Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 21 January 2012 10:30

ህዝቡ “የሥልጣን ሊዝ አዋጅ” ሊያወጣ ነው! ሥልጣን በሊዝ ሊሆን ነው - እንደ መሬት

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በግል ጥላቻ፣ በጥቅም ግጭት በፖለቲካ አመለካከት ልዩነት… አንዱ ለሌላው ውድቀትና ሞት መፍጠን ምክንያት የሆነበት ብዙ አጋጣሚዎች አሉ፡፡ የክፋት ተግባር ፈፃሚዎቹ አሻራ ላለመተው ብርቱ ጥንቃቄ ለማድረግ ይሞክራሉ፡፡ በጣም የሚገርመው አንዳንዶች በተዘጋጀላቸው ወጥመድ ተጠልፈው ሲወድቁ አንዳንዶች ተአምር በሚመስል መልኩ የተሸረበባቸው ተንኮል እንዳለ እንኳን ሳያውቁ ከአደጋ ይተርፋሉ፡፡

በዚህ ሳምንት ትኩረቴን ከሳቡት አንኳር ጉዳዮች አንዱ ሂዩማን ራይትስ ዎች በኢትዮጵያ መንግስት ላይ የሰነዘረው ውንጀላ ነው፡፡ ለነገሩ መንግስት በውጭ ጉዳይ ሚ/ር በኩል ልክ ልኩን ነግሮታል፡፡ ግን በቂ አልመሰለኝም (ያንሰዋል!) እኔ የምለው ግን ይሄ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ነኝ ባይ ተቋም ምነው ከላያችን ላይ አልወርድም አለ? እኔማ ሙሉ አቅሙንና በጀቱን ኢትዮጵያ በምትባል ጥንታዊ አገር ላይ እንዲያውል ስፖንሰር ያደረገው ባዕድ አገር ሳይኖር እንደማይቀር መጠርጠር ጀምሬአለሁ፡፡

ቆይ ግን ያለኛ አገር አላየም እንዴ? አንዴ ምርጫ ተጭበረበረ፣ (በ2000 ዓ.ም ምርጫ ወቅት) ሌላ ጊዜ ሰብዓዊ መብት ተጣሰ፣ አሁን ደግሞ የመሬት ወረራ (land grabbing)   ተስፋፍቷል ወዘተ እያለ ነው፡፡ ምን አልባት ግን ቂም ይዞ ቢሆንስ? ትዝ ይላችኋል… በ2002 ምርጫ ወቅት የኢህአዴግ ደጋፊዎች ግልብጥ ብለው ወጥተው አልነበር? ያኔ  ተቋሙ ምርጫው እንከኖች ነበሩበት ስላለ የኢህአዴግ ደጋፊዎቹ እግረ መንገዳቸውን አውግዘውት ነበር፡፡ አይ ሞኞ! ሰልፉ እኮ እሱን ለመቃወም ታስቦ የተዘጋጀ አልነበረም፡፡ ኢህአዴግ በ95 ነጥብ ምናምን ምርጫውን በዝረራ ሳይሆን በጠረባ በማሸነፉ የተደሰቱ ደጋፊዎች ድላቸውን ለማክበርና ለማብሰር አደባባይ ሲወጡ - ከወጣን አይቀር ብለው ነው ሂዩማን ራይትስ ዎችን የነቀፉት! (ተሳሳትኩ እንዴ?) እሱ ግን ከምር ወስዶት ይኸው እስከዛሬ ጠምዶ ይዞናል፡፡ ቆይ ግን በትክክል ጠቡ ከማነው? (መጥራት አለበታ!) ከእኛ ነው? ከመንግሥት ነው? ወይስ ከኢህአዴግ? መቼም እዚህ ውስጥ ተቃዋሚዎች ያሉበት አይመስለኝም፡፡ ምናልባት ግን ኢህአዴግ መንግሥት ከመሆኑ በፊት ከተቋሙ ጋር የጀመሩት ፀብ ካላቸው ለብቻቸው ይጨርሱት (እኛን አያነካኩን!) ፀቡ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ከሆነ ግን እኛንም ይመለከታልና በጋራ እንጨርሰዋለን፡፡ (በፒስም በሃርድም የሚፈራ የለም)

 

እኔማ አሁን እያሰጋኝ ያለው ምን መሠላችሁ? ተቋሙ ስሙን ቀይሮ “ኢትዮጵያን ራይትስ ዎች” ተብያለሁ እንዳይለን ነው፡፡ ለነገሩ አንድያውን ወደ ኢትዮጵያ ቢጠቃለል ይሻለው ነበር፡፡ እውነቴ ነው የምላችሁ … ሰሞኑን ስለዚህ ተቋም ስብሰለሰል ነው የሰነበትኩት፡፡ አንድ ቀንማ ምን አሰብኩ መሰላችሁ? ለምን የተቋሙን አመራር በሽብርተኝነት አንከሰውም… አልኩኝ (አፉን ዘግቶ ይቀመጥ ነበር) ግን ሳስበው ደሞ… ዓለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋም ከሰን እንደማናሸንፍ ገባኝና ሌላ አማራጭ ማሰብ ጀመርኩ፡፡ እናም ለምን በሽምግልና አንፈታውም? ስል አሰብኩ (እንደ ጋዜጠኛ ሰይፉ ፋንታሁንና ድምፃዊት ሳያት ደምሴ) ከ97 ምርጫ በኋላ በኢህአዴግና በተቃዋሚዎች መካከል ገብተው   የተፈጠረውን ግጭት በሽምግልና እንደፈቱት ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅ አይነት የእግዜር ሰው ብናገኝ እኮ ነገሩ በሰላም ይጠናቀቅ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ እንኳን ምርጫ ተጭበረበረ ብሎ ሊከስ ቀርቶ የዜጐች መብት ጭፍልቅልቅ ቢልም እንኳ ትንፍሽ አይልም (በፒስ አይሻልም ታዲያ?) በሰሞነኛ ጉዳይ ተጠምጄ አጀንዳዬን ሳልነግራችሁ ቀረሁ አይደል?

ይሄውላችሁ ለዛሬው የፖለቲካ ወጋችን አጀንዳ ፍለጋ የትም አንሄድም፡፡ ባለፈው ሳምንት “ቻይናው ኢህአዴግ ስንት ዓመት ይኖራል?” በሚል ርዕስ እዚሁ ጋዜጣ ላይ የቀረበው አፍቃሬ-ኢህአዴግ መጣጥፍ ከበቂ በላይ ይመስለኛል - ለአጀንዳነት፡፡

አንዲት ሴትወይዘሮ ጐረቤት ጋ ለመሄድ ሠራተኛዋ ነጠላዋን እንድታቀብላት ትጠይቃለች፡፡ አካሄዷ ለጠብ (ነገር ፍለጋ) እንደሆነ ያስታውቃል፡፡ ነጠላው ከመድረሱ በፊት ግን እዚያው ቤት ውስጥ ካለች ዘመድ ጋር በአንድ ጉዳይ አለመግባባት ይፈጠርና ጦርነት ይነሳል፡፡ ሴት ወይዘሮዋም ለሰራተኛዋ “ነጠላውን ተይው! እዚሁ ነገር አግኝቻለሁ” አለቻት ይባላል፡፡ እኔም ለወጌ የሚሆን አጀንዳ ወይም “ነገር” እዚሁ ጋዜጣ ላይ አግኝቻለሁ ለማለት ያህል ነው - ተረቱን ያመጣሁት፡፡

እኔ የምለው ግን… ከመቼ ወዲህ ነው ኢህአዴግ “ቻይናዊ” የሆነው? ባለፈው ሳምንት የፃፉት አብዲ መ. የተባሉ ፀሃፊ ለምን “ቻይናው ኢህአዴግ” እንዳሉ የሚያውቀው ፈጣሪ ብቻ ነው፡፡ እኔ ግን ምን ጠረጠርኩ መሰላችሁ? ኢህአዴግን ኢትዮጵያዊ አይደለም ብሎ ከሥልጣን ለማፈናቀል የተሸረበ ሴራ ቢሆንስ? (እሱ እንኳን የተበላ ዕቁብ ነው) በነገራችን ላይ የፅሁፉ አቅራቢ ገና ከርዕሳቸው በአንባቢው ላይ “ብዥታ” ለመፍጠር አልመው የተነሱ ይመስላሉ፡፡ (በነገራችን ላይ “ብዥታ” የሰሞኑ የካድሬዎች ቋንቋ ነው)

እንዲያም ሆኖ ግን “ቻይናው ኢህአዴግ” በሚል ርዕስ ካለፈው ሳምንት ቀደም ባለው ጊዜ “የሁለት ምርጫዎች ወግ” ላይ ትችት በሰነዘሩት አልአዛር ኬ የተባሉ አምደኛ ላይ የመልስ ምት የወረወሩት አብዲ መ.ን (ወይስ ጓድ አብዲ?) የብዕር አጣጣል  (የፖለቲካ አጣጣል አልወጣኝም) ወድጄላቸዋለሁ፡፡ ትንሽ ያልተመቸኝ ግን ምን መሰላችሁ? ኢህአዴግን ሲበዛ ከማድነቃቸው የተነሳ ከሃቅ ለመፋታት ዳር ዳር ማለታቸው ነው፡፡ ኧረ ህገ መንግስቱንም  ሳይዘነጉት አልቀሩም፡፡

ለቀጣዮቹ 30 እና 40 ዓመታት ኢትዮጵያን መግዛት (በገንዘብ ሳይሆን በሥልጣን) ያለበት ብቸኛው ፓርቲ ኢህአዴግ ነው የሚሉት ፀሃፊው፤ ተቃዋሚዎች ለአቅመ ሥልጣን አልደረሱም ሲሉ ይሟገታሉ፡፡ (ሙግታቸው በጨበጣ ቢሆንም) በእርግጥ እቺ ፖለቲካዊ አቋም የእሳቸው ኦሪጂናል ሃሳብ ሳትሆን በቀጥታ ከኢህአዴግ የኮረጁዋት እንደሆነች እሳቸው ባይነግሩንም እኛ ጠርጥረናል (በኮፒራይት አልጠየቅም ብለው ይሆን?)

ለነገሩ ኢህአዴግም በቅርቡ በይፋ እንደነገረን፤ ኢትዮጵያን ለወግ ማዕረግ ለማብቃት ልዩ አቅምና ተሰጥኦ ያለው ብቸኛ ፓርቲ እሱ ብቻ ነው - አውራው ኢህአዴግ፡፡ የእሱ ዘመነኞች የሆኑት ተቃዋሚዎች ግን ሰላም አደፍራሽና ልማት አደናቃፊ ስለሆኑ  ሥልጣን አካባቢ ዝር ሊሉ አይገባም እያለ ነው (ምን አገባውና የሚል ነገር አልወጣኝም!)

እኔ የምለው…ኢህአዴግ ሰሞኑን በመሬት ሊዝ አዋጁ ዙሪያ ከመዲናዋ ነዋሪዎች ጋር ያደረገውን ውይይት ተከታትላችኋል? (በአካልም ይሁን በቲቪ መስኮት) ባይገርማችሁ ነዋሪውና ካድሬው እንደድሮው ፈፅሞ አያሳስቱም፡፡ አንደኛ አብዛኞቹ ካድሬዎች ፍሬሽ ናቸው (ከሚሌኒየሙ በኋላ የተመለመሉ) በዚያ ላይ ገና በኢቴቪ መስኮት ብቅ ሲሉ ያስታውቃሉ! አንድ ሁለት ዓ.ነገሮች ከተነፈሱማ ለካድሬነት ከተመለመሉ ምን ያህል ጊዜ እንደሆናቸው ሳይቀር ልትገምቱ ትችላላችሁ፡፡ በነገራችን ላይ የኢህአዴግ ካድሬዎች ከዘመኑ ጋር እንዲዘምኑ የሥልጠና ካሪኩለሙ (የካድሬዎች ማለቴ ነው) በአፋጣኝ መሻሻል እንዳለበት አንዳንድ ኢህአዴግ የማያውቃቸው ጥናቶች ይጠቁማሉ (ሂዩማን ራይትስ ዎች ያሰራው ይሆን እንዴ?) እናም “መንግስታችን”፤ “ብዥታ”፤ “ልማት አደናቃፊ” ወዘተ የሚሉ የተሰለቹ (cliche ለማለት ነው) ቃላት የሚተፉ ካድሬዎች የፓርቲውን ደረጃ ዝቅ ያደርጉታል የሚል በጥናትና መረጃ ላይ የተደገፈ ስጋት አድሮብኛል፡፡ (ከመቆርቆር የመነጨ ነው)

ወደ አጀንዳዬ ልመለስ - ኢትዮጵያን መምራት ያለበት አውራ ፓርቲው ኢህአዴግ ነው ወደሚለው ክርክር ማለቴ ነው፡፡ እናም አገሪቱን ሥልጣን ይዞ ማን ይምራ የሚለውን አንገብጋቢ ጥያቄ በተመለከተ አንድ የሊዝ አዋጅ ተወያይ የተናገሩትን በምሳሌነት ልጥቀስላችሁ፡፡ “የሊዝ አዋጁ ወርቅ ነው፡፡ ግን ወርቅ ቢነጠፍም ህዝቡ አልፈልግም ካለ አልፈልግም ነው” አያችሁ ምንም ተባለ ምንም የማታ ማታ ወሳኙ ህዝብ ነው እንደማለት ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር ኢህአዴግ በጊነስ ላይ ሊሰፍር የሚችል ባለ 3 አሃዝ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እድገት ለማምጣት እየታተረ መሆኑን ማንም አይክድም፡፡ የአገሪቱ መጥፎ ገፅታ በመልካም ገፅታ እንዲተካም እየጣረ ነው፡፡ (ፕሮፓጋንዳውን ቀንሰንለት ማለት ነው) አገሪቱ በምግብ ራሷን እንድትችልም ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም (አንዳንዶች የልማት ስትራቴጂው “የልፋት ስትራቴጂ” ሆኖበታል ቢሉም) እነዚህንና ሌሎች የኢህአዴግ በጐ ጥረቶችን (ከንቱ ድካሞችም አሉ የሚሉ ገጥመውኛል) እንኳን ወዳጅ ጠላትም አይክደውም፡፡ ያፈጠጠ እውነት ነዋ! ይሄ ሁሉ ሆኖ ግን ለሚቀጥሉት 30 እና 40 ዓመታት ማን ስልጣን ይዞ አገሪቱን ይምራ የሚለውን ጉዳይ በድምፁ የሚወስነው ኢህአዴግም አቶ አብዲም እንዳልሆኑ ማወቅ ብልህነት ነው (ይሄም ያፈጠጠ እውነት ነው!) በኢህአዴግ የተረቀቀው ህገ መንግስት እንደሚለው ከሆነ ሥልጣን የሚሰጠውና የሚነሳው ብቸኛ ባለሙሉ መብት ህዝቡ ብቻ ነው፡፡ አቶ አብዲ እንደለመዱት “ህዝቡ ማነው?” ሲሉ ለማፋጠጥ ይዳዳቸው ይሆናል፡፡ እኔ ግን አስተማማኝና ማንም የማይጋፋው መልስ አዘጋጅቻለሁ፡፡ (ሊተናነቀው ግን ይችላል) ህዝቡ አቶ አብዲን ጨምሮ መላው ኢትዮጵያዊ ነው፡፡

እናም ይሄ ህዝብ ላሻው ድምፁን በመስጠት አንዱን ከሥልጣን አውርዶ ሌላውን ወደ ስልጣን ያመጣል - ህገ መንግስቱ እንደሚለው፡፡ እኔ በበኩሌ ይሄን የስልጣን ውዝግብ ለመፍታት የሚበጅ ማለፊያ ፕሮፖዛል አርቅቄአለሁ፡፡ በፕሮፖዛሌ መሰረትም ሥልጣን የፓርቲ ወይም የመንግሥት ቋሚ (ዘላለማዊ) ርስት ሳይሆን የህዝብ ሃብት ነው፡፡ ስለዚህም ህዝብ ይሄን ሃብቱን ለመረጠው ፓርቲ፣ ግንባር፣ ድርጅት፣ ነፃ አውጪ ሃይል፣ ኢንቬስተር፣ ምሁራን፣ ሳይንቲስት ወዘተ… በሊዝ ይሰጣል (መሬት በሊዝ እንደተባለው ማለት ነው) ፕሮፖዛሌ እንደሚለው፤ መንግስት በቅርቡ የመሬት የሊዝ አዋጅ እንዳወጣው ሁሉ ህዝብም አዲስ የሥልጣን ሊዝ አዋጅ ያወጣል፡፡ ምናልባት የስልጣን የሊዝ አዋጅ በነጋሪት ጋዜጣ ላይ ከወጣ በኋላ አንዳንድ “ብዥታዎች” ከተፈጠሩ ህዝቡ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሰብስቦ ያወያያል - ብዥታውን ለማጥራት፡፡  (በነገራችን ላይ አዋጅ ካወጡ በኋላ የማወያየት ስትራቴጂን የኮረጅኩት ከኢህአዴግ ነው) በፕሮፖዛሉ መሰረት ህዝቡ ሥልጣኑን ለየፓርቲዎቹ በሊዝ ሸንሽኖ ሊያከፋፍል ይችላል፡፡ ለምሳሌ ለኢህአዴግ - የመንገድና የኮንዶሚኒየም ግንባታ ሥልጣን፣ ለኢዴፓ - የኢንዱስትሪና የቴክኖሎጂ ጉዳዮች ሥልጣንን፣ ለመድረክ - የውጭ ግንኙነት ጉዳዮችን ሥልጣን ወዘተ በሊዝ ሊሰጥ አዋጁ ይፈቅድለታል፡፡ ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴም ይቋቋማል - ሥልጣን አንሶናል የሚሉ ፓርቲዎችን ቅሬታ የሚሰማ፡፡ በዚሁ የጥንታዊቷ አገር የአቢሲኒያ የሥልጣን ውዝግብ ተፈታ ማለት ነው (የትጥቅ ትግል አከተመ አትሉም!)

አሁን ደግሞ ከሥልጣን ወደ ስጦታ እንለፍ፡፡ (ስጦታም በሊዝ ይሁን እንዴ?) ከአፍሪካውያን ጋር በፍቅር ወድቄአለሁ እያለች ስትወተውት የቆየችው ኮሙኒስቷ ቻይና፤ ፍቅሯ የፉገራ እንዳልሆነ ለማሳየት የ200ሚ. ዶላር ዘንካታ ህንፃ ሰሞኑን ለአፍሪካ ህብረት (AU) አበርክታለች፡፡ (ጥሎሽ ይሆን እንዴ?) 20 ፎቆች አሉት የተባለው ትልቅና ዘመናዊ ህንፃ ከ30 በላይ የመሰብሰቢያ አዳራሾች የያዘ ሲሆን ሰፊው አዳራሽ 2550 ሰዎችን በአንድ ጊዜ ያስተናግዳል ተብሏል፡፡ የኢቴቪ ጋዜጠኛ ምንጭ ባይጠቅስም ይሄ አዳራሽ ኒውዮርክ ከሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ፅ/ቤት አዳራሽ ይበልጣል ብሏል፡፡ ይሄ በጥምቀት ሰሞን የተበረከተ ግሩም ህንፃ፣ ለሰጪዋ ለቻይናም ሆነ ለተቀባዮቹ ለአፍሪካውያን ትልቅ ፋይዳ እንዳለው እገምታለሁ ብቻ ሳይሆን አምናለሁም (ነገርዬው የሰጥቶ መቀበል መርህን የተከተለ መሆኑ ሳይዘነጋ ማለት ነው) አሁን ዋናው ጉዳይ የአፍሪካ መሪዎቻችን (አምባገነኖቹን ጨምሮ) እዚህ ወደ ላይም ወደ ጐንም ፈረስ የሚያስጋልብ ግሩም ህንፃ ውስጥ እየተሰባሰቡ ምን ይመካከራሉ የሚለው ነው፡፡ በየአፍሪካ አገሩ ያሉ አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ግን ሰሞኑን በቻይናና በስጦታዋ ዙሪያ ትችት መሰንዘራቸው አልቀረም (የስጦታ ፈረስ ጥርሱ አይታይም ሲባል አልሰሙም መሰለኝ)  እናም የቻይና ምርት እድሜ የለውም (አይበረክትም) የሚለውን የተለመደ ስም የማጥፋት ዘመቻ ተንተርሰው ህንፃው ፀሃይና ዝናብ ሲፈራረቅበት ሊፈራርስ ይችላል ሲሉ ጨለምተኛ ትንበያቸውን አሰምተዋል፡፡ ሌሎች ተቃዋሚዎች ደግሞ “ቻይና እንደ ህንፃው ስጦታ ሁሉ የስብሰባ አጀንዳ የማበረክተውም እኔ ነኝ ብትልስ” የሚል ጥርጣሬ  አዘል ጥያቄ አቅርበዋል (20 ፎቅ በነፃማ የለም!) ለነገሩ ይሄ ብዙ የሚያሳስብ አይደለም፡ (ለአፍሪካ መንግስታት ማለቴ ነው!) ለምን መሰላችሁ? ቢያንስ እንደ “ችኮዎቹ” የምዕራብ መንግስታት “እርዳታ የምንሰጠው ዲሞክራሲ ካሰፈናችሁ፣ ነፃና  ፍትሃዊ ምርጫ ካደረጋችሁ፣ የዜጐችን መብትና ነፃነት ካከበራችሁ…” ወዘተ የሚል ግጥም የሚመስል ቅድመ ሁኔታ (ቅድመ ግዴታ በሉት) በማስቀመጥ ቻይና ችክ አትልም (የገባት ናታ!) አጀንዳውም ቢሆን እኮ በስጦታ እንጂ በግዴታ አይደለም፡፡ ስለዚህ የቻይና ስጦታ ለአፍሪካ መሪዎች (በተለይ ለአምባገነኖቹ) የሚመች ነው - ይላሉ የፖለቲካ ተንታኞች፡፡

አዲሱ የአፍሪካ ህብረት ህንፃ መቼም ተዓምራዊ ብቻ ሳይሆን ታሪካዊም እንደሆነ እኔም እመሰክራለሁ - ከሰማሁት ተነስቼ ማለት ነው፡፡ ህንፃው የቆመበት ስፍራ በደርግ ዘመን “ዓለም በቃኝ” እየተባለ ይጠራ የነበረውና በተለይ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች የሚታጐሩበት ወህኒ ቤት እንደነበር ሰምቻለሁ - ከኢቴቪ፡፡ የአገራችን መንግስት ዓለም በቃኝን አፈራርሼ ነው ለህብረቱ ዘመናዊ ህንፃ መገንቢያ በስጦታ ያበረከትኩት ብሏል፡፡   ነገርዬውን ታሪካዊ የሚያደርገው ግን የመሬት ስጦታው አይደለም! የፖለቲከኞች ወህኒ ቤትን አፈራርሶ በቦታው ላይ የአፍሪካ አገራት የጋራ ንብረት የሆነውን “ቻይናዊ ህንፃ” እንዲቆም መደረጉ ነው እንጂ፡፡ በሌላ አነጋገር የፖለቲካ ነፃነት ማፈኝያ የነበረውን ሥፍራ ነው መንግስት (ኢህአዴግ) አፈራርሶ “የነፃነት ህንፃ” (የአሜሪካው Liberty statue አይነት) እንዲገነባበት የፈቀደው፡፡

እኔ ይሄን የኢህአዴግ በጐ ተግባር በቅን ልቦና ባደንቅም አንዳንድ ወገኖች ክፉኛ ሲተቹት በወሬ ወሬ ሰምቻለሁ፡፡ እነዚህ ወገኖች የመቃወም ክፉ ሱስ (ተቃውሞ ለተቃውሞ ሲባል እንደሚሉት ዓይነት) የተጠናወታቸው መሆኑን ባውቅም አስተያየታቸውን አከብራለሁ (ወድጄ ነው በህገመንግስቱ ተገድጄ!) እናም ምን አሉ መሰላችሁ? ኢህአዴግ እውነተኛ ነፃነት ወዳጅ ከሆነ የደርግን “ዓለም በቃኝ” ብቻ ሳይሆን የራሱ ፖለቲከኞችን የሚያጉርበትን ወህኒ ቤት ሊያፈራርስ ይገባል ሲሉ አቋማቸውን ገልፀዋል፡፡ በሌላ አነጋገር የቀድሞውን አገዛዝ ወህኒ ቤት ማፍረስ ምን ይገርማል - የራስን እንጂ እንደማለት ይመስላል (ኢህአዴግ ይሞክራ!)

በፅሁፌ መግቢያ ላይ ያነሳሁት የሂዩማን ራይትስ ዎች ጉዳይ ከልቤ አልወጣ ብሎ ስላንገበገበኝ ለእንዲህ ዓይነት ችግር የሚያጋልጠን የሚመስለኝን አንድ ነገር ጠቅሼ የፖለቲካ ወጌን ልቋጭ፡፡ እንደኔ ታዝባችሁልኝ ከሆነ አንዳንድ ጋዜጠኛ ሳይሆን ካድሬ የሚመስሉ የኢቴቪ ዘጋቢዎች፤ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ነን ባዮች ላይ በተደጋጋሚ ትንኮሳ ሲፈፅሙ ይታያል (ፀብ ያለሽ በዳቦ ዓይነት) አሁን ለምሳሌ ሰሞኑን በኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ግስጋሴ ዙሪያ ሰፊ ዘገባ ያቀረበ አንድ የኢቴቪ ጋዜጠኛ ዝግጅቱን የቋጨው እንዲህ ሲል ነው፡፡ “… እነዚህ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች አሁን አሁን እየተናነቃቸውም ቢሆን የኢትዮጵያን የልማት ዕድገት እየዘገቡ ነው” ይልና የቢቢሲን ዘገባ ገጭ ያደርግልናል፡፡ አሁን ይሄን ምን ትሉታላችሁ?

እውነቱን ለመናገር እንዲህ ያለ ትንኮሳ አገሪቱን ጥላሸት ከመቀባት ተለይቶ የሚታይ አይደለም፡፡ ይሄ ታዲያ እንኳን ጥሩ ጋዜጠኛ “መጥፎ ካድሬ”ም ለመሆን ብቃት ያንሰዋል፡፡ (እንዴ አገሪቷን  ከነቢቢሲ ጋር እያላተመ?)  ምናልባት ሂዩማን ራይትስ ዎች የጠመደን በእንዲህ ያሉ ሥነ ምግባር የጐደላቸው ጋዜጠኞች ቢሆንስ? (የጋዜጠኞች ማሰልጠኛ ዘመናዊ ተቋም በአፋጣኝ!) መልካም የጥምቀት በዓል እመኛለሁ!!

 

 

Read 4375 times Last modified on Saturday, 21 January 2012 10:34