Tuesday, 14 April 2015 13:01

ስድስት የሚደርሱ አዋጆች ፀደቁ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

   በአፍሪካ ለሚነሱ የሰላምና የፀጥታ ጉዳዮች የተቀናጀ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል የተጠንቀቅ ሃይል ማቋቋሚያ አዋጅ እንዲሁም የዲፕሎማቲክና የሰርቪስ ፓስፖርት ለያዙ ዜጐች የቻይና ቪዛን የሚያስቀር አዋጅን ጨምሮ ሌሎች ስድስት አዋጆች ፀድቀዋል፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጋቢት 24 ቀን 2007 ዓ.ም ካፀደቃቸው አዋጆች መካከል በተደጋጋሚ የሚከሰተውን ድርቅ በዘላቂነት ለማስወገድ የሚያስችል አዋጅና የኪዮቶ ፕሮቶኮልን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጆች ይገኙበታል፡፡
በተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው የምስራቅ አፍሪካ የተጠንቀቅ ሃይል ማቋቋሚያ አዋጅ እንደሚያመለክተው፤ የተጠንቀቅ ሃይሉ ከአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ በሚሰጠው ፍቃድ መሰረት በአፍሪካ ህብረት የሰላምና የፀጥታ ምክር ቤት የሚሰጡትን ግዳጆች እየተቀበለ በፍጥነት ምላሽ ይሰጣል፡፡ የተጠንቀቅ ሃይሉ ዋና መቀመጫውና የስልጠና ማዕከሉ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚሆንም አዋጅ አመልክቷል፡፡ በአምስቱ የአህጉሩ ቀጠናዎች በሚገኙ አገሮች ውስጥ ካሉ ፖሊሶች፣ ወታደሮችና ሲቪሎች በተውጣጡ አባላት የሚዋቀረው የተጠንቀቅ ኃይሉ የሚያከናውናቸው ተግባራት በአፍሪካ ህብረት ከለላ ውስጥ እንደሚሆንና ኢትዮጵያ ለተጠንቀቅ ሃይሉ ሰራዊቶችን የማሰልጠንና አስፈላጊ መሳሪያዎችን የማቅረብ ግዴታ እንደተጣለባት አዋጁ አመላክቷል።
ሌላው ምክር ቤቱ ያፀደቀውና በኢትዮጵያና በቻይና መንግስታት መካከል የተፈረመው ስምምነት፤ የሁለቱ አገራት ዜጐች ያለቪዛ መውጣት መግባት የሚያስችላቸው ነው፡፡ የዲፕሎማቲክና የሰርቪስ ፓስፖርት የያዙ የኢትዮጵያና የቻይና አገራት ዜጐች ያለቪዛ ለሰላሳ ቀናት ወደየአገራቱ መውጣትና መግባት የሚያስችላቸውን ይህንኑ ስምምነትም ምክር ቤቱ አጽድቆታል፡፡ ከምክትል ሚኒስቴር በላይ የሆነ ማዕረግ ያላቸው የማዕከላዊ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናትና ኦፊሰሮች ወይም ከሜጀር ጀነራል በላይ ማዕረግ ያላቸው የመከላከያ ባለስልጣናት ለኦፊሴሊያዊ ሥራ ወደ ሌላኛው ተዋዋይ አገር ድንበር ከመግባታቸው በፊት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ማሣወቅ እንደሚገባቸው በስምምነቱ ላይ ተገልጿል፡፡ የፀጥታ የደህንነትና የጤና ችግሮች በሚከሰቱባቸው ጊዜያት ተዋዋይ አገራት የስምምነቱን ተፈፃሚነት በሙሉ ወይም በከፊል መገደብ እንደሚችሉም ተጠቁሟል፡፡   

Read 2572 times