Monday, 20 April 2015 14:09

በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያውያን ስቃይ ቀጥሏል

Written by 
Rate this item
(45 votes)

ኤምባሲው በጥቃቱ ማዘኑን ገልጿል
“ኢትዮጵያውያን ለደቡብ አፍሪካ ህዝብ ሲያደርጉ የነበረውን ድጋፍ አሁን መጠቀሚያ ሊያደርጉት አይገባም”  -  (የፕሬዚዳንቱ ልጅ)
“ከደቡብ አፍሪካ አመራሮች ጋር እየተገናኘን ችግሩን ለመፍታት እየሰራን ነው”  - (ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፤ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር)

ሰሞኑን በደቡብ አፍሪካ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላይ እየተወሰደ ያለው የጥቃት እርምጃ ተባብሶ የቀጠለ ሲሆን በርካታ ኢትዮጵያውን ስደተኞች የጥቃቱ ሰለባ እየሆኑ መምጣታቸውን ምንጮች ጠቆሙ፡፡ ድርጊቱን የሚቃወሙ ሰላማዊ ሰልፎች እየተካሄዱ ሲሆን ጥቃቱ አሁንም እልባት አለማግኘቱንና ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ስደተኞች በከፍተኛ ስጋት ላይ እንደሆኑ እነዚሁ ምንጮች ገልፀዋል፡፡
እስከአሁን የሶስት ኢትዮጵያውያንን ህይወት የቀጠፈውና የብዙዎችን ሰርቶ የመኖር ተስፋ ያጨለመው የሰሞኑ የደቡብ አፍሪካ ጥቃት፣ አድማሱን እያሰፋና እየተባባሰ ሄዷል የሚሉት ኢትዮጵያውያኑ፤ ጥቃቱ እንዳይፈፀም የሚያደርግና ስጋታችንን የሚቀንስ ምንም አይነት እርምጃ በአገሪቱ መንግሥትም እየተወሰደ አይደለም ብለዋል፡፡ የአገራችን መንግስት ለጉዳዩ የሰጠው ትኩረት አነስተኛ ነው ሲሉ ወቅሰዋል፡፡
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ ልጅ ኤድዋርድ ዙማ፤ ጥቃቱን አስመልክቶ በሰጠው ቃለ ምልልስ፤ እርምጃው አግባብ መሆኑን ጠቁሞ ጥቃቱ መወሰድ ያለበት በአፍሪካውያን ላይ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ያለምንም ህጋዊ ሰነድ በደቡብ አፍሪካ እየኖሩ ባሉ የውጪ ዜጎች ላይ ጭምር ነው። እነሱን በማባበል ጊዜ ማጥፋት አያስፈልግም፡፡ ቀደም ሲል ስለአደረጉልን ድጋፍ እናመሰግናለን፡፡ ያንን ድጋፋቸውን ግን ለአሁን መጠቀሚያ ማድረግ አይችሉም” ብሏል፡፡
“በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ የውጪ አገር ዜጎች በሙሉ ወደሚመለከተው የመንግስት አካል ሄደው መመዝገብ አለባቸው፤ ምን እናውቃለን… ISISን ወይም አልሻባብን እየረዱ ሊሆኑ ይችላሉ” ሲልም የፕሬዚዳንቱ ልጅ ተናግሯል፡፡
የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ በበኩላቸው፤ በስደተኞቹ ላይ የተፈፀመውን ጥቃቅ አውግዘው “በችግራችን ወቅት ነፃነታችንን እንድናገኝ የእርዳታ እጃቸውን ዘረጉልን እንጂ አላሳደዱንም፤ ይህንንም ማስታወስ ይገባናል” ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ የደቡብ አፍሪካውን ጥቃት አስመልክተው ሲናገሩ፤ በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሙሉ ጊዜውን ለጉዳዩ ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው ከአገሪቱ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትርና ከሌሎች የደቡብ አፍሪካ አመራሮች ጋር ተገናኝተው ችግሩን ለመቅረፍ እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ “ሚኒስትሯ በሁኔታው በጣም እንዳዘኑና እንዳፈሩበት ነግረውናል” ያሉት ዶ/ር ቴዎድሮስ፤ ኢትዮጵያ ለደቡብ አፍሪካውያን ቤታቸው ነች፤ በነፃነት ትግላችን ወቅት ያደረጋችሁልንን ድጋፍ አንረሳውም፤ የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን” ብለውናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
እንደ ኢትዮጵያውያኑ ሁሉ ዜጎቻቸው የሰሞኑ ጥቃት ኢላማ የሆኑባቸው የዚምባቢዌና ማላዊ መንግስታት፣ በአገሪቱ እየተካሄደ ያለውን ጥቃት በማውገዝ ድርጊቱ እንዲቆም የሚጠይቅ ደብዳቤ ለአገሪቱ ኤምባሲ አስገብተዋል፡፡ በማላዊም በዚህ ጉዳይ የተሰባሰበ ቡድን የማላዊ ዜጎች የደቡብ አፍሪካ ምርቶችን ከመግዛት እንዲቆጠቡና በደቡብ አፍሪካ አየር መንገድ እንዳይጠቀሙ ጠይቋል፡፡  
በሌላ በኩለ፤በኢትዮጵያ የደቡብ አፍሪካ ኢምባሲ ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫ፣ የአገሪቱ ፖሊስ ዜጎቹንና የውጭ አገራት ዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅና ጥቃትና ዝርፊያ የሚፈጽሙ ህገወጦችን በቁጥጥር ስር ለማዋል እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡ የአገሪቱ መንግስት በውጭ አገራት ዜጎች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ጥቃት ለማስቆምና ጸጥታን ለማስፈን የተቀናጀ ርብርብ እያደረገ እንደሚገኝም ጠቁሟል፡፡ ይህም ሆኖ ከችግሩ ስፋት አንጻር የበለጠ የተቀናጀና ዘላቂነት ያለው ስራ መስራት የሚገባ መሆኑ ስለታመነበት አዲስ አቅጣጫ እየተቀየሰ መሆኑንም ገልጧል፡፡
ደቡብ አፍሪካውያን በታሪክ አጋጣሚ ከአገራቸው ወጥተው በኢትዮጵያና በሌሎች የአፍሪካ አገራት ይኖሩ እንደነበር ያስታወሰው መግለጫው፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ለደቡብ አፍሪካ የነጻነትና የአመራር ንቅናቄዎች ያደረገውን ድጋፍ ዛሬም በክብር እናስታውሰዋለን ብሏል፡፡
የሁለቱ አገራት ታሪካዊ ትስስር ለወደፊትም ይቀጥላል፤ ለአፍሪካ ልማት እውን መሆን የጀመርነው የጋራ ጥረትም ተጠናክሮ ይቀጥላል ያለው ኢምባሲው፣ በጥቃቱ ህይወታቸውን ላጡ ዜጎች ቤተሰቦች የተሰማውን ሃዘን ገልጾ፣ የቆሰሉትም በቶሎ እንዲያገግሙ ያለውን መልካም ምኞት ገልጧል፡፡

Read 7675 times