Saturday, 28 March 2015 09:00

ኤርትራ በኢትዮጵያ ወታደራዊ ጥቃት አልተፈፀመብኝም አለች

Written by 
Rate this item
(44 votes)

      በኤርትራ የወርቅ ማምረቻና ወታደራዊ ካምፕ ላይ የኢትዮጵያ አየር ሃይል ጥቃት መፈፀሙን የተለያዩ ድረገፆችና ሚዲያዎች ቢዘግቡም የኤርትራው ፕሬዚዳንት ቃል አቀባይ ጥቃቱ አልተፈፀመም ሲሉ ማስተባበላቸውን “ጊስካ አፍሪካ ኦንላይን” ጠቁሟል፡፡
“ቢሻ የወርቅ ማዕድን ማምረቻም ሆነ ወታደራዊ ካምፑ በኢትዮጵያ አየር ሃይል አልተደበደበም” ብለዋል ቃል አቀባዩ ለድረ ገፁ በሰጡት መረጃ፡፡
የሱዳኑ ጋዜጣ “ሳሀፋ” ሰሞኑን ባሰራጨው ዘገባ፤ የኢትዮጵያ አየር ሃይል ከአስመራ በ150 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውንና የካናዳ ኩባንያ የሆነውን ቢሻ የወርቅ ማእድን ማምረቻ መደብደቡን ሲገልፅ፣ “አሰና” የተሰኘ ድረ ገፅ በበኩሉ፤ ቢሻ የወርቅ ማእድን ማምረቻና ማይ እዳጋ በተባለ ቦታ የሚገኝ ወታደራዊ ካምፕ በኢትዮጵያ አየር ሃይል ወታደራዊ ጥቃት እንደተፈፀመባቸው ዘግቧል፡፡
ኢትዮጵያ በኤርትራ ላይ  ወታደራዊ ጥቃት ፈፅማለች ወይ በሚል ከአዲስ አድማስ የተጠየቁት የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሽመልስ ከማል በሰጡት ምላሽ፤ “ተጎዳን የሚል ይፋ አቤቱታ ሳይቀርብ እንዳልጎዳችኋቸው ማረጋገጫ ስጡ ማለት አግባብነት የለውም” ብለዋል፡፡”  
የቢሻ ወርቅ ማምረቻ አብላጫ ድርሻውን የያዘው “ኔቭሱን” የተባለው የካናዳ ኩባንያ ሰሞኑን በድረገፁ ባሰፈረው መረጃ፤ የወርቅ ማዕድን ማምረቻው በተፈፀመበት ዝርፊያና በዕድሳት ምክንያት  ለተወሰነ ጊዜ ሥራ አቁሞ እንደነበር ጠቁሞ በቅርቡ ወደ ስራው እንደሚመለስና ዝርፊያውን በተመለከተ የኤርትራ የፀጥታ ሃይሎች ምርመራ እያካሄዱ እንደሆነ አስታውቋል፡፡

Read 9536 times