Monday, 20 April 2015 14:12

በስደተኞች ላይ የተዘመተባት ደቡብ አፍሪካ

Written by 
Rate this item
(22 votes)

 ሶስት ኢትዮጵያውያን በጥቃቱ ህይወታቸው አልፏል
- ብዙዎች ንብረታቸውን ተዘርፈዋል፣ በእሳት ተለብልበዋል
“ስደተኞችን በጉያችን ይዘን የምናባብልበት ጊዜ ማብቃት አለበት!” - የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ልጅ
“ስደተኞች ጓዛቸውን ጠቅልለው ወደመጡበት መመለስ አለባቸው!” - የዙሉ ንጉስ ዝዌሊቲኒ  
    ከሶስት ሳምንታት በፊት...
እትብታችን በተቀበረባት አፈር ላይ የሌሎች አገራት ዜጎች ተደላድለው ተቀመጡ፣ የዕለት እንጀራችንን ነጠቁ፣ ሃብት አፈሩ በሚል ሰበብ የተበሳጩ ደቡብ አፍሪካውያን ጎበዛዝት፣ በቁጣ ነድደው ወደ አደባባይ ወጡ። ቆንጨራቸውን ይዘው፣ ከላይ እስከ ታች ታጥቀው፣ ደም ሊያፈስሱ ተንደረደሩ፡፡
ለአመታት ጊዜ እየጠበቀ ሲፈነዳ የቆየውና ከወራት በፊት በሶዌቶ ዳግም የተቀሰቀሰው የጥላቻ መንፈስ ያደረባቸው እነዚህ ደቡብ አፍሪካውያን፣ በኢስፒንጎና ቻትስዎርዝ ከተሞች የሚገኙ የውጭ ዜጎችን ሱቆችና ግሮሰሪዎች በእሳት አነደዱ፡፡ ከእሳት የተረፉትም ዘረፉ፡፡
ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ፤ ጥፋቱን ለማስቆም የፓርላማ አባላትንና ሚኒስትሮችን የያዘ ግብረ ሃይል አቋቁመው እየሰሩ እንደሚገኙ ቢያስታውቁም፤ ይህ ነው የሚባል ለውጥ አልታየም፡፡ የአገሪቱ ፖሊስ ይህንን የጥፋት እሳት ለመግታት ደፋ ቀና ሲል ቢሰነብትም አልተሳካለትም፡፡ ቁጣና ጥፋቱ በያቅጣጫው መሰራጨቱን ቀጠለ፡፡ ወደ ክዋማኩታ... ወደ ኡምላዚ... ወደ ሌሎች የደቡብ አፍሪካ ከተሞች ተዛመተ፡፡ አገሬው ስደተኛውን እያሳደደ ማጥቃቱን ገፋበት፡፡ ሰርቼ ሰው እሆናለሁ ያሉ በሺዎች የሚቆጠሩ የሌሎች አፍሪካ አገራት ስደተኞች፣ ከጥፋቱ ለማምለጥ በየአቅጣጫው ተበተኑ፡፡ ላባቸውን አፍሰው ያፈሩትን ሃብትና ንብረት ታግለው ለማዳን የደፈሩ ጥቂቶችም፣ ከሞት ጋር ተፋጠጡ፡፡
የአገሪቱ ፖሊስ ግን፣ ራሳቸውን ከጥቃት ለመከላከል በቡድን የተንቀሳቀሱትን እነዚሁ ስደተኞች ሊያግዛቸው አልፈለገም፡፡ ይልቁንም ባለፈው ረቡዕ በአስለቃሽ ጭስ በተናቸው፡፡
ባለፈው ሳምንት አርብ፣ ምሽት ላይ...
የውጭ አገራት ስደተኞችን ለማጥቃት የወጡት ደቡብ አፍሪካውያን፣ ፊታቸውን ከደርባን በስተ ደቡብ ወደምትገኘው ኡማልዚ ከተማ አዞሩ፡፡ በከተማዋ የሚገኙ የስደተኞች ሱቆችን በእሳት አቀጣጠሉ፡፡ በሱቆቻቸው ውስጥ እያሉ በድንገተኛው የእሳት ወላፈን ከተለበለቡት የውጭ አገራት ስደተኞች መካከል፣ ሁለቱ ወንድማማች ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡ አንደኛው በደረሰበት ቃጠሎ ለሞት ተዳርጓል፡፡
የያዝነው ሳምንትም በደቡብ አፍሪካ ለሚገኙ ስደተኞች የመከራ ሆኖ ቀጥሏል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ ምሽት...
ይባስ ብሎም የአገሪቱ መሪ ጃኮብ ዙማ ወንድ ልጅ፣ የውጭ አገራት ዜጎችን በጉያችን ይዘን የምናባብልበት ጊዜ ማብቃት አለበት ሲል አፍ አውጥቶ በመናገር ጥፋቱን የባሰ የሚያቀጣጥል ድርጊት ፈጸመ፡፡ የፕሬዚዳንቱ ልጅ ይሄን ባለባት ምሽት፣ አገሬው ለባሰ ጥፋት ታጥቆ ተነሳ፡፡ የደቡብ አፍሪካዋ የወደብ ከተማ ደርባን ጎዳናዎች፣ ስደተኞችን ለማጥፋት ቆርጠው በተነሱ፣ እሳትና ስለት በታጠቁ ዜጎች ተጥለቀለቁ፡፡ በከተማዋ ጥፋት ሆነ፡፡
በርካቶች ራሳቸውን ከሞት ለማዳን ድቅድቁን ጨለማ እየሰነጠቁ፣ እግራቸው የመራቸውን አቅጣጫ ተከትለው ሮጡ፡፡ አሶሼትድ ፕሬስ ከትናንት በስቲያ እንደዘገበው፤ ከሁለት ሺህ በላይ ስደተኞች በፖሊስ ጊዚያዊ መጠለያ ካምፖች፣ በስታዲየሞችና በተለያዩ የመንግስት ተቋማት ተጠለሉ፡፡
በዚህ የጥፋት ዘመቻ፣ ሰሞኑን ብቻ የ14 አመት ዕድሜ ያለውን ብላቴና ጨምሮ ሁለት የውጭ አገራት ዜጎችና 3 ደቡብ አፍሪካውያን ለህልፈተ ህይወት ተዳርገዋል፡፡ ፖሊስም በዚህ የጥፋት ዘመቻ ተካፍለዋል ያላቸውን 74 ያህል ሰዎች በቁጥጥር ውስጥ ማዋሉን አስታውቋል፡፡
በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵውያን ኮሚኒቲ መሪ ኤፍሬም መስቀሌን ጠቅሶ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ባለፈው ማክሰኞ እንደዘገበው፣ ባለፈው አርብ ሱቁ በእሳት የጋየበትን ግለሰብ ጨምሮ 3 ኢትዮጵያውያን በጥቃቱ ህይወታቸው አልፏል፡፡
ይህንን የዘረኝነትና የጥፋት ዘመቻ ለመቃወም ያለመና 10 ሺህ ያህል ሰዎች የተሳተፉበት ሰልፍ በደርባን ከተማ ተካሂዷል። ማላዊ ባለፈው ረቡዕ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ዜጎቿን ለማውጣት መዘጋጀቷን ስትገልጽ፣ ሞዛምቢክም በበኩሏ፤ ከደቡብ አፍሪካ በሚያዋስናት ድንበር አካባቢ የስደተኞች መሸጋገሪያ ካምፕ ማዘጋጀቷን አስታውቃለች፡፡
እ.ኤ.አ በ2008 ሶዌቶ ውስጥ በተቀሰቀሰ ተመሳሳይ ጥቃት፣ ከ62 በላይ የሌሎች አገራት ዜጎች ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ ከሰሞኑ የተከሰተውን ጥፋት ያቀጣጠለው ዝዌሊቲኒ የተባሉ የዙሉ ንጉስ የተናገሩት ንግግር ነው እንደተባለ ጠቁሟል፡፡
እኒሁ ተሰሚነት ያላቸው ንጉስ ባለፈው ወር ስደተኞች ወደየአገራቸው መመለስ አለባቸው ብለው ተናግረዋል በሚል ወቀሳ እየቀረበባቸው እንደሆነ ዘገባው ገልጾ፣ ይሄም ሆኖ ንጉሱ ግን እንዲህ ብለው አለመናገራቸውን በመግለጽ፣ ወቀሳውን ማጣጣላቸውን አክሎ አስታውቋል።
በተለይም ኢትዮጵያውያንና ሶማሊያውያንን ታላሚ አድርጎ የተጀመረው የዘረኝነት ጥቃት፣ አሁን ወደ ሁሉም የአፍሪካ አገራት ስደተኞች መስፋፋቱን የዘገበው ቪኦኤ፤ አገሬው የስደተኞቹን ንብረት በመዝረፍና በእሳት በማጋየት እንዲሁም በጭካኔ በመደብደብ ተግባሩ እንደገፋበት አመልክቷል፡፡
የደቡብ አፍሪካ መንግስት ጥቃቱን ያወገዘ ሲሆን ባለፈው ማክሰኞ የተለያዩ ሚኒስትሮች ንግግር አድርገዋል፡፡ የአገሪቱ ፖሊስ ሚኒስትር ናቲ ንህሌኮ፣ጥቃቱ አፍሪካውያን የራስ ላይ ጥላቻቸውን ያንጸባረቁበት መንገድ ነው ማለታቸውን News24.ዘግቧል፡፡
“አንዳንዶቻችን የውጭ ዜጎች ጥላቻ ነው ብለን ለማሰብ ተቸግረናል፡፡ የተወሰነ የፖለቲካ ችግርን የሚወክልም ይመስለኛል፡፡ የአውስትራሊያ ዜጎች በመንገድ ላይ ሲሳደዱ አታዬም፤ እንግሊዞች መንገድ ላይ ሲሳደዱ አታዩም፡፡” ብለዋል የፖሊስ ሃላፊው፡፡
እሳቸው እንዲህ ይበሉ እንጂ ፓኪስታኖችና ባንግላዲሾች ጥቃት እንደተፈጸመባቸው የሚያመለክቱ ዘገባዎች አሉ፡፡
የመከላከያ ሚኒስትሩ ኖሲቪዌ ማፒሳ-ንኳኩላ በበኩላቸው፤ “የውጭ ዜጎች በመሆናቸው ብቻ ንጹሃን ላይ ጥቃት ከሚፈጽሙ ወገኖች ጋር ደቡብ አፍሪካውያን መተባበር የለባቸውም” ብለዋል፡፡

Read 4689 times