Saturday, 28 March 2015 09:19

እማሆይ ኀሪተ ሥላሴና ሌሎች ያበረከቷቸው ቅኔዎች ሲፈተሹ

Written by  ጵርስፎራ ዘዋሸራ
Rate this item
(18 votes)

    በኢትዮጵያ ከሚታወቁት የሴት የቅኔ መምህራት ውስጥ አንደኛዋ እማሆይ ኅሪተ ሥላሴ ደባስ ናቸው። እማሆይ ኅሪት በአሁኑ ጊዜ የታላቁ ገዳም የዲማ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ሁለተኛዋ የቅኔ መምህርት ሆነው በማስተማር ላይ ይገኛሉ፡፡
ተወልደው ያደጉት እዚያው ዲማ አካባቢ ልደታ ለማርያም ቤተመስቀል ከተባለች ቦታ ነው። የተወለዱት በ1966 ዓ.ም ሲሆን በልጅነታቸው ዘመናዊ ትምህርት ቤት ገብተው ነበር፡፡ በአጋጣሚ ግን በተከሠተ የዓይን ሕመም የዓይን ብርሃናቸውን ሲያጡ፤ ወላጅ አባታቸው ከዘመናዊ ትምህርት ቤት አስወጥተው ወደ ባህላዊ ትምህርት ቤት እንዲገቡ ያደርጓቸዋል። እማሆይ ኅሪት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሚሰጠውን ትምህርት ተከታትለው በቅኔ መምህርነት ተመርቀዋል፡፡
ቅኔ የተማሩት እዚያው ዲማ ጊዮርጊስ ገዳም የሐዲሳትና የቅኔ መምህር ከነበሩት ከየኔታ ዘሚካኤል ዘንድ ነው፡፡ ከዚያም ወደ ደብረወርቅ ማርያም ተጉዘው ከየኔታ ከብካብ ዓለማየሁ ዘንድ ቀጽለዋል፡፡ አስከትለው በቁይ ወረዳ ውስጥ ወደሚገኘው ደቦዛ ሚካኤል ተጉዘው ከእመይቴ ወለተ ሕይወት (በአሁኑ ሰዓት የአክሱም ጽዮን ማርያም የቅኔ መምህርት ከሆኑት) ዘንድ ቅኔ ተምረዋል፡፡ እንዲሁም እዚያው ደቦዛ ሚካኤል ከጨጐዴ አካባቢ ከመጡና አሁን ደብረ ማርቆስ ቅኔ ከሚያስተምሩት ሊቀ ሊቃውንት ሰሎሞን ዳዊት ዘንድ ቅኔን ተምረው በሚገባ አመሥጥረዋል።
እማሆይ ኅሪት ደባስ ከደቦዛ ሚካኤል እንደገና ወደ ዲማ ጊዮርጊስ ተመልሰው ሐዲሳትን ተምረዋል፡፡ ሐዲሳት ከዐራቱ ጉባኤዎች (ብሉያት ሐዲሳት ሊቃውንት መነኮሳት) አንደኛው የትምህርት ክፍል ነው፡፡ ሐዲሳትን ከተማሩ በኋላ ወደ ታላቁ የቅኔ መምህር ሊቀ ሊቃውንት ያሬድ ሽፈራው ወደሚያስተምሩበት ጨጐዴ ቅድስት ሐና ቅኔ ቤት በመሄድና ለሦስት ዓመታት በመማር በቅኔ መምህርነት ተመርቀውና አስመስክረው ወደ ትውልድ ሀገራቸው ወደ ዲማ ጊዮርጊስ ተመልሰዋል፡፡ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮም የቅኔ መምህርት ሆነው በመሥራት ላይ ይገኛሉ። ከሚያስተምሩዋቸው ውስጥ አብዛኞቹ የሴት የቅኔ ተማሪዎች ሲሆኑ ከእርሳቸው ዘንድ ዳዊት የሚማሩ የሴት ተማሪዎችም ብዙዎች ናቸው፡፡
እማሆይ ኅሪት ደባስ የሐዲስ ዓለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም የካቲት 21 እና 22 ቀን 2007 በአዘጋጀውና በደብረ ማርቆስ ከተማ በሚገኘው የቤተመንግሥት አዳራሽ በተከናወነው 4ኛ ዓመት ዐውደ ጥናት ላይ ሥራዎቻቸውን ከአቀረቡ ባለሙያዎች አንደኛዋ ተጋባዥ ነበሩ፡፡ እማሆይ ያቀረቡዋቸው ቅኔዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡
ጉባኤ ቃና
ደራሴ ድርሰት ይብል በዘደረሰ ድርሰቱ፡፡
ፍቅረ ደብረ ድማህ ልዕልት እስከመቃብር ውእቱ፡፡
ፍቺ፡- የድርሰት ደራሲ በደረሰው ድርሰት እንዲህ ይላል፡፡ የታላቋ የደብረ ድማህ ልዕልት ፍቅር እስከ መቃብር ነው፡፡
ምሥጢር - ደራሲ ሐዲስ ዓለማየሁ ለደብረ ድማህ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያላቸው ፍቅር እስከመቃብር ነው፡፡
ጉባኤ ቃና
ለዓለመዓለም ይነብር ወይሄሉ ዝክረ ስመ ጻድቅ መፍትው፡፡
እስመ ከመ ሐዲስ ይትነሣእ ኩለሄ ስመ ዚአሁ ሕያው፡፡
ፍቺ - የተወዳጁ የጻድቅ መታሰቢያ ስም ለዘለዓለም ይኖራል፡፡ ልክ ሕያው የሆነው የሐዲስ ዓለማየሁ ስም ሁልጊዜ እንደሚነሣ የጻድቅ መታሰቢያ ስም ለዘለዓለም ይኖራል፡፡
ምሥጢር - የቅኔው መነሻ “ዝክረ ጻድቅ ለዓለም ይሔሉ፡፡” የሚለው
መዝሙረ ዳዊት ሲሆን ቅኔው የጻድቅ ስም ለዘለዓለም ሲነሣ እንደሚኖር ሐዲስ ዓለማየሁም በሥራቸው ሕያው ስለሆኑ ለዘለዓለም ይታወሳሉ እንደማለት ነው፡፡
ዘአምላኪየ
ዘመነ ምሕረት ኮነ ዘመነ ሥጋዌ ቅውም፡፡
ግእዝ ወእንግሊዝኛ አንበሳ ወላሕም፡፡
አምጣነ ወፈሩ ደርገ በህየ ደብረማርቆስ ገዳም።
ፍቺ - ቋሚ የሆነው ዘመነ ሥጋዌ የምሕረት ዘመን ሆነ፡፡ በደብረ ማርቆስ ጫካ ውስጥ አንበሳና ላም በጋራ ተሰማርተዋልና፡፡
ምሥጢር - በዚህ በተሻሻለው ዘመን አንበሳና ላም የሆኑት ግእዝና እንግሊዝኛ አቻላቻ ሆነው በአንድ ጉባኤ ላይ ቀረቡ፡፡ አንበሳው ግእዝ ሲሆን በላም የተመሰለው ደግሞ እንግሊዝኛ ነው፡፡
ዋዜማ
ሕንጻ ደብረ ማርቆስ ተጋብኦ
ከመ ይባርኩ መጽኡ ወተጋብኡ ቅድምና፡፡
ምሁራን ዘኢትዮጵያ ጽንፈ ባሕር ወጣና፡፡
ምሁራነ ጊዜ ዐቢይ እምድኅረ ሰምዑ በዜና፡፡
ክብረ ተጋብኦ ማርቆስ አምሳለ ሲና፡፡
ሐዋርያ ዘርእየ በፓና፡፡
ፍቺ - የደብረ ማርቆስን የመሰብሰቢያ ሕንጻ ይመርቁ ዘንድ የኢትዮጵያ ምሁራን ከባሕር ጠረፍና ከጣና አካባቢ ጭምር አስቀድመው መጡ፣ ተሰባሰቡ፡፡ የዐቢይ ዘመን ምሁራን በዜና ከሰሙ በኋላ መጡ፡፡ የሲና አምሳያ የሆነው የማርቆስ የክብር ጉባኤ ሐዋርያው በፓና ያየው ብርሃን ነውና፡፡
ምሥጢር - ምሁራን የደብረ ማርቆስን የባህል ዐውደ ጥናት
ያደምቁ ዘንድ ከየአቅጣጫው መጡ፡፡ የዕውቀት ብርሃንም ፈነጠቁበት፡፡
አጭር መወድስ
ለነ ለነ ለሕዝበ ጉባኤ ዘቆመ፡፡
ያብጽሐነ አምላከ ጉባኤ ከመ ዩም አመ፡፡
ፍቺ፡- ለእኛ ለእኛ ለጉባኤተኞች የቆመው የጉባኤ አምላክ ልክ እንደዛሬው ሁሉ ለሚቀጥለው ዓመት ጉባኤም ያድርሰን፡፡
ምሥጢር - የጉባኤው ተሳታፊዎች ሁሉ ለሚቀጥለው የጉባኤ ዓመት ፈጣሪ እንዲያደርሳቸው መልካም ምኞት መመኘት ነው።
በዐውደ ጥናቱ ላይ ቅኔዎቻቸውን ከአቀረቡት ውስጥ መምህር ኮከበ ጽባሕ ሰውነት አንዱ ናቸው። የኮከበ ጽባሕ ቅኔዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡
1. ጉባኤቃና
አመ ወድቀ ግእዝ አረጋዊ በዘሳባውያን ፍና፡፡
ለአንሥኦቱ ትረውጽ እንታክቲ ወለተ
ምሁራን ኅሊና፡፡
ፍቺ፡- ሽማግሌው ግእዝ በሳባውያን ጐዳና ላይ በወደቀ ጊዜ፤ የምሁራን ኅሊና የሆነች ሴት ታነሣው ዘንድ ትሮጣለች፡፡
ምሥጢር - አንድ ሽማግሌ በመንገድ ላይ ሲወድቅ አንዲት ሴት ታነሣው ዘንድ እንደምትሮጥ ምሁራንም በመውደቅ ላይ ያለውን የግእዝ ቋንቋ ያነሱት ዘንድ ጥናት እያካሄዱበት ነው፡፡
2. መወድስ
በሥርዓተ አበው ቀደምት ዘሐጸንኪዮሙ፣
ለደሃራውያን ውሉድ እመ ብዙኃን ኢትዮጵያ።
እንበለ አሐቲ ድካም ወእንበለ ንስቲት ጉዕትያ።
ጀርመን ዕቅብት ዘብእስኪ መጻሕፍተ ሀብታተ ቤትኪ ተካፈለት ነያ፡፡
ወዘንተ ተመነያ፣ አዋልደ ሮሜ ወዐረብ አሀተ ገሊላ ወሰማርያ፡፡
ወእንዘ ጀርመን ትፈትነኪ ትፈትነኪ ኬንያ፡፡
ከመ ሶርያ ለገባዖን ወከመ ገባኦን ለሶርያ፡፡
ወእንተ መውዕያ ለፀር አመነፀርኪ ህብልያ፡፡
አዕዛኒነ ኢይስምዓ ወአዕይንቲነ ኢይርዓያ፡፡
እስመ ኢናፍቅር ንሕነ ዘጸላዕትነ ጉህልያ፡፡
አዕዛኒነ ኢይስምዓ ወአዕይንቲነ ኢይርዓያ፡፡
ፍቺ፡- የብዙዎች እናት የሆንሺው ኢትዮጵያ ያለምንም ድካምና ልፋት በቀደሙት አባቶች ሥርዓት ያሳደግሻቸው የኋለኞቹ ልጆች እያሉ በዕቁባትነት (በጭን ገረድነት) የተቀመጠቺው ጀርመን (የባልሽ ቅምጥ የሆነችው ጀርመን)የቤትሽን መጻሕፍት ሀብታት (ንብረቶችን) ተካፈለች፡፡
ሰማርያና የገለሊላ እህቶች የሆኑት የዐረብና የሮማ ልጆችም ሀብት የመካፈልን ነገር (መጻሕፍት መውሰድን) ተመኙ፡፡
ጀርመን ስትፈትንሽ በቅርብ ያለቺው ኬንያም ትፈትንሻለች፡፡ ሶርያ ገባዖንን፣ ገባኦን ደግሞ ሶርያን እንደምትፈትን ኬንያም ልትፈትንሽ (መጻሕፍትን ልትዘርፍሽ) ትችላለች፡፡
የጠላት ማሸነፊያ የሆነውን ዘረፋን እያየሽ ከአስተናገድሽ (እያየሽ ዝም ካልሽ) ጆሮዎቻችን አይስሙ፣ ዓይኖቻችንም አይዩ፡፡
የጠላታችንን አጥፊነት እኛ አንወድምና፡፡ ይህ ከሚሆን ጆሮዎቻችን ከመስማት፣ ዓይኖቻችን ከማየት ቢጐድሉ ይሻላል፡፡
ምሥጢር፡- ባል ሲሞት የባልን ንብረት እካፈላለሁ ብላ በቅምጥነት ልጅ የወሰደች ወይንም ያልወሰደች ሴት ዋናይቱን የቤት እመቤት እንደምትሞግታት በቅምጥነት የተመሰለቺው ጀርመንም ምንም ሳትሠራና ሳትደክም የኢትዮጵያ ሊቃውንት የጻፉዋቸውን መጻሕፍት ዘርፋ ወሰደች፡፡ የእርስዋን ተግባር ያዩ ሌሎች አገሮችም ዘረፉ፡፡ ለዘረፋ ያሰፈሰፉ ሌሎች ሀገሮችም ስለአሉ መጻሕፍትን በትጋት እንጠብቃቸው፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

Read 15548 times