Tuesday, 14 April 2015 11:24

ህንድ በርበሬ የሚረጭ “አድማ በታኝ ድሮን” ልትጠቀም ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  - “በርበሬን የመረጥነው የከፋ ጉዳት ስለማያደርስ ነው” - የአገሪቱ ፖሊስ
   በሰሜናዊ ህንድ የምትገኘው ኡታር ፕራዴሽ ግዛት ዋና ከተማ የሆነችው የላክኖው ፖሊስ፣ ከአየር ላይ በርበሬ የሚረጩ አነስተኛ አድማ በታኝ ድሮኖችን በስራ ላይ ማዋል ሊጀምር ነው ሲል ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ዘ ኢንዲያን ኤክስፕረስ ጋዜጣን ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ የግዛቷ ፖሊስ ህገወጥ ተቃውሞ የሚያደርጉ ዜጎችን ለመበተን የሚያስችሉና እያንዳንዳቸው 2 ኪሎ ግራም በርበሬ የመጫን አቅም ያላቸው አምስት አነስተኛ ድሮኖችን በስራ ላይ ለማዋል ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡
“ህገወጥ አመጽ የሚያካሂዱ ዜጎችን በርበሬ እየረጨን እንበትናለን፡፡ ይህን ያልተለመደ የአድማ ብተና መሳሪያ ለመጠቀም የመረጥነው፣ በአመጹ ተሳታፊዎች ላይ የከፋ ጉዳት የማያደርስ በመሆኑ ነው፡፡ ህገወጥ ተቃውሞዎችንና የጎዳና ላይ አመጾችን በቁጥጥር ውስጥ በማዋል ረገድ ውጤታማ እንደሚሆንም ተስፋ አለን” ብለዋል ያሻዝቪ ያዳይ የተባሉት የግዛቲቱ ከፍተኛ የፖሊስ ባለስልጣን፡፡
የግዛቲቱ አስተዳደር ባለፈው አመት ባደረገው ሙከራ፤ በርበሬ የሚረጩ ድሮኖች አድማን በመበተን ረገድ ውጤታማነታቸውን በማረጋገጡ፣ ለእያንዳንዳቸው 10ሺህ ዶላር የከፈለባቸውን ድሮኖች በስራ ላይ ለማዋል መወሰኑንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
ህንድ በርበሬ የሚረጩ አድማ በታኝ ድሮኖችን በመጠቀም ከዓለማችን አገራት ቀዳሚዋ እንደሆነችም ዘገባው አክሎ ገልጿል።

Read 3815 times