Saturday, 28 March 2015 09:03

የአገራችን ፓርቲዎች፣ ተቀራራቢ አስተሳሰብ መያዛቸው አያስነውርም

Written by 
Rate this item
(4 votes)

የተሳሳተና ጎጂ አስተሳሰብ መያዛቸው ነው ችግሩ

   ለግንቦቱ ምርጫ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በተካሄደው ክርክር ላይ የተሳተፉ ሶስት ፓርቲዎች፣ ተመሳሳይ ሃሳቦችን እንዳቀረቡ የሚገልፅ ነበር የዛሬ ሁለት ሳምንት ፅሁፌ። ምን ያህል ተቀራራቢ እንደሆኑ ለማሳየትም፣ ከተከራካሪዎቹ አንደበት በምሳሌነት ጥቂት አባባሎችን ጠቅሻለሁ። ግን ለወቀሳ አልነበረም። እንዲያውም፣ የዋና ዋና ተፎካካሪ ፓርቲዎች  አስተሳሰብ ተቀራራቢ ካልሆነ፣ የምርጫ ፖለቲካ በአጭሩ ከመቀጨት አይድንም።
በእርግጥ፣ ፓርቲዎቹ የተለያየ የአስተሳሰብ አቅጣጫ እንደሚከተሉ ነው የሚናገሩት። ኢህአዴግን በመወከል የተከራከሩት አቶ አባይ ፀሐዬ፣ ፓርቲያቸው ‘አብዮታዊ ዲሞክራሲ’ ወይም ‘ልማታዊ ዲሞክራሲ’ የተሰኘ አስተሳሰብ እንደሚከተል ገልፀዋል - በከፊል የነፃ ገበያ አሰራርን ብንቀበልም መንግስት በኢኮኖሚ ውስጥ በሰፊው ጣልቃ መግባት አለበት በማለት። የመድረክ አመራር አባል ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ በበኩላቸው፣ ትክክለኛው አማራጭ የ‘ሶሻል ዲሞክራሲ’ አስተሳሰብ መሆኑን በመጥቀስ፣ ከከፊል የነፃ ገበያ አሰራር ጋር መንግስት በኢኮኖሚ ውስጥ ጉልህ ሚና ሊኖረው ይገባል ብለዋል - መንግስት ከዜጎች ገቢ 50% ያህል ታክስ ሲሰበስብ የሚታይባቸውን አገራት በምሳሌነት በመጥቀስ። ለነፃ ገበያ ስርዓት የተሻለ ትኩረት የሚሰጥ ‘የሊበራል ዲሞክራሲ’ አስተሳሰብን እንከተላለን ያሉት የኢዴፓው ዶ/ር ጫኔ ከበደ በበኩላቸው፣ መንግስት በኢኮኖሚ ውስጥ በተመረጠ አኳሃን ጣልቃ መግባቱ ግን አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል።
የፓርቲዎቹን ክርክር የሚከታተል ሰው፣ የፓርቲዎቹን የዝንባሌ ልዩነት መታዘብ እንደሚችል አያጠራጥርም። ነገር ግን፤ ፓርቲዎቹ የካፒታሊዝምና የሶሻሊዝም ሃሳቦችን ያቀላቀለ ተመሳሳሳይ ቅይጥ አስተሳሰብ የያዙ መሆናቸው ሚስጥር አይደለም። በአንድ በኩል ስለ ነፃ ገበያ እየተናገሩ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በሰዎች መካከል የሃብት ልዩነትን ለማጥበብ የመንግስት ጣልቃ ገብነት ያስፈልጋል በማለት ፓርቲዎቹ ይስማማሉ። በአንድ በኩል የንብረት ባለቤትነት መብትን እንደሚያከብሩ እየተናገሩ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሃብት ከሚያፈሩ አምራቾች ላይ ሃብት በመውሰድ ለሌሎች የማከፋፈል አሰራርን እንደሚደግፉ ሲገልፁ፣ “ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል” ወይም “ማህበራዊ ፍትህ” እያሉ ያሞግሱታል። የፓርቲዎቹ የአስተሳሰብ ተመሳሳይነት የዚህን ያህል በግልፅ የሚታይ ነው። ለነገሩ፤ እኔ ሳልሆን ፓርቲዎቹ ራሳቸው በአስተሳሰብ ተቀራራቢ መሆናቸውን በገሃድ ይመሰክራሉ። ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ በፋና ሬድዮ በተካሄደ ሌላ ክርክር ላይ እንደገለፁት፣ የሶሻሊዝምና የካፒታሊዝም አስተሳሰቦችን ያዳቀለ ቅይጥ አስተሳሰብ ነው የያዙት። የተወሰነ የነፃ ገበያ አሰራርንና የመንግስት የኢኮኖሚ ገናናነትን ያቀላቀለ ቅይጥ ኢኮኖሚን ነው የሚፈልጉት።
የተዋጣላቸው ተከራካሪ የሆኑት የኢዴፓ መስራች አቶ ልደቱ አያሌው፣ ኢህአዴግ ከጊዜ ወደ ጊዜ አስተሳሰቡን እየቀየረ ወደ ኢዴፓ አስተሳሰብ እየተጠጋ መጥቷል፤ ጥሩ ነው ሲሉ ተናግረዋል - በፋና ሬድዮው ክርክር። የኢህአዴግ ተወካይ አቶ ዛዲቅ አብርሃ በበኩላቸው፣ ተቃዋሚዎች ናቸው አስተሳሰባቸው በመቀየር ወደ ኢህአዴግ አስተሳሰብ እየተቀራረቡ የመጡት ብለዋል። “ማን ተጠጋ?” የሚለውን ጉዳይ አከራካሪ ጥያቄ በማድረግ፣ የፓርቲዎቹን የሃሳብ ልዩነት ለማጉላት እንችል ይሆናል። ግን የዚህችው መከራከሪያ ጥያቄ መነሻ ነጥብ መዘንጋት የለብንም። በአስተሳሰብ ተቀራራቢ መሆናቸውን ፓርቲዎቹ ራሳቸው ያምናሉ። ዋናው ነጥብ ይሄው ነው። አቶ ልደቱ እንዳሉት፣ የፓርቲዎቹ አስተሳሰብ መቀራረቡ ጥሩ ነገር ነው። ለምን?
አንደኛ ነገር፣ ፓርቲዎች የሚፎካከሩበት የምርጫ ፓለቲካ በሰላምና በተረጋጋ ሁኔታ ለረዥም ጊዜ ሊዘልቅ የሚችለው፣ የተፎካካሪ ፓርቲዎች መሰረታዊ አስተሳሰብ ተቀራራቢ ከሆነ ብቻ ነው። አለበለዚያ፣ አስተሳሰባቸው በእጅጉ የተራራቀ ከሆነ፣ አንዱ በምርጫ ተሸንፎ ሌላው ስልጣን ላይ በወጣ ቁጥር በ“ስር ነቀል ለውጥ” አገር ይታመሳላ። ስልጣን ላይ በተፈራረቁ ቁጥር አገሪቱ በ‘አብዮት’ አዙሪት የምትመሳቀል ከሆነች፣ የምርጫ ፓለቲካ ከጊዜያዊ ፋሽንነት ያለፈ እድሜ አይኖረውም። በሌላ ምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ የምግብ አሰራር ውድድር፣ በተለያዩ የምግብ ጣዕሞችና አይነቶች መካከል መሆን አለበት እንጂ፣ ውድድሩ በምግብ እና በአይነ ምድር መካከል ከሆነ ከአንድ ሙከራ በላይ አይዘልቅም። በሌላ አነጋገር፣ ውድድሩ የኮካና የፔፕሲ መካከል ሳይሆን፤ በለስላሳ መጠጥና በመርዝ መካከል እንዲሆን የምንጠብቅ ከሆነ፣ የምንፈልገው ወይም የሚበጀን ነገር ያልገባን አላዋቂዎች ሆነናል ማለት ነው። ከዚሁ ነጥብ ሳንወጣ ሁለተኛውን ቁምነገር ማስተዋል እንችላለን።
የተረጋጋ ስልጡን የምርጫ ፓለቲካ ለዘለቄታው እውን እንዲሆን፣ ሰፊ ድጋፍ ያላቸው ተፎካካሪ ፓርቲዎች በመሰረታዊ አስተሳሰብ ተቀራራቢ ሊሆኑ ይገባል። ይሄ የመጀመሪያው ቁምነገር ነው። ግን፣ ተቀራራቢ መሆናቸው ብቻ በቂ አይደለም። ለምሳሌ፣ ከአርባ አመት በፊት በአገራችን የነበሩ ዋና ዋና ፓርቲዎች፣ ተመሳሳይ የአስተሳሰብ ቅኝትን የተከተሉ እንደነበር ይታወቃል - ኢህአፓ፣ መኢሶን ወዘተ..። እጅጉን ተቀራራቢ ከመሆናቸው የተነሳ፣ አንዱን ከሌላው ለመለየት ያስቸግራል - የለየላቸው ሶሻሊስቶች (ኮሙኒስቶች) በመሆናቸው። ግን፣ ስልጡን የፖለቲካ ምርጫ አልተፈጠረም። ለምን? አስቡታ! የአንድ ፓርቲ አምባገነንነት መስፈን አለበት የሚል ተመሳሳይ አስተሳሰብ የያዙ ፓርቲዎች፣ በጭራሽ በጭራሽ ብዙ ፓርቲዎች የሚፎካከሩበት የምርጫ ፓለቲካ ሊፈጥሩ አይችሉም። የሁሉንም ሰው እውቀትና ንግግር እየተቆጣጠረ የሚያፍን፣ የሁሉም ሰው ኑሮና ንብረት ላይ እያዘዘ የሚወርስ፣ የሁሉም ሰው ማንነትና ሰብእና ላይ አድራጊ ፈጣሪ ሆኖ የሚገዛ አምባገነን መፈጠር እንዳለበት ተስማምተው የለ! ‘እኔ አምባገነን ልሁን’፣ ‘እኔ ልሁን’ እያሉ ይጨፋጨፋሉ፣ ይጨፈጭፋሉ እንጂ፣ እንዴት ብለው የተረጋጋ ስልጡን የምርጫ ፖለቲካ ይፈጥራሉ? ሁለተኛው ቁምነገር ይሄው ነው። ፓርቲዎቹ በአስተሳሰብ መቀራረባቸው ብቻ ሳይሆን፣ ቅርርባቸው በስልጡን የነፃነት አስተሳሰብ ዙሪያ መሆን አለበት።
አሳዛኙ ነገር፤ የአገራችን ፓርቲዎች በስልጡን የነፃነት አስተሳሰብ ዙሪያ ሳይሆን በቅይጥ አስተሳሰብ ዙሪያ ነው የተቀራረቡት። ይበልጥ አሳዛኝና አሳሳቢ የሚሆነው፤ በአለም ዙሪያ የሚታየው አዝማሚያም ተመሳሳይ ነው - ደረጃው ቢለያይም ከሞላ ጎደል ሁሉም አገራት በ“ቅይጥ አስተሳሰብ” ውስጥ የሚተራመሱ ሆነዋል። ከኮሙኒስት ኩባ እና ከቻይና ጀምሮ፣ እስከ ደቡብ አፍሪካና ቬኒዝዌላ... ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከኢትዮጵያ እስከ ራሺያና ህንድ፣ ከናይጄሪያ እስከ ፈረንሳይና ጃፓን፣ ከብራዚል እስከ ግሪክና ስፔን፣ ከግብፅ እስከ እንግሊዝና አሜሪካ... የቀረ አገር የለም ማለት ይቻላል። የኢኮኖሚ መስክን ብቻ ብንመለከት፣ በአንድ በኩል በነፃ ገበያ ስርዓት፣ አስገራሚ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችንና የምርታማነት እመርታዎችን፣ የየብልፅግና ለውጦችንና የኑሮ እድገትን እናያለን። በሌላ በኩል ደግሞ የነፃ ገበያ ስርዓትን በሚሸረሽር የመንግስት ጣልቃ ገብነት ሳቢያ፣ ቅጥያጣ ድጎማንና የታክስ ጫናን፣ የመንግስታት የእዳ ክምርንና የፋይናንስ ቀውስን፣ የሃብት ብክነትንና ሙስናን፣ ስራ አጥነትንና አመፅን እናመለከታለን። በአጭሩ፣ ከብልፅግና እድል ጋር፣ የጥፋት አፋፍ ላይ የደረሰ የኢኮኖሚ ቀውስ የእለት ተእለት ትዕይንት ሆኗል። የሁለት አገራትን ሙከራ ብቻ በጨረፍታ እንመልከት። በቅድሚያ ኩባን።
አብዛኛው የኩባ ሰራተኛ ወደ ሃያ ዶላር ገደማ የወር ደሞዝ እንደሚያገኝ የገለፀው የኒውስዊክ የትናንት እትም፣ የአንጋፋ ሃኪሞች ደሞዝ በቅርቡ ተሻሽሎ ወደ 70 ዶላር (ወደ 1500 ብር) ግድም የደረሰላቸው ቢሆንም የአብዛኞቹ ዶክተሮች ደሞዝ ግን 26 ዶላር (ወደ 600 ብር የሚጠጋ) እንደሆነ ዘግቧል።
የሃኪሞቹ ደሞዝ ከአብዛኛው ሰራተኛ ደሞዝ ያን ያህልም አይለያይም። ለምን? በፅዳት ሰራተኞችና በህክምና ዶክተሮች መካከል የገቢ ልዩነት እንዳይኖር ለማድረግ ነው - “ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል”፣ “ማህበራዊ ፍትህ” ይሉታል ሶሻሊስቶቹ። በአገራችን ፖለቲከኞች ዘንድ የሚዘወተሩ አባባሎች እንደሆኑም ታዝባችሁ ይሆናል። ያው፣ በሰዎች መካከል የቁመት ወይም የብልህነት ልዩነት እንዳይኖር፣ ረዣዥሞቹን መከርከም ወይም ብሩህ አእምሮዎችን ማደብዘዝ እንደማለት ነው። ይህንን ነው ፍትህ የሚሉት። የ50 ዓመቱ ኩባዊ ራፋኤል ግን፣ ለ“ማህበራዊ ፍትህ” የመስዋዕት በግ መሆን አንገሽግሿቸዋል። በወጣትነት እድሜያቸው በህክምና ተመርቀው መስራት የጀመሩ ጊዜ ምንኛ እንደተደሰቱ ባይረሱትም፣ ዛሬ ግን እንደ ሩቅ ዘመን ትዝታ ነው የያኔ ሙያቸውን የሚያስታውሱት። ስራቸውን ለቅቀው ከወጡ አምስት ስድስት አመታት ተቆጥረዋል። በእርግጥ አንዳንዴ፣ የህክምና ሙያቸውን ሲያስታውሱት፣ ከትዝታነትም አልፎ ያንገበግባቸዋል - ከሚወዱት ሙያ በመለየታቸው። ግን ሌላ አማራጭ አልነበራቸውም። በ12 ዶላር (250 ብር ገደማ) ደሞዝ የህክምና ሙያቸውን እንደጀመሩ የሚናገሩት ራፋኤል፣ ከበርካታ አመታት በኋላ ደሞዛቸው ወደ 15 ዶላር “እንዳደገ” ይገልፃሉ።
በእርግጥ ለአርባ አመታት ኩባን አንቀጥቅጠው የገዟት ፊደል ካስትሮ በእርጅናና በህመም ምክንያት ከስልጣናቸው ከተነሱ ወዲህ፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ አንዳንድ የለውጥ ጭላንጭሎች መታየት ጀምረዋል። የጀማሪ ዶክተሮች ደሞዝ እንኳ ወደ 600 ብር የሚጠጋ ሆኖላቸው የለ! ይሄ፣ በምድረ ኩባ “አጀብ” የሚያሰኝ ለውጥ ነው። ራፋኤል ግን፣ አሁንም ፈፅሞ አልተዋጠላቸውም። የለውጥ ጭላንጭል እየተፈጠረ መሆኑን አይክዱም። እንደ ድሮ ቢሆን ኖሮ፣ መንግስት ከመደበላቸው የስራ ቦታ መልቀቅ ባልቻሉ ነበር። ዛሬ ግን ይቻላል። ሁሉም ነገር በመንግስት ተይዞ በቆየበት አገር፣ ትንንሽ ሱቆችን መክፈት ተፈቅዷል። አንዳንድ ሃኪሞች፣ በሱቅ ንግድ መተዳደርን ቢመርጡ ምን ይገርማል?
ራፋኤል ግን፣ የታክሲ ሾፍርናን ነው የመረጡት። የግል ታክሲ ተፈቅዷላ። ቱሪስቶች በብዛት እንዲገቡ መፈቀዱ ደግሞ ጠቀማቸው። ዛሬ አቶ ራፋኤል በታክሲ ሹፍርና በወር ከ200 ዶላር በላይ ገቢ ያገኛሉ። ልጄ በህክምና ተመርቆ ሥራ ጀምሯል የሚሉት ራፋኤል፣ ነገር ግን ልጃቸው በህክምና ሙያው ከሚያገኘው ደሞዝ ይልቅ እሳቸው በታክሲ ሹፍርና የሚያገኙት ገቢ በአስር እጥፍ ገደማ እንደሚበልጥ ጠቁመዋል። ግን እሱም ሞኝ አይደለም። በእረፍት ቀናት አባቱን በመተካት የታክሲ ሹፍርና እንዲሰራ ሲጠይቁት አላቅማማም - ለሁለት ቀን ሰርቷል። “30 ዶላር ከፍየዋለሁ፤ በወር ከሚያገኘው ደሞዝ ይበልጣል” ብለዋል ራፋኤል። የቅይጥ ኢኮኖሚ ነገር እንዲህ ነው።
ያለ ጥርጥር የዛሬው ቅይጥ ኢኮኖሚ፣ ከትናንቱ “ያልተበረዘ የሶሻሊዝም ኢኮኖሚ” ይበልጣል። ግን አስቡት። የህክምና ዶክተር ከመሆን ይልቅ፤ የታክሲ ሾፌር መሆን ይሻላል - ገቢያቸው የትና የት! ነገር ግን የሃኪምና የሾፌር ገቢ መለያየቱና መራራቁ ወይም የታክሲ ሾፌር በወር 200 ዶላር ገቢ ማግኘቱ አይደለም ችግሩ። ከሃኪሞች ተቀንሶ አይደለም የሾፌሮች ገቢ የጨመረው። እንዲያውም፤ የታክሲ ስራን ጨምሮ በጥቂት መስኮች የግል ቢዝነስ በመፈቀዱ ምክንያት የተፈጠረው ለውጥ፣ እንደ ራፋኤል ለመሳሰሉ የታክሲ ሾፌሮች ብቻ ሳይሆን ለሃኪሞችም በተወሰነ ደረጃ ጠቅሟል። እናም፣ ብዙ ነው ባይባልም፣ የሃኪሞች ደሞዝ ትንሽ እንዲሻሻል ግፊት በማሳደር አስተዋፅኦ አበርክቷል። ምናልባት ወደፊት ደግሞ የግል ክሊኒክና ሆስፒታል ሲፈቀድ፣ የሃኪሞች ገቢ ሙያቸውንና ስራቸውን የሚመጥን የሚሆንበት እድል ይፈጠራል። በኩባ አሁን የታየችው የነፃ ገበያ ጠባብና ቁንፅል ጭላንጭል፣ የዚያችኑ ያህል ትንሽዬ የኑሮ ለውጥ እንደፈጠረችው ሁሉ፤ በጭላንጭሏ የገባው ብርሃን እየደመቀ የነፃ ገበያ ስርዓት እየሰፋና እየጨመረ ቢመጣ፤ የዚያኑን ያህል ከሶሻሊዝም የድንዛዜና የድህነት የሚላቀቁበት ሰፊ የእድገትና የብልፅግና እድል ይፈጠራል። አለበለዚያ ግን፤ “መማር ከንቱ” የሚያስብል፣ በጅምር የቅይጥ ኢኮኖሚ ሳቢያ የሚፈጠር ቀውስ ውስጥ ተዘፍቃ፣ የብልፅግና ጭላንጭሏ በአጭሩ ተቀጭቶ የኋሊት ትንሸራተታለች።
በሌላ አነጋገር፣ ቅይጥ ኢኮኖሚ፣ ወደ በለጠ የነፃ ገበያ ስርዓት የሚያመራ ጊዜያዊ የመሸጋገሪያ ክስተት ከመሆን አልፎ፤ ቋሚ ስርዓት እንዲሆን መመኘት ውሎ አድሮ የኢኮኖሚ ቀውስን ከመጋበዝ የተለየ ትርጉም አይኖረውም። በአሜሪካና በምዕራብ አውሮፓ፣ ከዚያም በእነ ታይዋንና ደቡብ ኮሪያ፣ ባለፉት 20 ዓመታት ደግሞ ፖላንድና ቼክ በመሳሰሉ የምስራቅ አውሮፓ አገራት እንደታየው፤ የነፃ ገበያ ስርዓትን ተግባራዊ ባደረጉት መጠን ነው ብልፅግና እውን የሚሆነው።
ቻይናም ከረሃብ ለመላቀቅና ወደ ብልፅግና ጎዳና የመግባት እድል ያገኘችው፤ በሌላ ምክንያት አይደለም። ከጊዜ ወደ ጊዜ የመንግስት ቁጥጥርን እየቀነሰች፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ የነፃ ገበያ አሰራርን ስታስፋፋ ስለቆየች ነው፤ ለ30 አመታት ያለማቋረጥ ከአስር በመቶ በላይ የኢኮኖሚ እድገት ስታስመዘግብ የቆየችው። በእርግጥ ባለፉት አራት አመታት የኢኮኖሚ እድገቱ ረገብ ብሏል፤ ወደ 7.5% ገደማ። ዘንድሮና በሚቀጥለው አመት የኢኮኖሚ እድገቱ ወደ 7 በመቶ እንደሚወርድ የገለፀው የቻይና መንግስት፤ የመቀዛቀዝ አዝማሚያው እንዳይባባስ ስጋት ቢያድርበት አይገርምም። የኢኮኖሚ እድገት ካላስመዘገበ፣ ስልጣን ላይ የመቆየት አቅሙ እንደሚሸረሸር አልጠፋውም። እና ምን ተሻለ?
የቻይና መንግስት ለበርካታ አመታት የነፃ ገበያ አሰራርን እያስፋፋ ቢመጣም፤ አሁንም ኢኮኖሚው ውስጥ የመንግስት ቁጥጥርና ድርሻ ግዙፍ ነው። ማለትም፤ ቅይጥ ኢኮኖሚ። ይህንኑ በቋሚነት ለመያዝ፤ “እስከ ዛሬ ድረስ በተወሰነ ደረጃ ተግባራዊ ያደረግሁት የነፃ ገበያ አሰራር በቂ ነው” ብሎ አሁን ባለው የቅይጥ ኢኮኖሚ ስርዓት መቀጠል እንደማይችል የአገሪቱ ባለስልጣናት ገብቷቸዋል። ለዚህም ይመስላል፣ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ባለፈው ሳምንት በሰጡት ረዥም ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፣ እስካሁን እንዳደረግነው የነፃ ገበያ አሰራርን በማስፋፋት እንቀጥላለን ያሉት። ለቢዝነስ ድርጅቶች የታክስ ቅነሳ እንደሚደረግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰው፤ የቢዝነስ ድርጅት የሚያቋቁሙ ሰዎች ላይ የተንዛዛ የቁጥጥርና የምዝገባ ቢሮክራሲ በግማሽ ቀንሰነዋል፤ አሁንም እንደገና በግማሽ እንቀንሰዋለን ብለዋል። ይበጃቸዋል! በቅይጥ አስተሳሰብ ተተብትቦ፣ ቅይጥ ኢኮኖሚን እንደ ቋሚ ስርዓት ይዞ ለመቀጠል መሞከር፣ መጨረሻው አያምርማ። የአገራችን ፓርቲዎችም፣ በጊዜ ይህንን እውነታ ቢገነዘቡ ይሻላቸዋል፤ ለሌሎቻችንም ይሻለናል።

Read 2769 times