Monday, 06 April 2015 08:36

አንዳንዴ ገዢ ፓርቲም በምርጫ ይሸነፋል! (ያላመነ ናይጀሪያን ይመልከት)

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(10 votes)
  • በምርጫ ወቅት “None of the above” ከማለት ያውጣን!
  • “በናይጄሪያ ክርስቶስ ምርጫ ቢያካሂድም ነፃና ፍትሃዊ አይሆንም”

  በናይጀሪያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንዴት እንደተነቃቃሁ አልነግራችሁም፡፡ (የቀድሞ የናይጀሪያ ፕሬዚዳንት) በነገራችን ላይ የናይጀሪያን ፓርቲዎች በጣም ነው ያደነቅኋቸው ገዢውንም ተቃዋሚውንም! ምናልባት የተነቃቃሁት የናይጀሪያ ተቃዋሚ ፓርቲ በማሸነፉ ይሆን እንዴ? (ከሆነም እኮ በቂ ምክንያት ነው!) እናላችሁ…ሳምንቱን ሙሉ ስለ ፓርቲዎች መረጃ ሳሰባስብ ነው ያሳለፍኩት (Inspired ሳልሆን አልቀረሁም!)
ይኸውላችሁ… ከኢንተርኔት ላይ የአፍሪካ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሚል ብራውዝ ሳደርግ  “Bizarre Political Parties Around The World” በሚል ርዕስ የአገር ፓርቲዎች ዝርዝር ከች አለልኝ፡፡ እውነትም Bizarre!! (ቅጥ አምባራቸው የጠፉ ፓርቲዎች!) አንዳንዶቹ ስማቸውም ዓላማቸውም ግርም ይላል፡፡ ጥቂቶቹ ቅዠት ይመስላሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ “የምኞት ፓርቲዎች” የሚመስሉ ናቸው፡፡ የሚገርመው ምን መሰላችሁ? ሁሉም ህጋዊ ናቸው - ፈቃድ ያላቸው!!
አያችሁልኝ ልዩነታችንን?... በሰለጠኑት አገር ማበድ ሁሉ ይፈቀዳል!! (የሌላውን መብት ሳይነኩ ነው ታዲያ!) ምን ትዝ እንዳለኝ ልንገራችሁ? ባለፈው ሳምንት ለመንግሥት ሚዲያ የላኩት የቅስቀሳ መልዕክት “ሳንሱር” ተደርጎ ተመለሰብኝ ያለው ተቃዋሚ ፓርቲ! (የእኛኑ ማለቴ ነው!) አዎ … ኢዴፓ ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫ፤ “መንግሥት ብንሆን የታሰሩ ፖለቲከኞችን በሙሉ እንፈታለን” የሚለውን ሃረግ ካላወጣችሁ “የምርጫ ቅስቀሳው አይተላለፍም” ተባልኩ አለ፡፡ ይኸውላችሁ እንግዲህ … ይሄንን እኮ ነው የምላችሁ፡፡ እዚያ (የሰለጠነው ዓለም!) ማበድ ሁሉ ይፈቀዳል (የፖለቲካ ፓርቲ ፈቃድ ሁሉ አውጥቶ ማበድ ይቻላል!)፤ እዚህ ደሞ (ጦቢያ) እንኳን ማበድ መመኘትም ክልክል ነው፡፡ (ምኞት ሳንሱር ይደረጋል!) እንግዲህ ራሱ ኢዴፓ ካሰራጨው መግለጫ መረዳት እንደሚቻለው፤ ፓርቲው ሳንሱር የተደረገበት ሌላ ሳይሆን ምኞቱን ነው፡፡ ከምሬ እኮ ነው … “በምርጫው ተወዳድሬ ባሸንፍና መንግሥት ብሆን የታሰሩ ፖለቲከኞችን እፈታለሁ” ማለት እኮ ንፁህ ምኞት ነው፡፡ (ቅዱስ ምኞት!) እውነት ግን ኢህአዴግ ምኑ አስፈርቶት ነው? ግራ አጋባን እኮ፡፡ (ወይስ “አሸንፋችሁ ላታሸንፉ … አታሳጡኝ!” ማለቱ ነው፡፡)
ቆይ ግን… “እኔ መንግስት ብሆን ወህኒ ቤቶችን በሙሉ ት/ቤት አደርጋቸዋለሁ” የሚል ደፋር ወይም ገገማ ተቃዋሚ ቢመጣ ኢህአዴግን ምን ሊውጠው ነው? ልብ አድርጉ! ተቃዋሚዎቹ ኢህአዴግን እንዲህ አድርግልን አላሉትም፡፡ ቢሉትም በጄ ስለማይል ምኞታቸውን ነው የገለፁት!! አያችሁ …ሚዲያ በመንግስት ሞኖፖሊ ሲደረግ የምታስቡትን ልንገራችሁ ይላል፡፡ የአየር ሰዓት ብቻ ሳይሆን የምትናገሩትንም ሰፍሬ ልስጣችሁ ማለቱ አይቀርም፡፡
እኔ ኢህአዴግን ብሆን ግን… ፈጽሞ ወደ ሳንሱር አልገባም ነበር፡፡ በቃ… ተሟሙቼ የተሻለ ነገር አስባለሁ፡፡ (አንዳንዴ ኢህአዴግ ማሰብ ይደክመዋል ልበል!?) እናላችሁ… የኢዴፓን አጀንዳ በጠራራ ፀሐይ እቀማዋለሁ - ኢህአዴግን ብሆን ማለቴ ነው፡፡ (በፖለቲካ ጨዋታ… የኮፒራይት ህግ የለም!!) እናም…24 ሰዓት ባልሞላ ጊዜ እሱ የተመኘውን  አደርገዋለሁ፡፡ በቃ… የታሰሩ ፖለቲከኞችን በሙሉ እፈታቸዋለሁ፡፡ (ህግንና ፖለቲካን ማጣቀስ ይቻላል!)
የኢህአዴግ ነገር አናዶኝ ወዳላሰብኩት አጀንዳ ገባሁ አይደል? (Sorry… ብያለሁ!) እስቲ ወደ Bizzare የፖለቲካ ፓርቲዎች ላፍታ ልመልሳችሁ፡፡ እናንተ… አንዳንዶቹ እኮ ስማቸው ራሱ ያስፈራል፡፡ ቆይ “ቫምፓየር” ብሎ ፓርቲ ምንድነው? (Horror party?) አንዱ ፖርቲ ደግሞ  “The Surprise Party” ይባላል። በቁንጅና ተወዳዳሪዎች የተቋቋመ የፖለቲካ ፓርቲም አለ - በታላቋ ብሪቴን!! “The Miss Great Britain Party” ብለውታል፡፡ በፖላንድ የቢራ አፍቃሪዎች የፖለቲካ ፓርቲ አለ፡፡ (የአገራቸው ምርጫ ቦርድ ፈረደበት!)
ከሁሉም ትኩረቴን የሳበው ግን “No Candidate Deserves My Vote” (“የትኛውም እጩ ድምፄ አይገባውም” እንደማለት!) የስሙ ርዝመት እኮ የአቋም መግለጫ  ነው የሚመስለው፡፡ በነገራችን ላይ እንዲህ ዓይነቱ ፓርቲ ለእኛም በጣም ነው የሚያስፈልገን። (ብሽቀት የወለደው ፓርቲ ሳይሆን አይቀርም!) የፓርቲው ዓላማ ምን መሰላችሁ? “የሚረባ ፓርቲ አልተፈጠረም፤ ድምፄን ለማንም አልሰጥም” የሚሉ ዜጐች ቤት ውስጥ አኩርፈው እንዲቀመጡ አይፈልግም፡፡ በሆነ መንገድ ንዴታቸውን መተንፈስ አለባቸው፡፡ ብሎ ያምናል፡፡ እናም በምርጫ ወረቀቱ ላይ “None of the above options” (ከቀረቡት ውስጥ የሚሆነኝ የለም እንደማለት!) የሚል አማራጭ የአገሩ ምርጫ ቦርድ እንዲያዘጋጅ ነው የሚታገለው። ድሮ ት/ቤት ጥያቄው ምርጫ  ሲሆን D-none of the above (መልሱ አልተሰጠም እንደማለት) የምትለዋ ትዝ ትለኛለች፡፡ ይሄ መቼም አባሰብን ነው እንጂ ምርጫ ጣቢያ ድረስ ሄዶ “መልሱ አልተሰጠም” ማለት እርግማን ነው! (None of the above ከማለት ያውጣን!!)
አሁን ደግሞ እስቲ የሰሞኑ ዋነኛ የመነጋገሪያ አጀንዳ ወደነበረው የናይጄሪያ ታሪካዊ ምርጫ እንመለስ፡፡ (በግንቦት ምርጫ አለብን አይደል!) በነገራችን ላይ የናይጄሪያው የዘንድሮ ምርጫ በአፍሪካ ታሪክ እጅግ ውዱ ነው ተብሏል (ከፍተኛ ገንዘብ የፈሰሰበት ለማለት ነው!) አያችሁ … ናይጄሪያውን ከኮሮጆ ወደ ኤሌክትሮኒክስ የምርጫ ሥርዓት ገብተው ተገላገሉ (ያለው ማማሩ አሉ!) በዚያ ላይ ምንም ውድ ቢሆን ናይጄሪያን ከብዙ ጥፋት አድኗታል - “ዲጂታል” ምርጫው! ምርጫ ቦርድንም “ገለልተኛ አይደለም” ከሚል ውዝግብ አትርፎታል፡፡ በአጠቃላይ ታሪክ ለውጧልና ቢወደድም ግዴለም፡፡ በዚያ ላይ እኮ አገሪቷ ህዝብ ብቻ ሳይሆን የከበረ ፈሳሽም ባለቤት ናት (ነዳጅ!) ናይጀሪያ በነዳጅ ሃብቷ ከአፍሪካ 1ኛ፣ ከዓለም 4ኛ ናት፡፡ አያያዙን ግን አላወቁበትም፡፡ ናይጄሪያ በሙስናም ከአፍሪካ 1ኛ ሳትሆን አትቀርም፡፡ እናላችሁ… ለምርጫው ብዙ ገንዘብ ብታወጣም አያስቆጭም (ምርጫና ሠርግ እኮ አንድ ነው!)
አንቶኒ ጎልድማን የተባለ ናይጄሪያዊ ከፍተኛ የቢዝነስ አማካሪ ከምርጫው በኋላ ስለጉድላክ ጆናታን ፓርቲ መሸነፍ ተጠይቆ ምን አለ መሰላችሁ? “ገዢው ፓርቲ የተሸነፈበት ብዙ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ዋናው ምክንያት ግን ምርጫው ባለመጭበርበሩ ነው”። የናይጄሪያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት አሉሴንጉን ኦባሳንጆ ደግሞ ምን ቢሉ ጥሩ ነው?  (እሳቸው እንኳ ከምርጫው በፊት ነው!) “በናይጄሪያ ኢየሱስ ክርስቶስም ምርጫ ቢያካሂድ ነፃና ፍትሃዊ አይሆንም!” ድሮ ቢሆን ኖሮ ኦባሳንጆ ልክ ይሆኑ ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን ታሪክ ተለውጧል፡፡
በናይጄሪያ ታሪክ በ30 ዓመታት ውስጥ ያልታየ ክስተት ነው፡፡ በቀድሞው የጦር አዛዥ የሚመራው የናይጄሪያ ተቃዋሚ ፓርቲ “All Progressives Congress” (APC) ጉድላክ ጆናታንን በ “ዝረራ” ነው ያሸነፈው፡፡ (ጊዜው የአፍሪካ ተቃዋሚዎች ነው ልበል?!) በነገራችን ላይ ሁለቱም ተፎካካሪዎች ተባብረው ነው ምርጫውን ከረብሻና ብጥብጥ ያዳኑት! እንዴት አትሉም? ሁለቱም በማህበራዊ ሚዲያ ደጋፊዎቻቸውን ሲያረጋጉ ነበር - ውጤት እስኪገለጽ፡፡ (ብስለት ይሏል ይሄ ነው!)
“ሁሉም ናይጀሪያዊ ብሄራዊ የምርጫ ኮሚሽን ውጤቱን አጠናቅሮ ይፋ እስኪያደርግ ድረስ በትዕግስት እንዲጠባበቅ አሳስባለሁ” በማለት ጉድላክ ጆናታን በፌስ ቡካቸው ላይ ፅፈው ነበር፡፡
የተቃዋሚ ፓርቲው መሪ ጄነራል ቡሃሪም ዝም አላሉም፤ “የአገሬ የናይጄሪያ ህዝቦች፤  ውጤቱ በሙሉ ተጠናቆ ይፋ እስኪደረግ ድረስ በትዕግስትና በንቃት ትጠብቁ ዘንድ እጠይቃችኋለሁ” ሲሉ ደጋፊዎቻቸውን አረጋግተዋል - በትዊተራቸው፡፡
በዚህ ብቻ ግን አላበቃም፡፡ የጀነራል ቡሃሪ ፓርቲ ምርጫውን በ “ዝረራ” ማሸነፉን ካረጋገጠ በኋላ ከፍተኛ የረብሻና የብጥብጥ ስጋት አረብቦ ነበር፡፡ የጉድላክ ጆናታን ደጋፊዎች ሽንፈትን በፀጋ ላለመቀበል ዳር ዳርታ አሳይተው ነበር ተብሏል፡፡ እናላችሁ… ጆናታን ትንሽ የማቅማማት ነገር ቢያሳዩ ኖሮ…፡፡ “ምርጫው ተጭበርብሯል” በሚል ሰበብ አገሪቷን ለመቀወጥ ያቆበቆበ ደጋፊ በሽበሽ ነበር፡፡ ላለፉት 17 ዓመታት ናይጄሪያን በፕሬዚዳንትነት የመሩት ጉድላክ ጆናታን ግን የአሸናፊው ፓርቲ መሪ ጋ ደውለው፤  እንደሰለጠኑት የምዕራቦቹ ፖለቲከኞች “Congratulation!’’ (እንኳን ደስ ያለህ!) አሏቸው (ሊቀጣጠል በነበረው ፍም ላይ ቀዝቃዛ ውሃ ቸለሱበት!)፡፡
የቡሃሪ ፓርቲ ቃል አቀባይ የሆኑት ላይ ሞሃመድ፤ አቡጃ ከሚገኘው ዋና ፅ/ቤታቸው ለሪፖርተሮች በሰጡት መግለጫ፤ “ጆናታን ሽንፈታቸውን በፀጋ ለመቀበል አይፈልጉ ይሆናል የሚል ፍራቻ ነበረን። በወሰዱት እርምጃ ግን ሁሌም በጀግንነታቸው ሲታወሱ ይኖራሉ” ብለዋል፡፡ “አሁን ውጥረቱ በአስደናቂ ፍጥነት ይረግባል” ሲሉም እርግጠኝነት በተሞላ ቃና ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡ እናላችሁ … የ2015 የናይጄሪያን ምርጫ ያሸነፈው የናይጀሪያ ተቃዋሚ ፓርቲ ብቻ አይደለም፡፡ ሁለቱም ናቸው - ተቃዋሚውም ገዢውም ፓርቲ! (በሌላ አነጋገር ምርጫውን ያሸነፈው ህዝቡ ነው!!)
ባለፈው ረቡዕ የዋለውን April 1st (አፕሪል ፉል) ከናይጄሪያ የምርጫ ውጤት ጋር እንደምንም ሊያቆራኙት የሞከሩ የፌስቡክ ፍሬንዶች አልጠፉም። እናም… “የናይጄሪያ ፓርቲዎች ምርጫውንም ውጤቱንም አፕሪል ፉል! እንዳይሉን?!” እያሉ ቀዝቃዛ ፍርሃት ሲለቁብን ነበር፡፡ (ደግነቱ አፕሪል ፉል ቶሎ አለፈ!)
ናይጀሪያ እንግዲህ በዚህም ሆነ በዚያ ታሪክ ሰርታለች፡፡ ኢህአዴግም…ተቃዋሚዎችም… ምርጫ ቦርዳችንም… ምርጥ ተሞክሮ - ምርጥ ትምህርት - ቀስመውበታል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡
ምርጫው ነፃ፣ ሰላማዊና ፍትሃዊ እንዲሆን መወትወትና መትጋት ተገቢ ነው፡፡ የዚያኑ ያህልም ታዲያ በምርጫ ማሸነፍም መሸነፍም እንዳለ ራስን ማስታወስ ተገቢ ነው (ይረሳል እኮ!)፡፡ አያችሁ… አንዳንዴ ገዢ ፓርቲም ሊሸነፍ ይችላል!! (ሟርት ሳይሆን እውነት ነው - Fact!!)
የጦቢያ ፓርቲዎች ምርጫን ፍጥጫ እያደረጉት ተቸገርን እኮ!!! (ዲሞክራሲያዊ ጨዋታ እኮ ነው!)
ይኸውላችሁ አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ ዘመኑ የአፍሪካ ተቃዋሚዎች ይመስላል፡፡ ባለፈው ዓመት (2014 ዓ.ም) በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድ ዓመት ውስጥ 4 ተቃዋሚ ፓርቲዎች ምርጫ አሸንፈው ስልጣን ይዘዋል፡፡ ዘንድሮ ደግሞ በናይጄሪያ!! ተደገመ (ገዢ ፓርቲዎችን ለማስበርገግ እኮ አይደለም)
ይልቅስ ምን አሰብኩ መሰላችሁ?…አንድ ሁለት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለማቋቋም!) (በኋላ እንዳልቆጭ ብዬ እኮ ነው!)

Read 2769 times