Saturday, 28 March 2015 08:57

ኢዴፓ የቅስቀሳ መልዕክቶቼ ሣንሱር እየተደረጉብኝ ነው አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(15 votes)

“ድርጊቱ የማይቆም ከሆነ በምርጫው ያለኝን ተሣትፎ ለማጤን እገደዳለሁ”

የኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)፤ ለየሚዲያዎቹ የሚልካቸው የምርጫ ቅስቀሳ መልዕክቶች ሣንሱር እየተደረጉ ተመላሽ እየሆኑበት መሆኑን ጠቅሶ በየጣቢያዎቹ ያለው ሣንሱር የማይቆም ከሆነ በምርጫው ላይ ያለውን ተሣትፎ ለማጤን እንደሚገደድ አስታወቀ፡፡
ፓርቲው ትናንት ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫ፤ ፋና ብሮድካስቲንግ ኤጀንሲና የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ከትላንት በስቲያ እንዲያስተላልፉ የተላከላቸውን የቅስቀሳ መልዕክት “ኢዴፓ ከተመረጠ በኢትዮጵያ ያሉ የፖለቲካ እስረኞች ይፈታሉ” የሚለው አገላለጽና ፓርቲው ምርጫ ቦርድን የተቸበት ሀረግ ካልተስተካከለ አናስተላልፍም ብለው እንደመለሱበት ጠቁሟል፡፡
“የጣቢያዎቹ ድርጊት በህገመንግስቱ የተከለከለውን ሣንሱር ማድረግና ሃሳብን የመግለጽ ነፃነትን የሚፃረር ነው” ያለው ፓርቲው፤ ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ በምርጫው ላይ ያለውን ተሣትፎ እንዲገታ የሚያስገድደው መሆኑን ገልጿል፡፡
የሚዲያ ተቋማቱ  ቅስቀሳውን አናስተላልፍም ማለታቸው “የመወዳደሪያ ሜዳው ከመቼውም ጊዜ የበለጠ እየጠበበ መምጣቱን ያሣያል” ያለው ኢዴፓ፤ መንግስትና ገዥው ፓርቲ ለመድብለ ፓርቲ የፖለቲካ ስርአትና ለፍትሃዊ ምርጫ ከአፍ ያለፈ ቁርጠኝነት እንደሌላቸው በግልጽ እየተረጋገጠ ነው ብሏል፡፡
ምርጫ ቦርድ የሚሠጠው የገንዘብ ድጐማ፣ የአየር ሰአት ድልድልና የክርክር መድረክ  በአግባቡ አለመከናውኑን እንዲሁም ኢህአዴግ ከተቋማቱ ላይ  እጁን እንዲያነሣ በቅስቀሳ መልዕክቱን መጠየቁን ጠቅሶ ይሄ እንዴት የስም ማጥፋት ሆኖ ሳንሱር ይደረጋል ብሏል - በመግለጫው፡፡
በቅስቀሳ መልዕክቶቹ ላይ እየተደረገ ያለው “ሣንሱር”፤ በምርጫው ተሣትፎ ላይ እንቅፋት እየፈጠረበት መሆኑን የጠቆመው ፓርቲው፤ በእንደዚህ ያሉ አሠራሮች የምርጫ መወዳደሪያ ሜዳውን ለገዥው ፓርቲ ምቹ የማድረግና ለተቃዋሚዎች መሠናክል የመፍጠር እንቅስቃሴ በምርጫ ስርአቱ ላይ የተጋረጠ አደጋ ነው ብሏል፡፡
በተመሳሳይ የቅስቀሳ መልዕክቶቼ ሳንሱር እየተደረጉብኝ ነው ያለው ሠማያዊ ፓርቲም፤ በፌደራሊዝም ጉዳይ ላይ በላከው የቅስቀሳ ፅሑፍ ግጭት የሚያስነሱ መልዕክቶች ተካትተዋል በሚል የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት (ኢቢሲ) ተመላሽ እንዳደረገበት አስታውቋል፡፡  

Read 2928 times