Monday, 06 April 2015 08:03

በየመን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ላይ የደረሰው ጥቃት እየተጣራ ነው

Written by 
Rate this item
(10 votes)

30 ኢትዮጵያውያን ከየመን ጅቡቲ ገብተዋል
    በየመን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ላይ የተፈፀመው ጥቃት  በማን እንደተፈፀመ እየተጣራ እንደሆነና  ከየመን ወደ አገራቸው ለመመለስ በኤምባሲው በኩል ከተመዘገቡ ኢትዮጵያውያን ውስጥ 30 ዜጎች  ጅቡቲ መድረሳቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ተወልደ ሙሉጌታ ለአዲስ አድማስ ገለፁ፡፡ በየመን መዲና ሰንአ የሚገኘው  የኢትዮጵያ ኤምባሲ ላይ ጥቃት መፈፀሙን ተከትሎ ጥቃቱ በማን እንደተፈፀመ እየተጣራ እንደሆነ የገለፁት አቶ ተወልደ፤ በተፈፀመው ጥቃት በኤምባሲው ሰራተኞች ላይ ምንም የደረሰ  ጉዳት የለም ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በየመን የሚገኙ ዜጎች ተመዝግበው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ባደረገው ጥሪ መሰረት፤ ከተመዘገቡት ውስጥ 12 ሴቶች፣ 11 ህፃናት እና 7 ወንዶች የተካተቱበት አንድ ቡድን ጅቡቲ መድረሱን ቃል አቀባዩ ጠቁመዋል፡፡
የመን ውስጥ በስደተኞች መጠለያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በሳኡዲ የአየር ጥቃት ተደብድበው ህይወታቸው አልፏል በሚል የተሰራጩ ዘገባዎችን በተመለከተ አቶ ሙሉጌታ በሰጡት ምላሽ፤ “በኛ በኩል ባደረግነው ማጣራት በዚህ ሁኔታ የሞተ ሰው የለም” ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል፤ የየመኑ የሁቲ አማፂ ቡድን ከኢራን የሚያገኘውን የወታደራዊ ቁሳቁስ ድጋፍ በቀይ ባህር በኩል በማሻገርና ለአማፂያኑ የወታደራዊ ስልጠና ቦታዎችን በአገሯ ላይ በማመቻቸት በተደጋጋሚ ስሟ የሚነሳው ኤርትራ፤ ሰሞኑን ተመሳሳይ ውንጀላ በሳኡዲ የመገናኛ ብዙሀን ተደርጎብኛል በሚል በሰጠችው ምላሽ፤ ውንጀላው መሰረተቢስ እንደሆነ ገልፆ የወሬው ምንጭም የአፍሪካ ቀንድ አገራት ናቸው ስትል አጣጥላለች፡፡
አብዛኛውን የየመን ክፍሎች በመቆጣጠር የአገሪቱን መሪ ከስልጣን ያስወገደው የሁቲ አማፂያን ቡድን፤ ከኢራን ከፍተኛ ድጋፍ እንደሚደረግለት የሚነገር ሲሆን የሚያገኘውንም ድጋፍ በማስተላለፍና ለወታደራዊ ስልጠና ቦታ በመስጠት ኤርትራ በተደጋጋሚ ስሟ እንደሚነሳ አገር እንደሆነች ይታወቃል፡፡ የመካከለኛው ምስራቅ የሚዲያ የምርምር ተቋም ከጥቂት አመታት በፊት “ኢራን በቀይ ባህር የእንቅስቃሴ አድማሷን እያሰፋች ነው” በሚል ርዕስ  ባወጣው መረጃ፤  ኢራን ለሁቲዎች የምታደርገው የወታደራዊ ቁሳቁሶች ድጋፍ በኤርትራ በኩል እንደሚያልፍ ጠቁሞ ኢራን ሁቲዎችን የምታሰለጥንበት ካምፕ ኤርትራ ውስጥ ከየጊንዳዕ ከተማ በስተምስራቅ ደንጎሎ የሚባል ቦታ እንደሚገኝ አስታውቆ ነበር፡፡ ሰሞኑን የሳኡዲ የመገናኛ ብዙሀን፤ ሁቲዎች ከኢራን ለሚያገኙት ድጋፍ ኤርትራ ትብብር ታደርጋለች ሲሉ ዘግበዋል፡፡
“ዘገባው ከሙያዊ ስነምግባር ያፈነገጠ ነው” በማለት ባለአስር ነጥብ መግለጫ ያወጣው የኤርትራ መንግስት፤ ዜናውን መሰረተ ቢስ ሲል ያጣጣለ ሲሆን የመረጃው ምንጮችም የአፍሪካ ቀንድ አገራት እንደሆኑ ገልጿል፡፡ “ሻባይት” የተባለው የኤርትራ መንግስት ድረገፅ በበኩሉ፤ የዚህ መረጃ ምንጮች አንዳንድ የስለላ ተቋማትና የኢትዮጵያው ህወሓት ነው ብሏል፡፡
የኤርትራ መንግስት ባወጣው ባለአስር ነጥብ አቋም ውስጥ፤ የየመን ጉዳይ የራሷ የውስጥ ጉዳይ ስለሆነ የትኛውንም የውጭ ሀይል በመደገፍ ኤርትራ እንደማትሰለፍ አስታውቋል፡፡
የሳኡዲ መንግሥት በበኩሉ፤ የሁቲ አማፅያን እንቅስቃሴ ለአገሬ ስጋት ናቸው በሚል  በየመን ወታደራዊ ድብደባ እየፈፀመ እንደምገኝ የሚታወቅ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስትም የሳኡዲን አቋም እንደሚደግፍ አስታውቋል፡፡

Read 4360 times