Saturday, 28 March 2015 09:57

የውዝዋዜ ንግስቷ ለህዳሴ ግድብ እስክስታ እመታለሁ አለች

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

ውዝዋዜ ስልጠና ትሰጣለች
የኢትዮ ሲኒያ ፕሮሞሽን እና ኤቨንትስ መስራችና ዳይሬክተር ተወዛዋዥ ጌታነህ ፀሐዬ ከሶስት ወራት በኋላ በመላው ኢትዮጵያ የሚቀርበውንና በየዓመቱ የሚቀጥለውን “አንድነት የውዝዋዜ ፌስቲቫል” ለማዘጋጀት ሲያስብ ከአገሯ ከወጣች 22 ዓመት ያስቆጠረችው የውዝዋዜ ንግስት እንዬ ታከለ በህይወት እንዳለች አያውቅም ነበር፡፡ ለዚህም ነው ዘንድሮ የሚቀርበው የውዝዋዜ ፌስቲቫል መታሰቢያነቱ ለእስክስታ እመቤቷ ደስታ ገብሬና ለውዝዋዜ ንግስቷ እንዬ ታከለ እንዲሆን የወሰነው፡፡
“እንዬ በህይወት መኖሯን ስሰማ በቀጥታ አድራሻዋን ወደማፈላለግ ነው የገባሁት” ያለው ጌታነህ፤ አድራሻዋን ካገኘ በኋላ ሊያዘጋጅ ባሰበው ፌስቲቫል ዙሪያ በጥልቀት ተወያይተው በመስማማቷ ከኢትዮጵያ ከወጣች ከረዥም ዓመታት በኋላ ሰሞኑን ወደ አገሯ ልትመጣ እንደቻለች ገልጿል፡፡
እንዬ ወደ አገር ቤት ከተመለሰች በኋላ ታላቁ የህዳሴ ግድብ አራተኛው የግንባታ ዓመት በዓልን አስመልክቶ በሚሊኒየም አዳራሽ በሚዘጋጀው ኮንሰርት ላይ ስራዋን እንድታቀርብ ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ጥያቄ እንደቀረበላት ለማወቅ ተችሏል፡፡ የኢትዮ ሲኒያ ፕሮሞሽንና ኤቨንትስ ባለቤት እና አርቲስት እንዬ ሰሞኑን በደብረዳሞ ሆቴል በሰጡት መግለጫ ላይ አርቲስቷ ለህዳሴው ግድብ 4ኛ የግንባታ ዓመት ስራዋን ለማቅረብ ፈቃደኛ እንደሆነች ጠቁማ “ድሮም አገራችን በረሃብ በተጠቃች ጊዜ ለረዱን የውጭ አገራት ምስጋና ለማቅረብ እስክስታ መትቻለሁ፤ የህዳሴው ግድብም የአገር ጉዳይ በመሆኑ እስክስታ እመታለሁ” ብላለች፡፡
በኢትዮጵያ በታዩት ለውጦች መገረሟን የጠቆመችው እንዬ ከረዥም ዓመታት በኋላ አገሯን ለማየት በመብቃቷ መደሰቷን ገልፃለች፡፡
የመጀመሪያው ዙር “አንድነት የውዝዋዜ ፌስቲቫል” ከሶስት ወር በኋላ በአዲስ አበባ፣ በባህርዳር፣ በጐንደር፣ በመቀሌ፣ በድሬደዋና በአዳማ እንደሚካሄድ የገለፀው አዘጋጁ ተወዛዋዥ ጌታነህ፤ በፌስቲቫሉ ላይ ለመታደም የሚፈልጉ የመግቢያ ትኬቱን ፌስቲቫሉ ከመካሄዱ አንድ ወር ከ15 ቀን ቀደም ብለው መግዛት እንዳለባቸው ጠቁሞ ከትኬቱ ጋርም በእንዬ አሰልጣኝነት የተሰራ የውዝዋዜ ሲዲ አብሮ እንደሚሰጣቸው ተናግሯል፡፡
“ፌስቲቫሉ እስኪደርስ ባለው የአንድ ወር ተኩል ጊዜ ውስጥ ታዳሚዎቹ ውዝዋዜዎቹን እየተለማመዱ ቆይተው ፌስቲቫሉ ሲከፈት የውዝዋዜ ትርኢቱን ከእንዬ እኩል እየተወዛወዙ ዝግጅቱን ያደምቁታል” ብሏል ጌታነህ። ፌስቲቫሉ በቋሚነት በየአመቱ እንደሚካሄድ የገለፀው ጌታነህ፤ ፌስቲቫሉ አንድነታችንን በውዝዋዜና በብሔር ብሔረሰቦች መካከል በሚደረግ የባህል ልውውጥ ለማጠንከርና ለሙያውና ለሙያተኞቹ ክብር ለመስጠት ዋነኛ መሳሪያ እንደሚሆን ጠቁሟል፡፡

Read 2532 times