Saturday, 28 March 2015 09:51

ታላላቅ አትሌቶች እና 41ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

   41ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በቻይናዋ ጉያንግ ከተማ  ላይ ዛሬ ሲካሄድ ባለፉት ሁለት ሻምፒዮናዎች ላይ ኢትዮጵያ በኬንያ የተወሰደባትን ብልጫ ለመመለስ ተስፋ ተደርጓል፡፡ በሁለቱም ፆታዎች 24 አትሌቶችን የሚያሳትፈው የኢትዮጵያ ቡድን ባለፈው ሰኞ ምሽት ወደ ስፍራው የተጓዘ ሲሆን ከኬንያ ባሻገር ከምስራቅ አፍሪካ የኡጋንዳ፤ የኤርትራ እና የታንዛኒያ አትሌቶች እንዲሁም የአሜሪካ፤ እንግሊዝ፤ ጃፓንና የአዘጋጇ ቻይና አትሌቶች በተለያዩ የውድድር መደቦች ጠንካራ ተፎካካሪዎቻቸው እንደሚሆኑ ተዘግቧል፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በነበራት የውጤት ታሪክ፣ በሌሎች ዓለም አቀፍ ውድድሮች ማለትም በኦሎምፒክና በዓለም ሻምፒዮና ታላላቅ ስኬት ያገኙ አትሌቶችን የምታፈራበት ምቹ መድረክ ሆኖ ቆይቷል፡፡
የኢትዮጵያ አገር አቋራጭ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ዶክተር ይልማ በርታ፤ አትሌቶቹ ለሶስት ሳምንታት ጠንካራ ዝግጅት ማድረጋቸውንና በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡ ካለፉት ሁለት ሻምፒዮናዎች የተሻለ ውጤት እንደሚጠብቁም ተናግረዋል፡፡ አትሌቶቹ ለአንድ ወር ያህል በቀን ሁለት ጊዜ ጠንካራ ልምምድ ሲሰሩ ቆይተዋል።ኢትዮጵያ የምትገኝበት መልክኣ ምድር በከፍታ ቦታ ላይ የሚገኝ እንደሆነ የገለፁት አሰልጣኞች፤ በአንጻሩ  ውድድሩ የሚካሄድበት የቻይናዋ ከተማ ጉያንግ ዝቅተኛ ስፍራ ላይ መገኘቷ የኢትዮጵያን አትሌቶች በጠንካራ ተፎካካሪነት ውጤታማ እንደሚያደርጋቸው ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቶች የአየር ሁኔታውን በአግባቡ በመጠቀምና የቡድን ስራ በመስራት በነጠላም ሆነ በቡድን  አሸንፈው  ጥሩ ውጤት ይዘው እንደሚመለሱም ተስፋ አድርገዋል፡፡
በ41ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና  ላይ 51 አገራትን የወከሉ 447 አትሌቶች በአራት የአገር አቋራጭ የውድድር አይነቶች፤ በ6 ኪሎ ሜትር ወጣት ሴቶች፣ በ8 ኪሎ ሜትር ወጣት ወንዶች፣ በ8 ኪሎ ሜትር አዋቂ ሴቶችና በ12 ኪሎ ሜትር አዋቂ ወንዶች ይሳተፋሉ፡፡ በሻምፒዮናው ባላቸው የውጤታማነት ታሪክ የኢትዮጵያ እና የኬንያ አትሌቶች ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷዋል፡፡  የኬንያ ቡድን ምርጥ አትሌቶቹን በጉዳት ቢያጣም በከፍተኛ የበላይነት በውድድሩ ለመሳተፍ መዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡
በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናው ከ1ኛ እስከ 6ኛ ደረጃ ለሚያገኙ አትሌቶች የገንዘብ ሽልማት ይበረከታል። ለ1ኛ 30ሺ ዶላር፣ ለ2ኛ 15ሺ ዶላር፣ ለ3ኛ 10ሺ ዶላር፣ ለ4ኛ 7ሺ ዶላር፣ ለ5ኛ 5ሺ ዶላር እንዲሁም ለ6ኛ ደረጃ 3ሺ ዶላር ነው፡፡ በቡድን ለሚያሸንፉ አገራት ደግሞ 60ሺ ዶላር ይበረከታል፡፡
በሻምፒዮናው ላይ ኢትዮጵያን የሚወክሉት 24 አትሌቶች (12 ወንዶችና 12 ሴቶች)   በ32ኛው የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ውድድር ላይ ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ በመውጣት ባስመዘገቡት ውጤት መሰረት ተመርጠዋል፡፡ ከመካከላቸውም ከሁለት ዓመት በፊት በፖላንድ በተካሄደው 40ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በግል ሜዳሊያ ካገኙት  ስድስት አትሌቶች አራቱ ይገኙበታል፡፡ በአዋቂ ወንዶች 12 ኪሎ ሜትር ኢትዮጵያን በመወከል ከፍተኛ ግምት የተሰጠው አፀዱ ፀጋዬ ሲሆን ከሁለት ዓመት በፊት በወጣት ወንዶች የወርቅ ሜዳልያ አግኝቶ የነበረው ሐጎስ ገብረህይወትም ባለፈው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ከኢትዮጵያ የተነጠቀውን የወርቅ ሜዳልያ ክብር እንዲመልስ ተጠብቋል፡፡  በአዋቂ ሴቶች የ8 ኪሎ ሜትር ውድድር ደግሞ ህይወት አያሌው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙ ልምድ  ያካበተችው በላይነሽ ዋቅጅራ ለተሻለ ውጤት ግምት አግኝተዋል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በፖላንዷ ከተማ ባይድጎስዝ ተደርጎ በነበረው  40ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና  የኢትዮጵያ ቡድን በተለይ በግል ውጤት በኬንያ አቻው ከፍተኛ ብልጫ ተወስዶበት ነበር፡፡ በወቅቱ ኬንያ የአለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናውን የሜዳሊያ ሰንጠረዥ (የግል እና የቡድን ድምር) በአምስት ወርቅ፣ ሶስት ብር እና አንድ ነሀስ በአጠቃላይ በ9 ሜዳሊያዎች አንደኛ ደረጃን በመያዝ አሸንፋዋለች፡፡ የኢትዮጵያ ቡድን በ3 ወርቅ፣ በ4 ብርና በ3 ነሀስ በድምሩ በ10 ሜዳሊያዎች በሁለተኛነት ማጠናቀቁ ሲታወስ፤ በወጣት ወንዶች 8 ኪ.ሜ. የወርቅ እና ነሐስ ሜዳልያ አሸናፊዎቹ ሀጎስ ገ/ሕይወት እና ሙክታር እድሪስ፣ በአዋቂ ሴቶች 8 ኪ.ሜ. የነሐስ ሜዳልያ ባለቤቷ በላይነሽ ኦልጂራ እና በወጣት ሴቶች 6 ኪሜ. የነሐስ ሜዳልያ አሸናፊዋ አለሚቱ ሀሮዬ ናቸው። በቡድን ውጤት በወጣትና አዋቂ ወንዶች የወርቅ ሜዳሊያ በወጣትና አዋቂ ሴቶች ደግሞ የብር ሜዳሊያ በማግኘት ነው፡፡
አዘጋጅነቱ ለኢትዮጵያስ?
የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በአይኤኤኤፍ ስር ከሚካሄዱ ፈታኝ የአትሌቲክስ ውድድሮች አንዱ ነው፡፡ መደበኛ ውድድሮቹ 4 ሲሆኑ በአዋቂ ወንዶች 12 ኪ.ሜ ሴቶች 8 ኪ.ሜ፤ እንዲሁም ለወጣቶች ወንዶች 8 ኪ.ሜ ሴቶች 6 ኪ.ሜ ይወዳደሩበታል፡፡ በ1998 እ.ኤ.አ በአዋቂዎች ምድብ በሁለቱም ፆታዎች የ4 ኪ.ሜትር አጭር ርቀት ውድድር ተጀምሮ ከ2006 እ.ኤ.አ በኋላ ተቋርጧል፡፡ ከ1973 እኤአ ጀምሮ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ለ38 ጊዜያት በየዓመቱ ተካሂዷል፡፡ በእነዚህ ግዜያት በተለይ ባለፉት 25 አመታት የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች በየውድድር መደቡ እስከ 10 ያለውን ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ መቆጣጠራቸው ባስከተለው ጫና ሻምፒዮናው ከ2011 እ.ኤ.አ ወዲህ  በየሁለት ዓመቱ እንዲደረግ ተወስኗል፡፡ ሻምፒዮናው በየሁለት ዓመቱ መካሄድ ከጀመረ ዘንድሮ 3ኛው ሲሆን በውድድሩ ታሪክ ደግሞ ለ41ኛ ጊዜ የቻይናዋ ከተማ ጉያንግ የምታስተናግደው ይሆናል፡፡ በ2017 እ.ኤ.አ 42ኛውን የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና የኡጋንዳዋ ከተማ ካምፓላ የምታዘጋጅ ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ የሻምፒዮናውን መስተንግዶ የምትጠይቅበትን ግዜ በጐረቤቷ ኡጋንዳ የተቀደመች ይመስላል፡፡  ከአፍሪካ አገራት ሞሮኮ ለሁለት ጊዜያት በ1975 እና በ1998 እኤአ፤ ደቡብ አፍሪካ በ1996 እኤአ እንዲሁም ኬንያ በ2007 እኤአ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናውን አስተናግደዋል፡፡ ከአውሮፓ እንግሊዝ፤ ፖላንድ፤ ፈረንሳይ፤ ስፔን ፤ፖርቱጋልና ጣልያን ከአንድ ጊዜ በላይ ውድድሩን ሲያስተናግዱ፤ አሜሪካም ከአንድ ግዜ በላይ አዘጋጅ ነበረች፤ ከኤስያ ጃፓን፤ ከመካከለኛው ምስራቅ ጆርዳን ሁሉ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናን አስተናግደዋል፡፡ በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና የተሳትፎ ታሪክ ከፍተኛውን ውጤት በማስመዝገብ ከዓለም ሁለተኛ ደረጃ የምትይዘው ኢትዮጵያ ውድድሩን የማዘጋጀት እድሏ ሰፊ ይሆናል። ስለዚህም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ቢያንስ ውድድሩን በ2019 እና በ2021 የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናውን ለማስተናገድ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡
የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች የበላይነትና የኢትዮጵያ ውጤት ታሪክ
ባለፉት 40 የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናዎች በውድድሩ በሁለቱም ፆታዎች የቡድን ውጤት ከቀረቡ 168 ሽልማቶች ኬንያና ኢትዮጵያ  123 በማግኘት በበላይነት ይመራሉ፡፡ በአዋቂዎች ምድብ በሁለቱም ፆታዎች በተለይ በረጅም ርቀት ኬንያ ለ35 ጊዜያት የቡድን ውጤቱን በወርቅ ሜዳልያ ስታሸንፍ ኢትዮጵያ ደግሞ ለ18 ጊዜያት የወርቅ ሜዳልያዎችን ድል አድርጋለች። የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናው በምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች የበላይነት ስር ከወደቀ ከ25 ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል፡፡ በተለይ ሁለቱ አገራት ኬንያ እና ኢትዮጵያ ባሳዩት የበላይነት በየአመቱ መካሄድ የነበረበትን ሁኔታ በየሁለት ዓመት እንዲቀየር ምክንያት ሆኗል፡፡  በአዋቂ ወንዶች በአጭርና በረጅም ርቀት ከ1981 እ.ኤ.አ ወደ አሸናፊዎቹ እየተፈራረቁ የተገኙት ከኬንያና ኢትዮጵያ ነው፡፡ በታዳጊ ወንዶች ምድብም ሁለቱ አገራት ከ1982 እ.ኤ.አ ወዲህ አሸናፊነቱን ተፈራርቀውበታል፡፡ በአዋቂ ወንዶች የ12 ኪ.ሜ ውድድር ከ1986-2003 እ.ኤ.አ የኬንያ አትሌቶች ለ18 ዓመታት አከታትለው አሸንፈዋል። በአዋቂ ሴቶች ምድብም በ1994 እ.ኤ.አ የፖርቱጋል አትሌት ጣልቃ ገብታ ብታሸንፍም ከ1991 እ.ኤ.አ ጀምሮ አሸናፊዎቹ ከኬንያ እና ከኢትዮጵያ የወጡ አትሌቶች ናቸው፡፡
የኬንያው አትሌት ጆን ኑጉኒ ለ5 የተለያዩ ጊዜያት በማሸነፍ የመጀመሪያው ቢሆንም በየዓመቱ ለተከታታይ 5 ዓመታት በረጅም ርቀት ለማሸነፍ የቻለው የኬንያው ፖል ቴርጋት ነው፡፡ በአጭርና ረጅም ርቀት የአገር አቋራጭ ድርብ ድል በማስመዝገብ የመጀመሪያው አትሌት ግን ኢትዮጵያዊው ቀነኒሣ በቀለ ነው፡፡ ቀነኒሣ በአጭር ርቀት 4 ኪ.ሜ እና በረጅም ርቀት 12 ኪ.ሜ ውድድሮች በ5 ሻምፒዮናዎች በተከታታይ በማሸነፍ ብቸኛው አትሌት ሲሆን በ2008 እ.ኤ.አ ላይ በረጅም ርቀት 6ኛውን የወርቅ ሜዳልያ በማግኘቱ ደግሞ በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናው ታሪክ ከፍተኛውን የውጤት ክብረወሰን ያስመዘገበ አትሌት ሆኗል፡፡ በሌላ በኩል በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናው በአዋቂ ውጤታማ ከሆኑ የኢትዮጵያ አትሌቶች መጠቀስ ያለባቸው ደራርቱ ቱሉና ጥሩነሽ ዲባባ ናቸው፡፡  አትሌት ደራርቱ ቱሉ በረጅም ርቀት ለ3 ጊዜያት ያሸነፈች ሲሆን፣ ጥሩነሽ ዲባባ ደግሞ በአዋቂዎች ምድብ በረጅም ርቀት ለ3 ጊዜያት እንዲሁም በአጭር ርቀት ለ1 ጊዜ ማሸነፍ የኢትዮጵያ አትሌቶችን ትልቅ ውጤት አስመዝግባለች፡፡
በአለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ በኢትዮጵያዊ አትሌት የመጀመሪያው የሜዳልያ ድል የተመዘገበው በ1981 እ.ኤ.አ ላይ በአዋቂዎች ምድብ የ12 ኪ.ሜ ውድድር መሃመድ ከድር ባገኘው የብር ሜዳልያ ነው፡፡ አትሌት መሐመድ ከድር ከአንድ ዓመት በኋላ በተመሳሳይ ውድድር አሸንፎ የመጀመሪያውን የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳልያ ለኢትዮጵያ አስገኝቷል፡፡ በአዋቂ ወንዶች የ12 ኪሎሜትር ውድድር ኢትዮጵያ ከሰበሰበቻቸው 10 የወርቅ ሜዳልያዎች ስድስቱን ያስመዘገበው አትሌት ቀነኒሣ በቀለ ከ2002-2008 እ.ኤ.አ ባለፉት ጊዜያት ሲሆን ሌሎቹን 4 የወርቅ ሜዳልያዎች መሃመድ ከድር (በ1982 እ.ኤ.አ)፣ በቀለ ደበሌ (በ1983 እ.ኤ.አ)፣ ገብረእግዚአብሔር ገ/ማርያም (በ2009 እ.ኤ.አ) እንዲሁም ኢማና መርጋ በ2011 እ.ኤ.አ ላይ አስመዝግበዋል፡፡
በአዋቂ ሴቶች የ8 ኪ.ሜ ውድድር ደግሞ በኢትዮጵያዊ አትሌት የመጀመሪያ የሜዳልያ የተገኘው በ1991 እ.ኤ.አ ደራርቱ ቱሉ በወሰደችው የብር ሜዳልያ ነው፡፡ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ደግሞ በ1995 እ.ኤ.አ ላይ አሁንም ደራርቱ ቱሉ የተጐናፀፈች ሲሆን ሌሎች ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎችን ደግሞ በ1975 በ2000 እ.ኤ.አ አግኝታለች፡፡ በአዋቂ ሴቶች ኢትዮጵያ ካስመዘገበቻቸው 9 የወርቅ ሜዳልያዎች 3 ከጥሩነሽ ዲባባ (በ2005፣በ2006፣ በ2008 እ.ኤ.አ) 2 በጌጤ ዋሚ (በ1996፣ በ1999 እ.ኤ.አ) እንዲሁም ወርቅነሽ ኪዳኔ (2003 እ.ኤ.አ) ተገኝተዋል፡፡
በርካታ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ሜዳሊያዎችን በግል እና ከቡድን ጋር በማግኘት በወንዶች ቀነኒሳ በቀለ በአጠቃላይ 27 ሜዳሊያዎችን በመውሰድ ከዓለም አንደኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ፣ በሴቶች ኢትዮጵያዊቷ ወርቅነሽ ኪዳኔ በ21 ሜዳሊያዎች መሪነቱ ላይ ተቀምጣለች።በግልና በቡድን የወርቅ ሜዳሊያዎች ድምር የአለም አገር አቋራጭን የተቆጣጠሩትም ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ናቸው። በወንዶች በግል ያገኛቸውን 12 ወርቅ ሜዳሊያዎች እና በቡድን ያገኛቸውን አራት የወርቅ ሜዳሊያዎች ጨምሮ በ16 ወርቅ ሜዳሊያዎች ቀነኒሳ በቀለ የወንዶቹን በቁጥር አንድነት ሲይዝ፣ በሴቶችም በግሏ አምስት፣ በቡድን ዘጠኝ የወርቅ ሜዳሊያዎችን ያገኘችው ጥሩነሽ ዲባባ በ14 ወርቅ ሜዳሊያዎች የሴቶቹን ዘርፍ አንደኛነቱን ይዛለች። በአንድ የአለም አገር አቋራጭ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ቢያንስ አራት ሜዳሊያዎችን በማግኘት ሰባት አትሌቶች ክብረወሰኑን ሲይዙ ሰባቱም አትሌቶች ኢትዮጵያዊያን ናቸው። እነሱም ሀይሉ መኮንን፣ ጌጤ ዋሚ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ወርቅነሽ ኪዳኔ፣ ገብረእግዚአብሄር ገብረማሪያም፣ ጥሩነሽ ዲባባ እና መሰለች መልካሙ ናቸው።

Read 3532 times