Print this page
Saturday, 21 January 2012 10:41

የማርቲን ሉተር የተሀድሶ እንቅስቃሴና የፌስ ቡክ አብዮት “ነፃነት የሰዎች ተፈጥሮአዊ መብት ነው”

Written by  ጥላሁን አክሊሉ
Rate this item
(2 votes)

የጨለማው ዘመን ተብሎ በሚጠራው ከ5ኛው መቶ ዘመን ጀምሮ አለም ከንግድ ግንኙነት፣ ከፈጠራ፣ ከፍልስፍና፣ ከኪነ-ጥበብና ከአርክቴክት ሥራዎች ተገልላ በፀጥታና በዝምታ የተዋጠችበት ዘመን ነበር፡፡ የባዛንታይን፣የሮምና የአክሱም ሥልጣኔ ውድቀት የተከሰተው በዚህ ዘመን እንደሆነ የታሪክ ማስረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ይሁንና በ14ኛው ክ/ዘመን የዓለምን ዝምታ የሰበረው ዝነኛው ተጓዥ ሃጂ ኢብን ባቱታ ከሞሮኮ፣ ታንጊር ከተባለበት ተነስቶ መላውን የሙስሊም አገሮችን በግመልና በመርከብ፣ በእግርና በአህያ ካካለለ በኋላ ወደ ሕንድ፣ ማልዲቪስ፣ ሲሪላክና ቻይና ድረስ ዘልቋል፡፡ እንዲሁም አውሮፓና አፍሪካም ተጉዟል፡፡ ኢብንባቱታ በአጠቃላይ ወደ 120 ኪሎሜትር በ30ዓመት ውስጥ ሲጓዝ፣  ዓለምን በባህል፣ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ እና በሃይማኖት አቀራርቧል፡፡ በጨለማው ዘመን አንቀላፍቶ ለነበረው ዓለምም ትልቅ መነቃቃት ፈጥሯል፡፡

ኢብን ባቱታ የፈጠረውን መነቃቃት ተከትሎም ከ14ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ እስከ 16ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ  ድረስ ጨለማውን ዘመን ሙሉ በሙሉ ያስወገደው የህዳሴው ዘመን (The Renaissance Period) ብቅ አለ፡፡ ይህም ዘመን በጀርመን የህትመት ማሽን የተፈጠረበት፣ በጣሊያን ጋሊሊዮ ጋሌሊ የተባለው ሳይንቲስት ዘመናዊ ቴሌስኮፕን ለዓለም ያበረከተበትን እና የአርት፣ የምህንድስናና የፈጠራ ሥራዎች እንደገና በዓለም ላይ ያበቡበት ዘመን ነበር፡፡ በአጠቃላይ ዛሬ ላለው የዓለም ገፅታ ከፍተኛ መሰረት የጣለው የህዳሴው ዘመን ነበር፡፡ በተለይም  የፕሮቴስታንት ሃይማኖት መሥራች የነበረው ማርቲን ሉተር ኪንግ የሮም ቤተክርስቲያንን ዶግማ በመቃወም ራሱን ከቤተክርስቲያኒቱ ያገለለበት ወቅት ነው፡

በወቅቱ ሊዮ አስረኛ የካቶሊክ ጳጳስ የነበሩ ሲሆን፣የቅዱስ ጴጥሮስ ካቴድራልን  ለማሰራት ከምዕመናን የገንዘብ መዋጮ እንዲሰባሰብ ትዕዛዝ ያስተላለፉበት ጊዜ ነበር፡፡ ምዕመናን በሚያዋጡት ገንዘብ የሀጢያት ስርየት እንደሚያገኙ ቤተክርስቲያኗ ትሰብክ ነበር፡፡ ነገር ግን ሉተር መዳን የአምላክ ጸጋ ሥጦታ እንጂ በውለታ አይደለም በማለት በቤተክርስቲያኒቷ ላይ ተቃውሞ አቀረበ፡፡ 95 የሚጠጋ የተቃውሞ ጥናታዊ ፅሁፎችን በዊተንበርግ ቤተክርስቲያን በር ላይ ለጥፎ ሄደ፡፡

ማርቲን ሉተር በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ላይ ተሃድሶ ለማድረግ የተጠቀመበት ዘዴ፣ በ21ኛው ክ/ዘመን አምባገነን መሪዎችን ከሥልጣን ለመጣል ከተካሄደው ስልት ጋር የሚመሳሰል ነበር ፡፡

ባለፈው ዓመት የፈረንጆች 2011ዓ.ም ገና ከመጥባቱ በፍራፍሬ ንግድ ላይ የተሰማራው የከፍተኛ ትምህርት ምሩቁ የሆነው መሀመድ ቡአዚዝ ሥራውን እንዳይሰራ እንቅልፍ የሆኑበትን ፖሊሶች በመቃወም፣ በራሱ ላይ ቤንዚን አርከፍክፎ በማቃጠል ሕይወቱን ካጠፋ በኋላ በመላው ቱኒዝያ ሕዝብ በቁጣ እንዲነሳ ያደረገ ሲሆን በተለይም የቱኒዚያ ወጣቶች በፌስ ቡክ ድረ-ገፅ ከየቦታው እየተጠራሩ ወደ ቱኒዝ አደባባይ ለመውጣት ሰዓት አልፈጀባቸውም፡፡ ተቃውሞ እጅግ የበረታባቸው ቤን አሊ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ስልጣናቸውን  ብቻም ሳይሆን ቱኒዚያን ጥለው እብስ አሉ፡፡

መሀመድ ቡአዚዝ በራሱ ላይ ያርከፈከፋት ቤንዚን  በቱኒዚያ ብቻ ሳትወሰን  ካይሮ ድረስ በመዝለቅ አገር አማን ብለው ለ30 ዓመታት ግብፅን ሲመሩ የነበሩትን የሙባረክንም አገዛዝ ገርስሳለች፡፡ ወጣት ግብፃውያን እንደ ቱኒዚያውያን በፌስ ቡክ እየተጠራሩ ታህሪሪ አደባባይን ለ18 ቀናት ከጨናነቁ በኋላ ሙባረክ ስልጣን ሊለቁ ችለዋል፡፡ መሀመድ በራሱ ላይ የለኮሳት ቤንዚን አጠቃላይ የአረብ አገራት መሪዎችን በወላፈኗ ብትለበልብም አብዛኞቹ እንደ ቱኒዚያና እንደ ግብፅ የፌስ ቡክ ወዳጆች ባለመሆናቸው አልተጠቀሙበትም፡፡ ነገር ግን በፌስ ቡክ ሳይሆን በጥይት ቡክ የተሰናበቱት ጋዳፊን ጨምሮ በሽር አላሳድንም ሊበግራቸው የሚችለው እንደጋዳፊ ጥይት ቡክ ሊሆን ይችላል ፡፡

ወደ ሉተር ዘመን እንምጣ፤ ከ500 ዓመት በፊት ማርቲን ሉተር የተሃድሶ እንቅስቃሴውን ለማድረግ በራሪ ወረቀቶችን፣ ፓምፍሌቶችን እንዲሁም መንፈሳዊ መዝሙር ያያዙ ቡክሌቶችን ተጠቅሟል፡፡ በቱኒዚያና በግብፅ ወጣቶች በፌስ ቡክ ‹‹ያልሰማህ ስማ›› እየተባባሉ እንደተጠራሩት ሁሉ ሉተርም የህትመት ውጤቶችን እንደማህበራዊ ድረ ገፅ (ፌስ ቡክ) ተጠቅሟል፡፡

ጥልቅ እውቀት እንደነበረው የሚነገርለት ማርቲን ሉተር ኪንግ፤ በዊተንበርግ ቤተክርስቲያን በር ላይ የለጠፈውን 95 የተሃድሶ መልእክት ወደ ጀርመንኛ  በመተርጎም በጥራዝ ወረቀት እና በፓፍሌት መልክ በኑምበርግ፣ በሊፒዚንግ፣ በባሲል እያባዛ አሰራጭቷል፡፡

በተጨማሪም መፅሀፍ ቅዱስን በጀርመንኛ በመተርጎም በመላው ጀርመን  አሰራጭቷል፡፡ ሉተር ለሚያካሂደው መንፈሳዊ አብዮት ጓደኞቹ ወጪውን  በመሸፈን የገንዘብ ድጋፍ ያደርጉለት ነበር፡፡

በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በጀርመን የካቶሊክ አማኝ ነበሩት አያሌ ጀርመናዊያን  ሉተር ያሰራጫቸውን መልእክቶችን አምነው ሊቀበሉ ቻሉ፡፡ ማርቲን ሉተር በሕትመት ውጤቶች ስላገኘው ውጤት ሲገልጽ፣ እጅግ ከጠበቁት በላይ ነው ብሎ ነበር፡፡ በቱኒዚያና በግብጽ ያሉ ወጣቶች በማህበራዊ ድረ ገፅ አማካኝነት በሚለዋወጡት መልክት ለተቃውሞ ሲወጡ ምን ማድረግ  እንዳለባቸው እያንዳንዱን ሁኔታ የሚገልፅ መረጃ ይለዋወጣሉ እንደነበር ሁሉ በማርቲን  ሉተር ዘመንም ሉተር ባሰራጫቸው ብሮሸሮችና ፓምፍሌቶች ላይ ውይይት በማድረግ አንድ አይነት አቋም ለመያዝ ችለዋል፡፡ የተሃድሶ ተከታታዮች የተዛነፈ አቋም እንዳይኖራቸው ሉተር ከፍተኛ ጥረት በማድረጉ መላው ጀርመንን በተሃድሶ ሊያጥለቀልቀው ችሏል፡፡ሉተር ያሳተማቸው ፓምፍሌቶች ወደ ተለያዩ ከተሞች ለማሠራጨት የመፅሀፍት አከፋፋይ በርካታ ቅጂዎች በመያዝ ሲንቀሳቀሱ የያዙትን ፅሁፎች በከተሞች ውስጥ በጩኸት በማስተዋወቅ ሕዝቡ እንዲወስዳቸው ያደርጉ ነበር፡፡ የሉተርን ዓላማ የተቀበሉ በርካታ የሃይማኖት ሰባኪዎች ፓምፍሌቶቹን ይዘው በመንቀሳቀስ የጀርመናውያንን ልብ በፓምፍሌቶቹ ለመማረክ ችለዋል፡፡ ፓምፍሌቶቹ ያልተማሩትንም እንዲጠቅም  ከፅሁፉ ጋር የሚሄድ ምስል ተጠቅሟል፡፡

“sermon on indulgences and grace” የተባለው በጀርመንኛ  የታተመው የመጀመሪያው ፓምፍሌት በ1518 ዓ.ም. ለ14 ጊዜ የታተመ ሲሆን፣ በእያንዳንዱ እትም ደግሞ 1000 ኮፒ የሚጠጋ ነበር፡፡ ከ1520 እስከ 1526 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ 6000 አይነት ፓምፍሌቶች ታትመው ተሰራጭተዋል፡፡ በአጠቃላይ  በመጀመሪያዎቹ የተሃድሶ አመታት ጊዜ ውስጥ ከ6 ሚሊዮን እስከ 7ሚሊዮን ፓምፍሌቶች ታትመዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንድ አራተኛውን ሉተር ያሳተማቸው ሲሆን፣ ቀሪዎቹን  ደግሞ አሳታሚ ድርጅቶች አትመው አሰራጭተውታል፡፡ ሉተር ፓምፍሌቶችን  በስፋት ካሰራጨ በኋላ፣ መፅሀፍ ቅዱስንም ወደ ጀርመንኛ በመተርጎም  አሰራጭቷል፡፡ ነገር ግን ወዲያው የካቶሊክ ቤተክርስቲያንን ቁጣ ቀሠቀሠ፡፡ ቤተክርስቲያኒቱ የሉተርን መፅሀፍ ቅዱስ የሚተካና በካቶሊክ ሀይማኖት  ዘንድ እውቅና ያገኘ ሌላ መጽሀፍ ቅዱስ ሊዘጋጅ እንደሚገባ ወሰነች፡፡ ብዙም ሳይቆይ ሁለት ጀርመንኛ መፅሀፎች ታተሙ፡፡ እንደገና በ1546 ዓ.ም የሮም ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የትሬንት ጉባኤ፣ የመጽሀፍ ቅዱስ ትርጉምን ጨምሮ ማንኛውም ሃይማኖታዊ ጽሁፍ ህትመት በቤተክርስቲያኒቱ ቁጥጥር ሥር እንዲሆን ደነገገ፡፡‹‹ከአሁን በኋላ ቅዱሳን መፅሀፍት… በተቻለ መጠን ትክክል በሆነ  መንገድ ሊታተሙ ይገባል፤ በተጨማሪም ማንኛውም አይነት መንፈሳዊ ጉዳይን የሚመለከቱ መፅሀፍት የደራሲው ስም ሳይፃፍበት ማተምም ሆነ ማሳተም አሊያም የሰበካው ጳጳስ መርምሮ ሳይፈቅድ እንዲህ ያሉ ፅሁፎች መሸጥ ሌላው ቀርቶ መያዝ እንኳ ሕገ ወጥ ተግባር ነው›› በማለት አስታወቀች፡፡

በአካባቢያቸው በሚነገረው ቋንቋ የተረጎሙ መፅሀፍ ቅዱስን ለመያዝ ወይም  ለማሠራጨት  የሞከሩ ሁሉ የካቶሊክ  ቤተክርስቲያን  ገፈት  ቀማሽ  ይሆኑ ነበር፡፡ ማርቲን  ሉተር ኪንግ  ግን በካቶሊክ  ቤተክርስቲያን  መግለጫ ሳይበገር ፓምፍሌቶቹንም ሆነ  መፅሀፍ ቅዱስን በሁሉም ህብረተሠብ  ዘንድ በስፋት እንዲሰራጭ አድርጓል፡፡በአረብ  አብዮት ወቅት የፖለቲካ እንቅስቃሴ መሪዎች( Political activists) አምባገነን መሪዎችን ለመቃወም ሕዝቡን ሲቀሰቅሱ በፌስ ቡክ  ካሰራጩት መልእክት በተጨማሪ ሕዝቡ አደባባይ ከወጣ በኋላ የተቃውሞ መሪ በመሆን ሕዝቡን  የሚቀሰቀስ ንግግር ያደርጉ ነበር፡፡ በተመሣሣይ በሉተር ዘመን በየቦታው በተሠራጩት ፓምፍሌቶች ዙርያ ቤተሠቦች፣ጓደኛሞች እንዲሁም የስራ ባልደረቦች ተሰባስበው ይወያዩበት ነበር፡፡ በርካታ የተሃድሶ አቀንቃኞችም ልክ እንደ ሉተር ሕዝቡን አነቃቅተዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ1924 ዓ.ም በጀርመን የተለያዩ የመሰብሰቢያ አዳራሾች ተከፍተው የስብከት ስራዎች መካሄድ ጀመሩ፡፡ ማርቲን ሉተር በቃላት ካሰራጫቸው ፓምፍሌቶች በተጨማሪ ከመልእክቱ ጋር የሚስማሙ ምስሎችን እንዲሁም መዝሙሮችንም  አሰራጭቷል፡፡ ልክ እንደ ምፍፕሌቶቹ ሁሉ መንፈሳዊ መዝሙር የያዙ በቡክሌት መልክ የተዘጋጁ የመዝሙር ግጥሞችን አሰራጭቷል፡፡ ሉተር ካሠራጫቸው መዝሙሮች ውስጥ የመጀመሪያው የመዝሙር “We are  starting  to sing  a new Song” የሚል ነበር፡፡ የሉተርን የተሀድሶ አላማ የተከተሉ በርካቶች ዛቻና ማስፈራሪያ የደረሠባቸው ሲሆን፣ ከነዚህም ውስጥ በ1523 ዓ.ም የሉተርን የተሃድሶ ዓላማ የተቀበሉ ሁለት የካቶሊክ መነኮሳት በብራስልስ መገደላቸው ይጠቀሳል፡፡ ማርቲን ሉተር አያሌ ወዳጆችና ተከታዮችን እንደማፍራቱ ሁሉ በካቶሊክ  ቤተክርስቲያን ዘንድ ከፍተኛ ውግዘት የደረሠበት ሲሆን በአይነ ቁራኛ የሚፈለግ ሰው ሆነ፡፡ ካቶሊክ ሉተርን ፀረ-ክርስቶስ (Anti-Christ) እንደሆነ በይፋ መግለጫ አወጣች፡፡  የሉተር ተከታዮችም በበኩላቸው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሊቃውንትንና የሥነ መለኮት ምሁራንን ማብጠልጠል ተያያዙት፡፡በዊንትበርግ የተጀመረው የተሃድሶ እንቅስቃሴ እየተጠናከረ መምጣት አብዛኛውን የአውሮፓ ግዛትን በበላይነት ትቆጣጠር ለነበረችው ለሮም ቤተክርስቲያን እጅግ ፈታኝ ነበር፡፡ በተለይ የማርቲን ሉተር ኪንግ ዝና በጀርመን፣ በፈረንሳይ፣ በቤልጅየም በኒውዘርላንድና በሌሎችና በአካባቢዎች ዝናው በከፍተኛ ደረጃ በመሰማቱ በርካታ አውሮፓውያን የተሃድሶውን ትምህርት ተቀላቀሉ፡፡ በጨለማው ክ/ዘመን ስልጣኔዋን ያጣችው ሮም፤ አሁን ደግሞ የአውሮፓ ቤተክርስቲያን የበላይ ተጠባባቂነቷን አሳጣት፡፡ አብዛኛውን የአውሮፓን ክፍልና መካከለኛውን ምስራቅ የራሷ ግዛት አድርጋ  ስትገዛ የነበረችው ሮም፤ ማርቲን ሉተር ኪንግ  በቤተክርስቲያኗ ላይ በለኮሰው እሳት ኃይሏን ቀስ በቀስ መነጠቅ ጀመረች፡፡

ከ16ኛ ክ/ዘመን በኋላ በርካታ የአውሮፓ አገራት ከሮም መንግስት ጉያ  በመውጣት ነፃነታቸው ማወጅ ጀመሩ፡፡ በሰሜን ካሮሊና ዩኒቨርስቲ የማህበራዊ ሳይንስ ምሁር የሆኑት ዜይኔፕ ቱፌኪ ሲናገሩ፤ “በየትኛውም ዘመን የሚኖሩ ህዝቦች አንደበታቸውን የሚገልጹበት መንገድ አያጡም” ብለዋል፡፡ የ500 ክ/ዘመን ልዩነት ባለው  የሉተር ዘመንና ቴክኖሎጂዎች በተራቀቁበት በ21ኛው ክ/ዘመን የሰው ልጆች መብትና ፍላጎትን ሊያግድም ሆነ ሊያፍን የሚችል ነገር ሊኖር እንደማይችል እያስተዋልን ነው፡፡ ነፃነት መንግስታት ወይም የሀይማኖት መሪዎች የሚቸሩት ሳይሆን ሰዎች የግድ ማግኘት የሚገባቸው ተፈጥሮአዊ መብታቸው ነው፡፡ ይህም በ16ኛው ክ/ዘመንና  በ2011 የአረብ አብዮት የታየ እውነታ ነው፡፡

ምንጭ፡- The Economist Encyclopedia AWAKE

 

 

Read 8360 times Last modified on Saturday, 21 January 2012 10:44