Saturday, 28 March 2015 08:56

ዩኒቨርሲቲው የእነ ዶ/ር መረራን ኮንትራት ማራዘም አላስፈለገኝም አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(11 votes)

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካል ሣይንስ መምህር ዶ/ር መረራ ጉዲና እና የፍልስፍና መምህሩ ዶ/ር ዳኛቸው አሠፋን የኮንትራት ጊዜ ያላራዘመው በዘርፉ ተተኪ መምህራን ስላሉት መሆኑን የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ገለፁ፡፡
የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አድማሱ ፀጋዬ ትናንት ከሌሎች የስራ አመራሮች ጋር በሠጡት መግለጫ፤ የሁለቱ መምህራን ጉዳይ በየሚዲያው መነጋገሪያ መሆኑ እንዳስደነቃቸው ገልፀው፣ “ዩኒቨርሲቲው ሁለቱን መምህራን ከሌሎች ነጥሎ አይመለከትም፤ እነሱን የሚተኳቸው መምህራን ስላሉ የጡረታ ጊዜያቸውን ማራዘም አላስፈለገንም” ብለዋል፡፡
ሌሎች በርካታ መምህራን በዚህ መልኩ የጡረታ ጊዜያቸው አለመራዘሙን የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ፤ ዩኒቨርሲቲው በየትኛውም የትምህርት ክፍል በቂ መምህራን አለኝ ብሎ ካመነ ለጡረታ የደረሱ መምህራንን ኮንትራት ላያራዝም የሚችልበት የቆየ አሠራር እንዳለው አስታውቀዋል፡፡ አንድ መምህር ዩኒቨርሲቲ 7 አመት ካስተማረ በኋላ የ1 አመት እረፍት የሚሰጥበት አሠራር በዩኒቨርሲቲው መኖሩን የገለፁት ፕሬዚዳንቱ የአንድ አመት እረፍት የሚሠጠው መምህሩ በዕረፍት ጊዜው ምርምሮችን እንዲሰራ መሆኑን ጠቁመው ከጡረታ በኋላ ይህ አይነቱ እረፍት እንደማይሰጥና የአንዱ መምህር ጉዳይ ከዚህ ጋር እንደሚያያዝ ተናግረዋል፡፡
የጡረታ ጊዜ ማራዘምም ሆነ አለማራዘም የዩኒቨርሲቲው አስተዳደራዊ መብት መሆኑን የጠቀሱት የስራ አመራሮቹ፤ የጡረታ ጊዜያቸው ያልተራዘመው ሁለቱ መምህራን ጉዳዩን ለሌላ አላማ መጠቀማቸው አግባብ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ በሌላ በኩል ዩኒቨርሲቲው ገቢ የሚያስገኙለት 10 ያህል ራሳቸውን የቻሉ የንግድ ተቋማትን ማቋቋሙን በመግለጫው ላይ አስታውቋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት እንደገለፁት፤ የማተሚያ ቤት፣ የመፅሐፍት መደብር፣ የሬስቶራንት፣ የከብት ማደለቢያ፣ የዎርክ ሾፕ ማዕከላትን ጨምሮ ሌሎች በዩኒቨርሲቲው የተቋቋሙ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ራሳቸውን ችለው የንግድ ፍቃድ በማውጣት  የገቢ ምንጭ እንዲሆኑ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የሚሰሩ የማማከር ስራዎችም የገቢ ምንጭ ይሆናሉ ብለዋል ፕሬዚዳንቱ፡፡
ዩኒቨርሲቲው በተደጋጋሚ ከግዢ ጋር ተያይዞ የሚቀርብበትን ስሞታ ለመቅረፍ ብቁ ባለሙያዎችን ለማፍራት ጥረት እያደረገ መሆኑን የጠቆሙት የስራ አመራሮቹ፤ ችግሮቹን ለመፍታት የዩኒቨርሲቲው የንግድ ስራ ት/ቤትና የቢዝነስ ፋኩልቲ እገዛ እያደረጉለት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው ወደ 750 አልጋዎች በድብቅ ይከራያሉ ተብሎ በአንዳንድ ሚዲያዎች የቀረበው መረጃ ከእውነት የራቀ ነው ያሉት አስተዳደሮቹ፤ በዩኒቨርሲቲው በተለይም የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ተማሪዎችን የክልል ተማሪዎች በድብቅ አስጠግተው እንደሚያኖሯቸው ይታወቃል ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ በተጠቀሰው መልኩ ዶርሞች ተከራይተው አለመገኘታቸውን አመራሮቹ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ዩኒቨርስቲው በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ በ110 አመታት ውስጥ ምንም አይነት የመሬት መንቀጥቀጥ እንዳላጋጠመ በምርምር ማረጋገጡን የጠቆሙት አመራሮቹ፤
በአሁን ወቅትም በግድቡ አካባቢ የመሬት መንቀጥቀጥን የሚከታተሉ ዘመናዊ መሣሪያዎች ተከላ ለማከናወን በሂደት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በዓለማቀፍ ደረጃ ዩኒቨርስቲው የሚሰጠው ደረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መሆኑን የጠቆሙት  ፕሬዚዳንቱ፤ በአሁን ሰአት ከ16ሺህ በላይ የድህረ ምረቃ ተማሪዎችን ጨምሮ ከ52ሺህ በላይ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ካምፓሶች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ነው ብለዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ይበልጥ የምርምርና የጥናት ማዕከል እንዲሆንም ከሁለተኛ ድግሪ በላይ ያሉ ተማሪዎች ላይ አተኩሮ እየሠራ መሆኑንም ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል፡፡

Read 6257 times