Tuesday, 14 April 2015 08:26

‘ፍቅር ሲጠና ቆሎ ያጓርሳል…’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(5 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እንኳን ለብርሀነ ትንሳኤው በሰላም አደረሳችሁ!
ቀለልና ዘና ያለ፣ በሦስተኛው ቀን የማያነጫንጭና ከራስና ከሌሎች ጋር የማያጣላ በዓል ይሁንልንማ! ኑሮን የማያስጠላ የበዓል ሰሞን ያድርግልንማ!
የምር ግን በዓል ስንቀበል እንዴት እንደሆነ ልብ ብላችሁልኛል? በቃ ምን አለፋችሁ…ድፍን አገር በቁመትም ይሁን በክብደት ቅደም ተከተል ተሰልፎ “ኪስህን ክፈት…” እየተባለ ገንዘብ የተጠቀጠቀለት ነው የሚመስለው፡፡ የዝንቦች ‘ዳንሲንግ ዊዝ ዘ ስታርስ’ ምናምን አይነት ውድድር ሲካሄድበት የነበረው ሱቅ ሁሉ ግፊያ ይሆናል፡፡ እነሱ እኛን እንደሚሉን እኛም እነሱን… “እኔ የምለው ሰዉ ከየት ነው ገንዘብ የሚያመጣው?” እያልን እንተዛዘባለን፡፡ በዛ ሰሞን፣ ገንዘብ ከመቸገሩ የተነሳ… “እኔ የምፈራው ይህች ዓለም የበቃችኝ ዕለት ገመድ እንኳን መግዣ እንዳላጣ ነው…” አይነት ነገር ሊል ጫፍ የደረሰው ሁሉ የበዓል ሰሞን ባለ‘ሳይንቲስቱን’ እያከታታለ ሲመዠርጠው…አለ አይደል… የምትናገሩት ይጠፋችኋል፡፡
በዓልን በጨፈገገ ፊት ከማክበር ያድነንማ!
ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ለበዓል እኮ ቆፍረንም፣ ቧጠንም ቢሆን ‘የልምዳችን አትቀርም፡፡’ ሰዋችን የቆጠባትንም ቢሆን አውጥቶ ‘ከሰው እኩል’ ይሆናታል እንጂ የጎረቤትን የሽንኩርት ቁሌት እያሸተቱ ማን በሩን ዘግቶ ይውላል! ነገርዬው… አለ አይደል… “የማን ቤት ሞቆ የማን ይበርዳል!” አይነት ነው፡፡
ስሙኝማ...በዓላት ሰሞን ኤ.ቲ.ኤሞች አካባቢ ያለውን ግፊያ ልብ ብላችኋል! እናማ…ሰዋችን ሀኪም “ገዝተህ ተጠቀም…” ያለውን አሞክሲሊን ምናምን ለመግዛት ሰባ ሰማንያ ብር ለማውጣት ሲያቅማማ ቆይቶ በዓል ሲሆን ግን ያውም ተጋፍቶ ሺህ ምናምኑን ያወጣል…ያን ያህል ከቀረ ማለት ነው፡፡
ነገርዬው የሚመጣው ከጥቂት ቀናት በኋላ የበዓሉን ሰሞን ስንሸኝ ነው፡፡ ያኔ ጠብ ከቤት ይጀመራል፡፡
“እ! ታዲያ እኔ ሽንኩርት ሆኜ ድስት ውስጥ ልገባልህ ነው!…”
“እና ከየት ላምጣልሽ! የለገደምቢ የወርቅ ማዕድን የእሱ ነው አሉሽ እንዴ!” ምናምን አይነት ‘እሰጥ አገባ’ ይጀመራል፡፡
“አሁን ይሄ ወር እንዴት ሊገፋ ነው!
“አንድ ሊትር ዘይት እንዲህ ይረርብን!”
“አሁን ይሄ ኑሮ ነው…ሦስት ኪሎ ሽንኩርት ለመግዛት ሠላሳ ምናምን ብር ቤቱ ውስጥ ይጥፋ!” ምናምን ይባላል፡፡ (ስሙኝማ…‘እንደ አካሄዷ’ ከሆነ ሽንኩርትም እንደ ‘ዳይመንድ’ ዲታ ሆድ ውስጥ ብቻ ልትገኝ ነው፡፡ ልክ ነዋ… ይልቁንም የምግብ ባለሙያዎቻችን ከ‘ሽንኩርት ነጻ’ የሆነ ሹሮ እንዴት እንደምንሠራ የሆነ ዘዴ ይፍጠሩልንማ…የሹሮ እህልም እንደ ለገደንቢ ወርቅ ሩቅ እስኪሆንብን ድረስ ማለት ነው! (ስለኑሮ መወደድና ‘ፍሬኑ ስለተበጠሰው’ የዋጋ ነገር አገር አቀፍ ኮንፍረንስ ይጠራልንማ፡፡)
እናላችሁ… ስንቀበለው “ሆዴ፣ አንጀቴ…” ያልነውን ነገር ሁሉ ስንሰናበተው “ዓይንህ ለአፈር…” አይነት ነገር ማለት እየለመድነው መጣን መሰለኝ። ቀድሞውኑም ‘የመጀመሪያ ፍቅራችን’ ጣራ ይነካል፤ በኋላም ‘የመጨረሻ ጥላቻችን’ እንዲሁ ጣራ ይነካል። ምን አለፋችሁ… ተመስገኖ መጥቶ ተመስግኖ የሚመለስ ነገር እየጠፋ ነው፡፡
‘ፍቅር ሲጠና ቆሎ ያጓርሳል’ የሚሏት ነገር አለች።
ስሙኝማ… ለምሳሌ ለመጀመሪያ ጊዜ አዲስ እንትናዬ ስትገኝ ያለው ውዳሴ… አለ አይደል… “እንዲች አይነት ቆንጆና ንጹህ ልብ ያላት ሴት ልብ ወለድ ውስጥስ ትገኛለች!” ያሰኛል፡፡  
“የእኔ ጌታ መልኳ በል፣ ጠባዩዋ በል… እንዴት አድርጎ ቢፈጥራት ነው የምታሰኝ ነች፡፡”
ፍቅር ሲጠና ቆሎ ያጓርስ የለ!
ሲጣሉ ደግሞ ምን ይባላል መሰላችሁ… “ብታያት እኮ የሆነች አስጠሊታ፡፡ መልክ የላት፣ ጠባይ የላት… ስጡላ ሰው ይሉሀል እሷ ነች፡፡ ጭራና ቀንድ የሌላት ሰይጣን በላት፡፡”
ያጓረሰ ፍቅር ሲያልቅ ደግሞ ያናክሳል፡፡
ደግሞላችሁ…መሥሪያ ቤት አዲሰ አለቃ ይመጣል፡፡ ገና ከዋዜማው ‘በእሳቸው መጀን’ አይነት ነገር ይጀመራል፡፡
“መሥሪያ ቤታችን ሊያልፍለት ነው፡፡”
“መሥሪያ ቤታችን በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋጣለት ሥራ አስኪያጅ ሊመጣለት ነው…”
“የእንትን ፋብሪካ ሠራኞች ሲወዱት!”
“ሊለቅ እንደሆነ ሲሰሙ ሲላቀሱ ነው የዋሉት አሉ፡፡”
እናላችሁ…ሦስት ወር እንደቆየ… አለ አይደል…ያጓረሰ ፍቅር ማናከስ ይጀምራል፡፡
“ሰውየው ጨረሰን እኮ! ማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ያልጻፈው ለራሱ ብቻ ነው፡፡”
“ለሚያወራው እንኳን ለከት የሌለው! እኔ የምለው ይሄ አይነት ‹ቦካሳ› ምናምን ከየት ነው ያመጡት!”
“አልሰማችሁም… ቢሮ ውስጥ እኮ ነው እንትን የሚለው! ከመሥሪያ ቤቱ ሴቶች የቀረችው አበሩ ነች አሉ፡፡ እሷም የዓመት ፈቃድ ስለወጣች ስላላገኛት ነው!” (ቂ…ቂ…ቂ…)
አዲስ የሂሳብ ክፍል ኃላፊ ይመጣል፡፡
“ለክሩ የሚሞት እንዴት ያለ ታማኝ ሰው መሰላችሁ፡፡ የበፊተኛው እኮ የድርጅቱን ገንዘብ በጠጅ ነው የጨረሰው አሉ፡፡”
“እንኳን የሌላ ሰው ገንዘብ ሊመኝ የራሱን ገንዘብ አውጥቶ ነው የሚሰጠው…” ምናምን እየተባለ ይወራል፡፡
ትንሽ ወራት ቆይቶ ያጓረሰ ፍቅረ ማናከስ ይጀምራል፡፡
“ባንክ እኮ ምንም ገንዘብ አልተረፈም ነው የሚባለው…”
“ቀምቃሚ  ነው አሉ፣ ገንዘባችንን ሁሉ በጠጅ ጨረሰው እኮ…”
“መጀመሪያውኑ እኮ እሱን ገንዘብ ያዥ ይሁን ያለው ማነው! የታወቀ ሞላጫ አይደል እንዴ…” “የሚኖርበት ሰፈር ሴቱን ሁሉ ቅምጥ አስቀምጦ ባለ አበባ ቀሚስና አምበሬ ጭቃ እየገዛ ሲያድል ነው የሚውለው አሉ…” ምናምን ይባላል፡፡
የምር ግን…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የአምበሬ ጭቃ ዘመን ናፈቀንሳ! አምበሬ ጭቃ ቀላል ‘ወጪ ቆጣቢ’ ነች እንዴ! ‘ጆርጂዮ አርማኒ’ የለ፣ ‘ሁጎ ቦስ’ የለ፡ ‘ሻነል’ ምናምን የለ…አምበሬ ጭቃ የገዛ እንትና እኮ… አለ አይደል… ለቄሶች ቢነገርለት ስሙ ቅዳሴ ውስጥ ይገባ ነበር!  
እናላችሁ…ያጓረሰ ፍቅር ማናከስ ሲጀምር እንዲህ ነው፡፡
እሷና እሱ ቆሎ ሲጓረሱ ይከርሙና ቸኮላቱ ሁሉ አመድ፣ አመድ ማለት ይጀምራል፡፡ እናማ…እሷዬዋ ምን ትላለች…
“ለአንተ ያለኝ ፍቅር አልቋል፡፡ እንካ ቀለበትህን። ሰለሞንን ነው የምወደው፡፡”
“ሰለሞን የት ነው ያለው?”
“ምን ልታደርግ… ልትጣላ!”
“ነጻ ባወጣኝ ምን አጣላኝ! ይልቅ ቀለበቱን ስንት እንደሚገዛኝ ጠይቂልኝ፡፡”
እናማ አንዳንዴ ፍቅር ሲበቃው ቀለበት ያሸጣል።
ይቺን ስሙኝማ…ሰውየው ለጓደኛው… “ሚስቴን ልፈታ ነው፣” ይለዋል፡፡ ጓደኝየውም፤
“ለምንድነው የምትፈታት? ትወዳት አልነበር እንዴ!” ሲል ይጠይቃል፡፡
“ተለውጣለች፣ ይኸው አራት ወር ሙሉ አላነሰገረችኝም፣” ይላል፡፡ ጓደኝየው ምን ቢለው ጥሩ ነው፡
“ታዲያ እንዲህ የመሰለች የተባረከች ሚስት ነው የምትፈታው! የእኔዋ እኮ አይደለም በአራት ወር በአራት ቀን የሁለት ዓመቱን ነው የምታወራው…”
ቆሎ ያጓረሰ ፍቅር ሲያናክስ አሪፍ አይደለም፡፡
በዚህ በበዓላት ሰሞን ሁሉም ነገር በልክ ይሁንማ!
በድጋሚ እንኳን ለብርሀነ ትንሳኤው በሰላም አደረሳችሁ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 4706 times