Monday, 20 April 2015 14:08

የአለም ባንክ ለ“አፍሪፍሎራ” 90 ሚ. ፓውንድ ሊያበድር ነው

Written by 
Rate this item
(3 votes)

የአለም ባንክ ቡድን አባል የሆነው ኢንተርናሽናል ፋይናንስ ኮርፖሬሽን (IFC) ተቀማጭነቱ በኢትዮጵያ ለሆነው አፍሪፍሎራ ግሩፕ የተባለ የአበባ አምራች ኩባንያ ማስፋፊያ የሚውል የ90 ሚሊዮን ፓውንድ (2ቢ.880ሚ. ብር ገደማ) የገንዘብ ብድር ሊሰጥ መሆኑን አስታወቀ፡፡
ከ9ሺህ በላይ ሰራተኞች ያሉት አፍሪፍሎራ ከአለም ባንክ በሚያገኘው የገንዘብ ብድር የአበባ ምርቱን 60 በመቶ ለማሳደግ፣ ውሃን መልሶ ለመጠቀም የሚያስችል ቴክኖሎጂ ለመገንባት፣ የፈጠረውን የስራ ዕድል ከ50 በመቶ በላይ ለማሳደግና ሌሎች የማስፋፊያ ስራዎችን ለማከናወን እንደሚያውለው ተቋሙ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
አፍሪፍሎራ በአበባ ምርት ዘርፍ የስራ ዕድል በመፍጠር በኢትዮጵያ ቀዳሚው እንደሆነ የጠቆመው የኢንተርናሽናል ፋይናንስ ኮርፖሬሽን መግለጫ፣ በቀጣይም አለማቀፍ የአካባቢና የማህበራዊ ዘላቂነት መስፈርቶችን ባሟላ መልኩ ምርቱን ለማሳደግ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁሟል፡፡
በዝዋይ አካባቢ በሚገኘው የኩባንያው ዋና እርሻ እስከ 40 ሺህ የሚደርሱ ሰዎችን በቀጥታ፣ ከ100 ሺህ በላይ የሚሆኑትን ደግሞ በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ እያደረገ  ሲሆን ትምህርት ቤቶችን፣ ሆስፒታልና ስቴዲየም በመገንባት ማህበራዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝም አስታውቋል፡፡
ኢንተርናሽናል ፋይናንስ ኮርፖሬሽን ባለፈው የፈረንጆች የበጀት አመት ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ለሚከናወኑ የግብርና ቢዝነስ ፕሮጀክቶች 686 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉንም መግለጫው አክሎ አስታውቋል፡፡

Read 2114 times