Saturday, 28 March 2015 09:25

ናይጀሪያ ለዛሬው ምርጫ ደህንነት ሁሉንም ድንበሮቿን ዘጋች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

   ናይጀሪያ በዛሬው ዕለት የምታከናውነውን ፕሬዚዳንታዊና የፓርላማ ምርጫ ከቦኮ ሃራም ጥቃትና ከውጭ ሃይሎች ጣልቃ ገብነት ለመከላከል እንዲሁም ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ  በሚል ካለፈው ረቡዕ ምሽት ጀምሮ ሁሉንም የባህርና የየብስ ድንበሮቿን መዝጋቷን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
የናይጀሪያ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ፓትሪክ አባ ሞሮ ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ የሌሎች አገር ዜጎች ድንበር አቋርጠው በመግባት በአገሪቱ ምርጫ ድምጽ ለመስጠት እንዳቀዱ የሚያመለክቱ መረጃዎች በመገኘታቸው፣ ምርጫውን ከውጭ ጣልቃ ገብነቶች ለመከላከል ሲባል ድንበሮቹ ተዘግተዋል፡፡
ቦኮ ሃራም በተባለው የአገሪቱ ጽንፈኛ ቡድን ላለፉት ስድስት አመታት ሲፈጸሙ የቆዩ ጥቃቶችን በመሸሽ ወደ ጎረቤት አገራት የተሰደዱ በሺዎች የሚቆጠሩ ናይጀሪያውያን፣ በዛሬው ምርጫ ድምጽ መስጠት እንደማይችሉም ዘገባው አስታውቋል፡፡
ባለፉት ስድስት ሳምንታት የአገሪቱ ሃይሎች በአሸባሪው የቦኮሃራም ቡድን ቁጥጥር ስር የነበሩ የድንበር አካባቢዎችን መልሰው መያዝ ቢችሉም፣ በተለይ በሰሜን ምስራቃዊ የአገሪቱ አካባቢዎች ሰርጎ ገቦች ድንበር ጥሰው ገብተው ምርጫውን ያደናቅፋሉ በሚል ስጋት መንግስት ሁሉንም የአገሪቱ ድንበሮች ለመዝጋት መወሰኑን ዘገባው ገልጧል፡፡
ምርጫው በሰላማዊ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ለማስቻል ሲባል፣ ሁሉም የአገሪቱ ድንበሮች እስከ ዛሬ እኩለ ሌሊት ድረስ ዝግ ሆነው እንደሚቆዩና ቦኮ ሃራም በሚንቀሳቀስባቸው ቦርኖ፣ ዮቢና አዳማዋ ግዛቶች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንደተጣለም ተዘግቧል፡፡
የቦኮ ሃራምን ጥቃት የመቋቋም ቁርጠኝነትና ብቃት ያንሳቸዋል በሚል በስፋት ሲተቹ የቆዩት ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን፣ በጸጥታ ስጋት ለሳምንታት ተራዝሞ  ዛሬ በሚካሄደው ምርጫ ከተቀናቃኛቸው የቀድሞው የጦር መሪ ሙሃማዱ ቡሃሪ ብርቱ ፉክክር እንደሚጠብቃቸው ቢቢሲ ጠቁሟል፡፡
ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን፤ ጦራቸው በቦኮ ሃራም ቁጥጥር ስር የሚገኙ የአገሪቱ ግዛቶችን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥር ውስጥ እንደሚያደርግ ባለፈው ሳምንት ቢናገሩም፤ ቦኮ ሃራም እስከ 11 ዓመት ዕድሜ ያላቸው 500 ህጻናትን ዳማሳክ ከተባለችው የአገሪቱ ከተማ አፍኖ መውሰዱን ቢቢሲ ባለፈው ማክሰኞ ዘግቧል፡፡

Read 2248 times