Monday, 06 April 2015 08:30

“አንተን ያገባሁ ጊዜ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(9 votes)

እንዴት ሰነበታችሁማ!
እንኳንም ለሆሳእና አደረሳችሁማ!
እንግዲህ የሠርጉም ወቅት እንደገና ደረሰ አይደል! ለሙሽሮች ቢኖርም ባይኖርም መልካም ‘አከንባሎ ሰበራ’ ይሁንላችሁማ! መመኘትን ማን አየብን!     
እሷዬዋ…“ታውቃለህ፣ አንተን ያገባሁ ጊዜ ደደብ ነበርኩ…” ስትለው፤ እሱዬው ምን ቢላት ጥሩ ነው… “እኔ ፍቅር ይዞኝ ስለነበር ደደብነትሽ አልታየኝም ነበር” ብሏት እርፍ!
“አንተን ያገባሁ ጊዜ…” ምናምን ከመባባል ያድናችሁማ፡፡
በቀደም ዕለት የምናውቃቸው ሰዎች ለጓደኛቸው ሽምግልና የሚሄዱበት ቀጠሮ ነበራቸው፡፡ እናላችሁ…ሁለት ጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቷቸው ሁለት ጊዜም የልጅቷ ወላጆች የቤታቸውን በር እየቆለፉ ጠፉባቸው አሉ። ኮሚክ ዘመን እኮ ነው! ምን ቀጠሮ መስጠት ያስፈልጋል! በቃ “አትምጡብን…” ማለት ሲቻል በዛ ዕድሜ ቀጥሮ መጥፋት ምናምን ቀሺም ነገር ነው፡፡ ምን መሰላችሁ…ምክንያታቸው ገና አልታወቀም፡፡ ዘንድሮ እኮ  በየጓዳችን ብዙ ‘ጉድ’ አለ!
በነገራችን ላይ ምንም እንኳን ዘንድሮ የሀበሻ ልጅ ቤተሰቦች በልጆቻቸው ዕድል ላይ የ‘ቬቶ’ ድምጽ የሌላቸው ቢሆንም አንዳንድ ልምዶች ክፋት የላቸውም። ያው አማቾች ምናምን መሆናቸው ስለማይቀር ክብር መስጠቱ ክፋት የለውም፡፡
“አንተን ያገባሁ ጊዜ…” ምናምን ከመባባል ያድናችሁማ፡፡
ሽምግልና የመሄድ ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…ሰዎቹ የልጅቷን አባት ሊያናግሩ ሄደው ይመለሳሉ፡ ‘እጩ ሙሽራ’ ሆዬም…
“አባዬን ምን አላችሁት?” ብላ ትጠይቃቸዋለች። እነሱም…
“ልጅዎትን ለልጃችን በጋብቻ እንዲሰጡን ልንጠይቅ ነው የመጣነው አልናቸው፣“ ይሏታል።
“ምን አላችሁ? በንዴት ጦፎ ቤቱን በጠበጠው አይደል!” ብላ ስትጠይቅ ምን ቢሏት ጥሩ ነው…
“እንኳን ሊናደዱ እግዜሐር ይስጣችሁ ብለው ተራ በተራ መጨመጩን፣” ብለዋት እርፍ!
ልጄ… “መቼ ከቤት ወጥታልኝ የጡረታ ገንዘቤ በበረከተልኝ…” የሚል አባት እንዳለ ማሰብ ጥሩ ነው።
እንትና…“ሚስት እንደመምረጥ ወላጆቿንም መምረጥ የሚቻል ቢሆን አሪፍ ነበር…” ያልከው ምን ያህል ብትማረር ነው! እኔ የምለው…‘የአማቶች የሥራ ኃላፊነት’ ምናምን የሚባል ‘ሰርኩላር’ ነገር ቢወጣ አሪፍ ነው፡፡ ልክ ነዋ…ዘንድሮም እኮ አማቶች የሚረብሹት ትዳር መአት እንደሆነ እንሰማለን፡፡
“አንተን ያገባሁ ጊዜ…” ምናምን ከመባባል ያድናችሁማ፡፡
የምርጫን ነገር ካነሳን አይቀር…ገነት ውስጥ ነው፤ ያኔ አዳምና ሔዋን ብቻቸውን በነበሩበት ጊዜ፤ ያኔ “ሔዋን ብትሄድ ሌላ ሔዋን ትተካለች…” የሚሉት ሲንግል ምናምን ባልተለቀቀበት ወይም ሊለቀቅ ባልታሰበበት ዘመን፡፡ እናላችሁ… አዳምና ሔዋን መስኩ ላይ ቁጭ ብለው ሔዋን ራሷን ትከሻው ላይ ጣል ታደርጋለች፡፡ ድምጿን ለስለስ አድርጋም… “አዳምዬ አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ?” ትለዋለች። እሱም…  
“ጠየቂኝ… ይላታል፡፡
“አዳምዬ፣ ትወደኛለህ?” ትለዋለች፡፡ እሱም ጊዜ ሳያጠፋ፣
“በጣም እንጂ፣” ይላታል፡፡ ከዛም ድምጹን ዝቅ አድርጎ ለራሱ ምን ብሎ ቢያጉረመርም ጥሩ ነው… “ምን ምርጫ አለኝና!”
የሚመረጥ ነገር በጠፋበት፣ ነገሩ ሁሉ ስልቻ ቀልቀሎ፣ ቀልቀሎ ስልቻ አይነት ነገር በሆነበት ዘመን “ከዚህኛው ይሄኛው ይሻለኛል…” የምትሉበት ምርጫ አያሳጣችሁማ። (እንትና… ‘የምትምርጠውን’ ወሰንክ ወይስ እንዲሁ ቴሌቪዥን ባየህ ማግስት… “አንጀቴን አራሱልኝ…” እንዳልክ ልትቀር ነው! ደግሞ፣ እግረ መንገዴን… “ጿሚ ነኝ…” እያልክ የእኛ ሲደርቅ የአንተ አንጀት እንዴት ሊርስ ቻለ! ቂ…ቂ…ቂ… “እኛ አመድ ሲነፋብን እነ እንትና ምነው ወዝ በወዝ ሆኑ!” እንደሚባለው ማለት ነው።)
የምር ግን እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…በብዙ ነገር ምርጫ እያጣን ነው፡፡ ለምን እንደሆነ ያኛውም ይህኛውም “ሲፋቅ እንትን ነው…” አይነት እየሆኑብን ልባችንን ሞልተን…አለ አይደል… “ይሄ ይሻለኛል…” ማለት አልቻልንም፡፡
አንዱን ችግር አንድ ቦታ ስንሸሸው ‘ሻል ይላል’ የተባለው ቦታ ደግሞ ያው ችግር ‘መልኩን ለውጦ’ ይጠብቀናል፡፡ አንዱ ሰው ባህሪው አልስማማ ይለናል። ሻል ይላል ወዳልነው ሌላኛው ሰው ዘንድ ስንሄድ እሱኛው ደግሞ ሌሎች የባሱ ባህሪያት ይዞ እናገኘዋለን፡፡
አንዱ በሆነ ባልሆነው የሚያፈጥና የሚቆጣ አለቃን ሲያወርዱልን “እሰይ!” እንላለን፡፡ የተሻለ ተብሎ የሚመጣው አለቃ ደግሞ በሆነ ባልሆነው የማስጠንቀቂያና የደሞዝ ቆረጣ ደብዳቤ ‘የመጻፍ ሱስ’ ያለበት ሆኖ ቁጭ፡፡
‘የሚመረጥ ነገር’ አያሳጥችሁማ!
ስሙኝማ..ዘንድሮ ነገሬ ካላችሁ እንትናዬዎች ለመመረጥ የሚያደርጉት ፉክክር አንዳንዴ ግርም ይላል፡፡ ከተማችን ውስጥ እያየናቸው ያሉ የአንዳንድ እንትናዬዎች አለባበስ ያኔ ሚኒስከርት መልበስ ጦሰ ያስከትልባት የነበረችውን አዲስ አበባ ሊያስናፍቀን ምንም አይቀረው። አሀ…የቀሚሱና የእንትኑ ጫፍ እኩል ነዋ!
ለመመረጥ የሚደረገውን ነገር ካነሳን አይቀር ከዚህ በፊት ካላወራናት ይቺን ስሙኝማ…እሷዬዋ ዕድሜዋ ገፋ እያለ ሲሄድ… አለ አይደል…በጣም ውድ የሆኑ መዋቢያዎች ትገዛለች፡ እነሱንም እየተቀባባች በቃ ምን አለፋችሁ… ‘ፏ’ ትላለች። እናላችሁ…ላያት ሰው ከዋናው ዕድሜዋ ላይ ‘ትዌንቲ ምናምን’ ቀንሶላት “ባቅላባ ብገዛልሽ ምን ይመስልሻል…” የሚላት አይነት ትሆናለች፡፡
ታዲያላችሁ… አንድ ቀን ለረጅም ሰዓታት ስትኳኳልና ስትቀባባ ቆይታ ወደ ሳሎን ትመጣለች፡፡ አቶ ባልንም… “ውዴ፣ ለምሳሌ እኔን ባታውቀኝ ኖሮ እንዲህ ስታየኝ ዕድሜዬን ስንት ትገምተው ነበር?” ትለዋለች፡፡ እሱም ልክ እንደማያውቃት ከላይ እስከታች ደጋግሞ ያያታል፡፡
“ቆዳሽን ሳየው ሀያ ዓመት፣
ጸጉርሽን ሳየው አሥራ ስምንት ዓመት
ተክለ ሰውነትሽን ሳየው ሀያ አምስት ዓመት ትመስይኛለሽ…” ይላታል፡፡ እሷዬዋም በጣም ከመደሰቷ የተነሳ… “አፌ ቁርጥ ይበልልህ፣ የእኔ ፍቅር። ምን አባቴ ላድርግህ!” ብላ ትጠመጠምበታለች፡፡ ይሄኔ አቶ ባል…
“ቆይ ረጋ በይ…” ይላታል፡፡ “መች ጨረስኩና ነው!” እሷዬዋም ኮስተር ትልና…
“ይኸው ነገርከኝ አይደል እንዴ!” ትለዋለች፡፡ እሱ ሆዬ ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው…
“ነጣጥዬ ነዋ የነገርኩሽ… ገና መች ደምሬ ጨረስኩ!” ብሏት እርፍ፡፡ ‘ሲክስቲ ስሪ’ ሊመጣ ነው እኮ! ይሄ ጂም የሚሉት ነገር የሀያ አምስት ዓመት ኮረዳ ‘ሼፕ’ እየሰጠ ነው ለካ ሴቱ ሁሉ እንዲሀ ያማረበት! “እንትና አሁን ሀያ ስድስት ነኝ የምትለው የሚሌኒየሙ ጊዜ ለህዳር አቦ ሠላሳ አራት ሊሆናት ነው…” ሲባል አልሰማንም ነበር እንዴ!”
እናማ…እንትናዬዎች ተነጣጥሎ የተነገራችሁ ነገር ተደምሮ እስኪመጣ ድረስ አትመኑማ፡፡
“አንተን ያገባሁ ጊዜ…” ምናምን ከመባባል ያድናችሁማ፡፡
እናላችሁ…እንዲህ የሠርጉ ዘመን ሲቃረብ አመራረጡ ላይ አሪፍ መሆን ሳይሻል አይቀርም።
ሰውየው ‘ሾቭኒስት’ ምናምን የሚሉት አይነት ነው። እናላችሁ ሚስት ያገባል…“የእኔ ህጎች” የሚላቸውን ነገሮች ያስቀመጣል፡፡ “እቤት የምመጣው በፈለግሁት ሰዓት ነው፤ ትንፍሽ እንድትይ አልፈልግም፡፡ እኔ እራት ውጪ እበላለሁ እስካላልኩኝ ድረስ ግሩም ራት ሠርተሽ ጠረዼዛው ላይ ማስቀመጥ አለብሽ። በፈለግሁት ሰዓት አደን እሄዳለሁ፣ ከጓደኞቼ ጋር እጠጣለሁ፣ ካርታ እጫወታለሁ… የእኔ ህጎች እነዚህ ናቸው። አስተያየት አለሽ?” ይላታል፡፡ እሷም ምን ብትለው ጥሩ ነው…
“ባልከው ሁሉ እስማማለሁ፡፡ ግን እንድታውቅ የምፈልገው አንተ ኖርክም አልኖርክ እዚህ ቤት ውስጥ ነገርዬውን እነሆ በረከት መባባል የሚቻለው ከምሽቱ አንድ ሰዓት ላይ ነው፡፡” እንዲህ እርፍ ይበለው! ባሎቻችሁ እያመሹ ያስቸገሯችሁ እንትናዬዎች… አለ አይደል… “ከአንድ ሰዓት በኋላ እነሆ በረከት ብትጠይቅ ሻንጣዬን ይዤ ውልቅ ነው…” ምናምን አይነት ነገር በሏቸውማ!
“አንተን ያገባሁ ጊዜ…” ምናምን ከመባባል ያድናችሁማ፡፡
ለስንብት ይቺን ስሙኝማ… ሰውየው ጣልያናያዊ ናቸው፡፡ እናማ… የመጨረሻ ሰዓቷ ደርሳ አልጋቸው ላይ ሆነው ጥሪያቸውን ይጠብቃሉ። ከዛም በጣም የሚወዱት የቸኮላት ሽታ ከምድር ቤት ያውዳቸዋል። በጣም ከመጎምጀታቸው የተነሳ ራሳቸውን መቆጣጠር ያቅታቸዋል፡ እንደምንም ተግተርትረው ከአልጋ ይወርዳሉ፡፡ ደረጃዎቹን እየዳሁና እየተንፏቀቁ ማብሰያ ቤት ይደርሳሉ። ቸኮላቱ ጠረዼዛ ላይ ‘ደረቱን ገልብጦ’ ያዩታል። እንደምንም እየተሳቡ፣ እየተደነቃቀፉ ይደርሱና ተንጠራርተው አፈስ አድርገው ወደ አፋቸው ያደርጋሉ። ይሄኔ ሚስትዬው ይመጡና ምን ቢሉ ጥሩ ነው… “አንተ ሰውዬ ምንድነው የሚያንቀዠቅዥህ! እኔ ያዘጋጀሁት ለቀብርህ የሚመጣውን ሰው መሸኛ ነው እንጂ ለአንተ ነው እንዴ!” አሉና አረፉት! አይ ‘ጥልያን’!
“አንተን ያገባሁ ጊዜ…” ምናምን ከመባባል ያድናችሁማ፡፡

Read 2675 times