንዲህ በሽ፣ በሽ በሆነበት ዘመን የፕሮግራም ጥራት ላይ አለማተኮርም ቀሺም ነገር ይሆናል፡፡
ሀሳብ አለን…ሽልማቶቹ ሁልጊዜ በጎችና የውሀ ማጣሪያዎች ምናምን ብቻ ከሚሆኑ…አለ አይደል… ለምሳሌ… “የአራት ዓመት የዲ.ኤስ.ቲቪ የደንበኝነት ክፍያ…”፣ “በአትክልት ተራ የሦስት ዓመት ሙሉ የሽንኩርት፣ የቃሪያና የቲማቲም ወጪ…”፣ “በእንትን ፎር ስታር ሆቴል ለዘጠኝ ወር ለሁለት ሰው ሙሉ የምግብና የአልጋ አገልግሎት…”  “የሁለት ዓመት የመብራት፣ የውሀና የስልክ ክፍያ…” ምናምን የሚባሉ ሽልማቶች ይካተቱልንማ! (ብቻ… የሚቀጥለው በዓል ይድረስ እንጂ የበዓል በጀቴን በኤፍ.ኤም. ሽልማት ካላሟላሁማ!)
ስሙኝማ… ቢራን የማይጠጣ ሰው እንኳን ዘንድሮ ቢራ ቢጠጣ አይገርምም፡፡ አሀ…የምር እኮ በማስታወቂያና በስፖንሰርሺፕ ‘ቢር ዋር’ ምናምን አይነት ነገር ያለ ነው የሚመስለኝ፡፡ ሀሳብ አለን… ቢራዎች… “ምርጥ ቢራ ጠርሙሱ ሁለት ብር ከሽልንግ…” ምናምን የሚል ውድድር ውስጥ ይግቡልንማ!
እናላችሁ… የሚቀጥለው ለአቅመ ስፖንሰርሺፕ የሚያበቃ በዓል ይቃረብ እንጂ…የሆነ “እንደ ጥላሁን መዝፈን እችላለሁ…” ምናምን ብዬ ለሞራሌ ወይ የሺህ ብር በግ፣ ወይ 42 ኢንች ፍላት ስክሪን ቴሌቪዥን የማገኝበትን ዘዴ ለመቀየስ እየሞከርኩ መሆኑን አሳውቃለሁ፡፡ አይደለም በሥራ ላይ ያሉት ኤፍ ኤሞች… “ወደፊት ሊኖሩ ይችላሉ…” የምላቸው ኤፍ፡ኤሞች አይቀሩኝም፡፡ (ሰሞኑን ጠላ አበዛሁ እንዴ! ጠላ እየተጎነጨሁ  (ስርዝ የራሴ) ኮምፒዩተር ላይ እየተየብኩ መሆኑን ሳሳውቅ ሁሉ ሰው እውነቱን እንዲያወጣ በማበረታታት ነው፡፡ ቂ…ቂ…ቂ… እንትና… ቅዳሜ ዕለት ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ከምናምን የደወልክልኝ ምን ‘እየተጎነጨህ’ ነበር?)
አንዱ ለጓደኛው ምን ይለዋል መሰላችሁ… “የዶሮዎች ነገር ሁልጊዜ ይገርመኛል…” ይላል። ጓደኝዬውም… “ለምንድነው የሚገርምህ?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ሰውየው ምን አለ መሰላችሁ… “ገና ሳይፈጠሩ የሚበሉ እንሰሳት ቢኖሩ ዶሮዎች ናቸው፡፡” እኛማ… አለ አይደል… ዘንድሮ ዶሮዎቹ ‘ተፈጥረውም፣ ሳይፈጠሩም’ ኪሳችንን የዩክሬይን ጦር ሜዳ እያስመሰሉብን ነው የተቸገርነው፡፡
‘ቺክን’ እንኳን በአቅሟ “ሦስት መቶ ሀምሳ ብር!”
እናላችሁ…የምር ራሳችንን መለስ አድርገን ማየት ያለብን ጊዜ ነው፡፡ “መቼም የፈለገው ይምጣ እንጂ በዓልን በባዶ ቤት አላሳልፍም…” እያልን ፈራንካችን በጠራራ ጸሀይ ‘በሱናሚ’ መወሰድ የለበትም፡፡ (‘ሱናሚ’ ያልኩት ለማጋነን እንጂ… የእኛን ገንዘብማ ቆስጣ እንኳን የማታወዛውዝ ነፋስ ይዛው እንደምትሄድ ‘ጠፍቶኝ’ አይደለም፡፡)
እናላችሁ…ዋጋ ጭማሪዎች… አለ አይደል… ምክንያታዊ ሲሆኑ… “እነሱም ምን ያድርጉ…” እንላለን፡፡ ኮሚክ እኮ ነው… ቀደም ባሉት ጊዜያት በዋዜማው… “መሸት ሲል ይቀንሳል…” ይባል እንዳልነበር ዘንድሮ እየጨለመ ሲሄድ ጭራሹኑ እየባሰበት ይሂድ!  
‘ቺክን’ እንኳን በአቅሟ “ሦስት መቶ ሀምሳ ብር!”
ዛሬ ተበልቶ ነገ ሆድ ባዶ ለሚሆነው ነገር… አለ አይደል… የአበዳሪ ሲሳይ መሆንም አሪፍ አይደለም። የብድር ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…
እሱዬው እሳቸው ዘንድ ይሄድና… “ጌታየ፣ እ… እ…ምን መሰለዎት…”  ምናምን እያለ ሲንተባተብ እሳቸው… “ምን ሆነህ ነው፣ ለምን በደንብ አትናገርም?” ይሉታል፡፡ እሱም፣
“ምን መሰለዎት፣ እንዲሰጡኝ…እንዲሰጡኝ…” ሲል ያቋርጡትና…
“ውሰዳት፣ ፈቅጄልሀለሁ፡፡ ውሰዳት… እንደውም የትራንስፖርቱን እኔ እከፍላለሁ…” ይሉታል፡፡ እሱም ግራ ይገባውና… “ጌታዬ አልገባኝም፣ ውሰዳት ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?” ይላል፡፡ እሳቸውም… “ልጅህን ለሚስትነት ስጠኝ፣ ላግባት አይደል እንዴ ያልከኝ…” ይሉታል፡፡ እሱም…
“ኧረ አይደለም ጌታዬ፣ እኔ እንዲሰጡኝ ማለት…እንዲያ…መቶ ብር እንዲያበድሩኝ ልጠይቅዎት ፈልጌ ነው…” ይላል፡፡ እሳቸው ምን ቢሉ ጥሩ ነው…
“መቶ ብር! መቶ ብር አበድረኝ ነው ያልከው? የት አውቅህና ነው መቶ ብር የማበድርህ?” ብለውት እርፍ!
አንዳንድ ገና ‘ቤት ውስጥ’ ያላችሁ እንትናዬዎች… አለ አይደል… ‘ፋዘር’ ከመቶ ብርና ከእናንተ ለየትኛችሁ ‘እንደሚንገበገቡ’ አጣሩማ፡፡
‘ቺክን’ እንኳን በአቅሟ “ሦስት መቶ ሀምሳ ብር!”
ሰውየው ምን የመሰለ የዶሮ ጥብስ ይቀርብለታል፡፡ እናላችሁ ምን ይላል…
“ይቺን ዶሮ እንኳን አልበላም፡፡”
“ለምንድነው የማትበላው! ምን ጎደላት?” ሲሉ ይጠይቁታል፡፡
“በመፈልፈያ ማሸን የተፈለፈለች ነች፣” ይላል፡፡
“በመፈልፈያ ማሽን መፈልፈሏን በምን አወቅህ?” ይሉታል፡፡ ምን ቢል ጥሩ ነው…
“እናት የፈለፈለቻት ብትሆን ኖሮ ሥጋዋ ይሄን ያህል አይጠነክርማ!” ብሎ እርፍ፡፡ (እንትና… ያቺ “ምንችክ ያለች ነች…” የምትላት እንትናዬ… በእናት ‘ብሬስት ሚልክ’ ማደግ አለማደጓን አጣራማ!)
‘ቺክን’ እንኳን በአቅሟ “ሦስት መቶ ሀምሳ ብር!”
መልካም የዳግማይ ትንሳኤ የሳምንት መጨረሻ ይሁንላችሁማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3458 times