Monday, 20 April 2015 14:07

የንግድና ሸማቾች ባለስልጣን በሴባስቶፖል ሲኒማ ላይ ክስ መሰረተ

Written by 
Rate this item
(7 votes)

ሲኒማ ቤቱ ህገወጥ የንግድ አሰራርን ይከተላል ተብሏል

የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን አቃቤ ህግ፤ በሴባስቶፖል ኢንተርቴይንመንት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ላይ ክስ መሰረተ። ክሱ የተመሰረተውና የታየው ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ረፋድ ላይ በባለስልጣኑ አስተዳደር ችሎት ሲሆን የባለስልጣኑ አቃቤ ህግ ሴባስቶፖል በፈጸመው ፀረ ውድድር  የንግድ አሰራር ምክንያት ክሱ እንደተመሰረተበት በክስ ቻርጁ አመልክቷል፡፡
ሴባስቶፖል ክስ የተመሰረተበት ኤግዚቢሽን ማዕከል በሚገኘው ሲኒማ ቤቱ አዳዲስ ፊልሞችን ለማሳየት የሚመጡ ፕሮዲዩሰሮችን ፊልሞቻቸው የሚታዩት ኢዮሃ ሲኒማ ላለማሳየት የሚስማሙ ከሆነ ብቻ እንደሆነ በመግለፅና በፊልም ፕሮዲዩሰሮች ላይ ጫና በማሳደር ተገቢ ያልሆነ የንግድ አሰራር እያካሄደ በመሆኑ ነው ይላል የክስ ቻርጁ፡፡
የሴባስቶፖል ኢንተርቴይንመንት ድርጊት በአቅራቢያው የሚገኘው ኢዮሃ ሲኒማ በገበያው የፊልም አቅርቦት እንዳያገኝና ተወዳዳሪ ሆኖ እንዳይቀጥል ብሎም ከገበያ እንዲወጣ የሚያደርግ ፀረ-ውድድር የንግድ አሰራር እንደሆነ በክስ ቻርጁ ያተተው የባለስልጣኑ አቃቤ ህግ፤ ድርጊቱም የፌደራል የንግድ ውድድርና የሸማቾችን አሰራር መብት አዋጅን የሚቃረን በመሆኑ ይህን የሚያደርግበት ምክንያት ምን እንደሆነ ተከሳሹ ድርጅት መልስ ይዞ ለሚያዚያ 8 እንዲቀርብ ቀጠሮ የሰጠ ቢሆንም በዕለቱ የሴባስቶፖል ሲኒማ ባለቤት አርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ “ጊዜው አጥሮኛል” በሚል ምክንያት መልሱን ይዞ አልቀረበም፡፡ በእለቱ ተሰይሞ የነበረው የባለስልጣኑ አስተዳደር ችሎት፤ ተከሳሹ ድርጅት መልሱን ይዞ እንዲቀርብ ለሰኔ 1 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
የኢዮሃ ሲኒማ ባለቤትና ዋና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ አዩ ዓለሙ፤ ሴባስቶፖል ባደረሰባቸው ጫና ላለፉት ሁለት ዓመታት በፊልም እጥረት ከፍተኛ ኪሳራ እንደደረሰባቸው ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል። “እስከዛሬም ሲኒማ ቤቱን ያልዘጋነው በአንዳንድ ደፋርና የመጣው ይምጣ ብለው ፊልማቸውን ኢዮሃ በሚያስገቡ ፕሮዲዩሰሮች ብርታት ነው” ያሉት ሥራ አስኪያጇ ጉዳዩ እዚህ ደረጃ ላይ እንዳይደርስ ላለፉት ሁለት ዓመታት ቢታገሱም እንዳልተሳካ ገልፀዋል፡፡
የሴባስቶፖል ሲኒማ ባለቤት አርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመን ለማነጋገር በተደጋጋሚ ብንደውልም ስልኩ ባለመነሳቱ ሃሳባቸውን ለማካተት አልቻልንም፡፡

Read 3247 times