Monday, 06 April 2015 08:36

በችግሮች የተተበተበው የቢዝነስ አሰራራችን!

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(2 votes)

ኢትዮጵያና የአውሮፓ ኅብረት ቢዝነስ ፎረም፤ መመሪያ አዘጋጁ
   ኢትዮጵያ ከመላው ዓለም (በቢዝነስ መስክ) የብዙ ኢንቨስተሮችን ቀለብ እየሳበች ትገኛለች፡፡ ቻይና፣ ቱርክ፣ ሕንድ፣ አውሮፓ፣ አሜሪካ፣… በርካታ ኢንቨስተሮች እየመጡ ነው፡፡ ከአውሮፓ ኅብረት አገሮች የተውጣጡ 300 ኩባንያዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በኢትዮጵያ ኢንቨስት እያደረጉ ይገኛሉ። ኩባንያዎቹ ባለፉት 10 ዓመታት በውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት (FDI) ከቀዳሚዎቹ ሦስት ደረጃዎች አንዱን ይዘዋል፡፡
እኒህ የአውሮፓ ኩባንያዎች ባለፉት 20 ዓመታት በኢትዮጵያ 13.3 ቢሊዮን ብር ኢንቨስት ማድረጋቸውንና ከማንኛውም የውጭ ኢንቨስተር በላይ ለ450 ሺህ ዜጐች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ከኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኩባንያ የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡ ከእነዚህ ባለሀብቶች ውስጥ ከመቶ 95ቱ በተጨማሪ ኢንቨስት ለማድረግ መወሰናቸውን ወይም እያሰቡበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ይሄ ማለት ግን የቢዝነሱ አሰራር እንደ አውሮፓ ምቹና ዝግጁ ነው ማለት አይደለም፡፡ በአውሮፓ አመቺ የቢዝነስ ሕግ ደንብና መመሪያ እንዳለ ይታወቃል፡፡ እዚህ ደግሞ ልምዱ፣ አሠራሩ፣ መዋቅሩ ገና ነው፡፡ ኋላቀር የቢዝነስ ሕግና ደንብ ነው ያለው፡፡ ይሄ በሥራቸው ላይ ችግር እየፈጠረባቸው ቢሆንም እየተነጋገሩና እየተመካከሩ ለመቀጠል የኢትዮጵያና የአውሮፓ ኅብረት ቢዝነስ ፎረም መሠረቱ እንጂ ተማረው ጥለው አልሄዱም፡፡
ፎረሙ፣ አዲስ አበባ ያሉ የአውሮፓ ኅብረት ተወካዮች ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል የአውሮፓ የሆኑትን ኩባንያዎች ለመደገፍ በአውሮፓ ኅብረት በ2012 የተመሠረተ ሲሆን ዓላማውም ከአባላቱና ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመነጋገርና በመመካከር በኢትዮጵያ ኢንቨስት ላደረጉ የአውሮፓና ሌሎች የውጭ አገር ኢንቨስተሮች ሕጋዊና አመቺ የቢዝነስ አሠራር መፍጠር ነው፡፡ ፎረሙ የመጀመሪያውን የምክክር መድረክ በ2014 በማድረግ የቴክኒክ ጥናት ለማካሄድ ፕሮጀክት ቀርጿል፡፡
ፕሮጀክቱ ባደረገው ጥናት መሠረት፤ በኢትዮጵያ የሚሠሩ ኢንቨስተሮች፤ የታክስ (አስተዳደር) ችግሮችን ጨምሮ በርካታ እንቅፋቶች እንደሚገጥሟቸው አመላክቷል፡፡ ከእነሱም ውስጥ አሁን ያለው ሕግ ዘላቂነት አጠራጣሪ መሆን፣ ባለስልጣናት ውሳኔ የመስጠት መብታቸው እስከምን ድረስ እንደሆነ በግልፅ አለመታወቅ፣ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የውጭ ምንዛሪ ያለመኖር፣ የሥራ ፈቃድ የማግኘት ችግር፣ ሀገር ውስጥ ገቢ፣ ሕጋዊ የሆኑ ጉዳዮች አፈጻጸም ችግር፣ የመሠረተ ልማት እጦት፣ ለኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን ቅድሚያ ያለመስጠት፣ ሙስና እንዲሁም የፋይናንስ ችግሮች ተጠቅሰዋል፡፡ እነዚህ በጥልቀት ሲጠኑ፣ ዋና ዋናዎቹ ችግሮች አራት ናቸው ይላል - ጥናቱ፡፡ እነሱም ታክስ (አስተዳደር)፣ የአስተዳደር ጫና፣ የንግድ ፈቃድና አገር ውስጥ ገቢ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያና የአውሮፓ ኅብረት የቢዝነስ ፎረም ጥናት የተጀመረው ባለፈው ዓመት ሲሆን ዘንድሮ እንደሚጠናቀቅ ታውቋል፡፡ ከጥናቱ ውጤት በመነሳትም በኢትዮጵያ የተሰማሩ የአውሮፓ ኅብረትና የሌላ አገር ኢንቨስተሮች የሚገጥሟቸውን ችግሮች በማወቅና ሊሻሻሉ የሚችሉበትን መንገድ በማመቻቸት ችግር ፈቺ መመሪያ (ሮድ ማፕ) ተዘጋጅቷል፡፡
የጥናቱ ተሳታፊዎች የኢትዮጵያ የታክስ ሲስተም በተለይ ወደ አስገዳጅና ይግባኝ ደረጃ ሲመጣ መሻሻል እንዳለበት ተስማምተዋል፡፡ የታክስ መጠን መናር፣ ቋሚ ያልሆነ ፍተሻ ወይም ብርበራ፣ ተገቢ ያልሆነ የታክስ ሲስተም፣ ያልነበረ ሕግን ወደኋላ ሄዶ ተፈጻሚ የማድረግ አሰራር… እንደችግር የጠቀሱት ተሳታፊዎቹ፤ መጥፎ ሕግ ከባድ ቅጣት ያስታቅፋል ብለዋል፡፡ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሰዎች ችግሩ ምን ያህል እንደሆነ ለማጣራት ያለመፈለግ፣ አዲስ አስገዳጅ ደረጃ ማውጣት፣ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን አንድ ተመሳሳይ ጉዳይ በተደጋጋሚ በመደመር የሚያባክኑት በርካታ ጊዜ… እኒህም የሚጋፈጧት ችግሮች እንደሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ሌላው ተሳታፊዎች በበኩላቸው፤ “የኢትዮጵያ መንግሥት ከመጠን ያለፈ መመሪያ ይከተላል፣ የወረቀት ሥራ በጣም ያበዛል፣ ምንም ነገር የማያልፍ ከመሆኑም በላይ የሕዝቡን ቅሬታ አቀራረብ ውስብስብ አድርጐታል… የተወሳሰቡ መመሪያዎች፣ በጣም የጠበቀ ቁጥጥር፤ የመ/ቤቶች ቅንጅት ማጣት፣ ግልጽ ያልሆነና ተደራራቢ የመ/ቤቶች ኃላፊነትና ሥልጣን፣ የአንዳንድ መ/ቤቶች ብቃት የለሽና የማይገባቸው መሆን… እንደድክመት ተጠቅሰዋል፡፡
በኢትዮጵያ ቢዝነስ ለመጀመርና ለማካሄድ የሚጠየቀው የሥራ ፈቃድ አበዛዝ አሰልቺ መሆኑን ተሳታፊዎቹ ጠቅሰው፤ ፈቃዱን ለማግኘትና ለማደስ የሚወስደው ጊዜም በጣም ብዙ ነው ብለዋል። በየዓመቱ ፈቃድ ማደስ፣ ፈቃድ ለማውጣት የሚጠየቀው ድግግሞሽ፣ ፈቃድ ለማግኘት እርግጠኛ ያለመሆን እንዲሁም የትኛው ቢዝነስ በምን ዘርፍ እንደሚመደብ ያለማወቅ ችግሮች እንዳሉ አስተውለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ጉምሩክና ገቢዎች ባለሥልጣን ችሎታ ማነስ፣ ከአቅም በላይ የመገመት ሲስተም፣ ረዥምና የተንዛዛ ይግባኝ… በኢትዮጵያ ቢዝነስ ውስጥ የታዩ ችግሮች ናቸው፡፡
እነዚህን ሁሉ ችግሮች በመቅረፍ በኢትዮጵያ አመቺ የቢዝነስ ሁኔታ ይፈጥራል የተባለ የሥራ ማቀላጠፊያ     (ችግር ፈቺ) መመሪያ ተዘጋጅቷል፡፡ እንደ ችግር በተነሱ አንዳንድ ነጥቦች ላይ የመንግሥት ባለሥልጣናት የሠራተኛ ድክመትና አቅም ማነስ ካልሆነ በስተቀር ሌሎች የሉም ብለው ሲከራከሩ፣ ኢንቨስተሮች በበኩላቸው “በደንብ አሉ” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የሠራተኛውን አቅም መገንባት እንደሚያስፈልግ ግን ሁለቱም ተማምነዋል፡፡
የመንግስት ሠራተኛ ባጠፋው ኢንቨስተሩ መቀጣት እንደሌለበት፣ አንድ ዕቃ ተገዝቶ አገር ውስጥ ሲገባ ብዙ ወጪዎች ስላሉ የታክስ መሠረቱ መስፋት እንደሚገባው፣ እነዚያ ወጪዎች ካልታሰቡ ግን ኢንቨስተሩ እንደሚከስር እና ሌሎች የተለያዩ አስተያየቶች ተሰንዝረው መንግሥትም ሆነ ኢንቨስተሮች ችግሮችን በጋራ ለማስወገድ ተባብረን እንሠራለን በሚል በጎ መንፈስ ውይይቱ ተጠናቋል፡፡   

Read 1673 times