Monday, 06 April 2015 09:27

ሃዩንዳይ “ሾፌር አልባ” መኪኖችን ለገበያ ሊያቀርብ ነው

Written by 
Rate this item
(3 votes)

    ታዋቂው የመኪና አምራች ኩባንያ ሃዩንዳይ ሞተር፤ የሾፌር እገዛ ሳያስፈልጋቸው ሙሉ ለሙሉ በራሳቸው መንቀሳቀስ የሚችሉበት ቴክኖሎጂ የተገጠመላቸውን ዘመናዊ መኪኖች አምርቶ በመጪዎቹ አምስት አመታት ውስጥ ለአለም ገበያ እንደሚያቀርብ አስታወቀ፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመጣው የዓለማችን የአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ የቴክኖሎጂ ውድድር ተፎካካሪ ሆኖ በመዝለቅ ላይ ያለው የደቡብ ኮሪያው የመኪና አምራች ኩባንያ ሃዩንዳይ፣ እነዚህን መኪኖች እ.ኤ.አ እስከ 2020 በገበያ ላይ እንደሚያውል ባለፈው ማክሰኞ ማስታወቁን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ሃዩንዳይ ሞተር፤ ከዚህ በፊትም በተለየ ሁኔታ ባመረታቸው ጄነሲስን የመሳሰሉና እግረኛ ድንገት ወደ መንገድ ሲገባ ያለ ሾፌሩ ትዕዛዝ ፍሬን የሚይዙ ውድ መኪናዎቹ ላይ፣ መሰል ቴክኖሎጂዎችን መግጠሙን ዘገባው አስታውሷል፡፡
የጀርመኑን መርሴድስና የአሜሪካውን ጄኔራል ሞተርስ የመሳሰሉ ታላላቅ የዓለማችን የመኪና አምራች ኩባንያዎች እንዲሁም፤ ጎግልንና አፕልን የመሳሰሉ የቴክኖሎጂው ዘርፍ ፊታውራሪዎች፣ ምንም አይነት የሰው ድጋፍ ሳያስፈልጋቸው ሙሉ ለሙሉ ራሳቸውን ችለው ረጅም ርቀት መሽከርከር የሚችሉ መኪናዎችን ከዚህ ቀደም ማምረታቸውን ዘገባው አስታውሷል፡፡
ይሄም ሆኖ ግን፣ አንዳንድ ተንታኞች ሾፌር አልባ መኪናዎች፣ ከአገራት ጥብቅ የትራንስፖርት ህጎችና አደጋን ለመከላከል ሲባል ከወጡ መመሪያዎች ጋር በተያያዘ በአፋጣኝ ተቀባይነት ያገኛሉ ብለው እንደማያስቡ መናገራቸውን የጠቀሰው ዘገባው፤ እ.ኤ.አ እስከ 2020 አጋማሽ ድረስ ለአለማቀፍ ገበያ ይቀርባሉ የሚል ግምት እንደሌላቸው መግለጻቸውንም አመልክቷል፡፡

Read 3047 times