Tuesday, 14 April 2015 08:44

ስብና መዘዙ!

Written by 
Rate this item
(8 votes)

      የሰውነት ክብደት እንዲጨምር ከሚያደርጉት ምክንያቶች መካከል ሰውነታችን ከሚያስፈልገውና መጠቀም ከሚችለው በላይ ካሎሪ መውሰድ ዋንኛው ነው፡፡ አንድ ሰው ለዕለታዊ እንቅስቃሴ የሚበቃውን ያህል ካሎሪ ከሚመገባቸው ምግቦች ውስጥ ማግኘት ይኖርበታል፡፡ ወደ ሰውነቱ ውስጥ የሚያስገባው የካሎሪ መጠን በዕለታዊ እንቅስቃሴው ከሚጠቀምበት በላይ ሲሆን ግን በተለያዩ የሰውነት ክፍሎቹ ውስጥ እየተጠራቀመ ይሄድና ውፍረትን ያመጣል፡፡ በእርግጥ የሰውነት እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ የአስተዳደግ ሁኔታና በዘር መውረስ ለውፍረት መንስኤ እንደሆኑ ይታወቃል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ጭንቀት፣ ድብርት፣ የመንፈስ መረበሽ፣ የሆርሞን መለዋወጥ፣ ለተለያዩ ህክምናዎች የሚወሰዱ መድሃኒቶች ለውፍረት መባባስ አስተዋጽኦ ከሚያደርጉ ነገሮች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የአመጋገብ ሥርዓት እንደዚሁ ለውፍረት መባባስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ ጮማና ስብ የበዛባቸውን ምግቦች መመገብ ውፍረትን ከማባባሱም በላይ ለተለያዩ የጤና ችግሮች ይዳርጋል፡፡
የስብና ቅባት ነክ ምግቦች ጣጣ
ከፍተኛ የክብደት መጨመርና ይህንኑ ተከትሎ የሚመጡ የተለያዩ የጤና ችግሮች፤
የወገብ ህመም ፣ የአጥንት መሳሳትና ስብራት እንዲሁም የአጥንት መገጣጠሚያዎች ህመም፤
ቦርጭ ይህም ለልብና ሌሎች ተጓዳኝ የጤና ችግሮች ይዳርጋል፤
አንዳንድ የካንሰር ህመሞች በውፍረት ሳቢያ የመከሰት /የመባባስ እድል አላቸው፤
የወር አበባ መዛባትና የሃሞት ከረጢት ጠጠር፤
የደም ግፊት፣ የስኳርና የኮሌስትሮል መብዛት ችግሮችም በቅባትና ስብ መንስኤነት የሚከሰተው የውፍረት ችግር ውጤቶች ናቸው፡፡ 

Read 7605 times