Saturday, 21 January 2012 10:17

ጉዞ ወደ ጐንደር

Written by  አንተነህ ይግዛው
Rate this item
(0 votes)


ጥር 8 ቀን 2004 ዓ.ም፡፡

መስቀል አደባባይ ልንገናኝ ቀጠሮ ይዘናል፡፡

መንገደኞች ነን፡፡ ወደ ሰሜን ልናቀና ጓዛችንን ጠቅልለን ከየቤታችን የወጣን…ከንጋቱ 12 ሰዓት ላይ ተገናኝተን ረጅም ርቀት ለመጓዝ የተቀጣጠርን 12 መንገደኛ ጋዜጠኞች፡፡

ወደ ጐንደር ነው ጉዟችን፡፡

“አደራ እንዳትቀሩ” ብላ ልካብናለች ጐንደር፡፡ ጥምቀትን አብረናትንውል ዘንድ ጠርታናለች፡፡ “2ኛውን ኢትዮጵያን በጐንደር ብሔራዊ ትዕይንት ደግሼ እየጠበቅኳችሁ ነው” ብላናለች፡፡ ጥሪዋን አክብረን ልንሄድ ነው የተገናኘነው፡፡ ሄደን ልናያት አይተን ልናጣጥማት በየቴሌቪዥናችን፣ በየጋዜጣችን፣ በየሬዲዮዋችን የበአሏን ድምቀት መልሰን ልናንፀባርቅላት መስቀልአደባባይ ተገናኝተናል፡፡ እኔ ሄኖክ፣ እነ እማዋይሽ፣ እነ መልካሙ፣ እነ ዳንኤል፣ እነ ሳሚ፣ እነ ነብዩ… እኛ  ሩቅ ተጓዥ ጋዜጠኞች፡፡

ዙዎቻችን በአንድ ሙያ ላይ የተሰማራን እንደመሆናችን እርስበርስ የምንተዋወቅ ነንና ለመግባቢያ ብለን የምናባክነው ጊዜ የለንም፡፡ እንደተገናኘን ነው ሳቅ ጨዋታው የተጀመረው፡፡ የሪፖርተር ጋዜጣው ሄኖክ ያሬድ በዚያ እርስበርስ በምንግባባበት፣ ወደ ደቡብ ስንዘልቅ፣ ወደ ድሬዳዋ ስንሻገር ከዚህ በፊት አብረን ስንጓዝ በለመድነው ሰላምታ ነው የተቀበለን፡፡

“አባ መስቀላዬ!” እያለ…

ከባለስልጣኖቻችን በአንዱ ስም የሚጠራ ነጭ “ሚኒባስ” ተዘጋጅቶልናል፡፡ ይህ ዘመናዊ “ሚኒባስ” በባለስልጣኑ ስም የተሰየመበትን ምክንያት ለማሰላሰልና “ይሄ ነው” ለማለት በቂ ጊዜ ወስዶ ጥናት ማድረግ ይጠይቃል፡፡

እኔ ደግሞ ለጥናት የሚሆን በቂ ጊዜ የለኝም፡፡ ቸኩያለሁ፡፡ ሚኒባሱ ጉዞ የሚጀምርበትን ጊዜ በጉጉት እየተጠባበቅኩ ነው፡፡ ስለ “ሚኒባሱ” ስም ከማጥናት ይልቅ ከጐኑ በተደረደሩ አውቶብሶች መቅናት ጀምሬያለሁ፡፡

ዘመናዊ አውቶብሶች መንገደኞችን ይዘው በየአቅጣጫው ጉዞ እየጀመሩ ነው፡፡ ወደ ባህርዳር፣ ወደ መቀሌ፣ ወደ ሐረር፣ ወደ ጐንደር…

በአውቶቡሶቹም በተሳፋሪዎቹም ቀናሁ፤ ቶሎ ጉዞ ጀምረው ቶሎ ያሰቡበት ይደርሳሉ፡፡ ከእነዚህ አውቶቡሶች አንዱ ወደ ጐንደር ነው የሚሄደው፡፡ እኛ ወደምንሄድበት አቅጣጫ ነው የሚያቀናው… ከእኛ ቀድሞ ሲነሳ ሳየው ከእኛ ቀድሞ እንደሚደርስ እያሰብኩ ነው በዚህ አውቶቡስ የምቀናው፡፡

የጐንደሩ አውቶቡስ ሄደ…

12 ሰዓት ከ45 ደቂቃ፡፡

ከፊታችን የሚጠብቀንን 750 ኪ.ሜ ያህል መንገድ በሳቅ ጨዋታ ታጅበን ጀመርነው፡፡

ከጨዋታ አዋቂዎች ጋር ነኝ፡፡ ቀልደው ከሚያስቁ ባለለዛዎች ጋር ነው ጉዞዬ፡፡

ከመስቀል አደባባይ ተነስተን፣ በብሔራዊ በኩል ሽቅብ ወደ ፒያሳ እያመራን ነው፡፡ የቸርችል ጐዳናን ዳገት ልንጨርስ ጥቂት ሲቀረን ግን ከመካከላችን አንደኛው ተጓዥ ወደ ውጭ እየጠቆመ በግርምት ማውራት ጀመረ፡፡

“ገና ሳይጀመር!” አለ በጣቱ ወደ ውጭ እየጠቆመ፡፡ ጣቱን ተከትለን ወደ ውጭ ተመለከትን፡፡ ወደ ሰሜን ሊጓዝ ከመስቀል አደባባይ ቀድሞን የተነሳ ዘመናዊ አውቶቡስ ከመንገድ አካፋይ የብረት አጥር ጋር ተጋጭቶ ቆሟል፡፡ “ቀድመውኝ ሊደርሱ ነው” ብዬ የቀናሁባቸው ተሳፋሪዎች ከአውቶብሱ ወርደው ተመለከትኳቸው፡፡

“አቦ ይሄ እኮ ነው ነጃሳ” የሚባለው፡፡ እኔ ጉዞ ልጀምር ስል እንደዚህ አይነት ነገር ሲገጥመኝ ይደብረኛል፡፡ “ምልኪ ሲባል ሰምታችሁ አታውቁም?” ወዳጃችን ስለ “ምልኪ” መተንተኑን፣ መኪናችን በደጐል አደባባይ ዞራ ወደ ጊዮርጊስ መክነፏን ቀጥለዋል፡፡

የእንጦጦን ዳገት ተያይዘዋል፡፡ ግራና ቀኙን ወደ እንጦጦ የሚሮጡ ስፖርተኞች ይታዩናል፡፡ ከእነዚህም መካከል አንዱ፣ ነገ ከነገ ወዲያ ራሱንም አገሩንም የሚያስጠራ…  አትሌት ሊሆን ይችላል …

ዛሬ ግን ለእኛ ለመንገደኞች ተጨማሪ ሳቅ የሚያመጣ ተተኪ የቀልድ መነሻ ሆኖናል፡፡ …

በመስኮት ያየውን ጀማሪ አትሌት መነሻ በማድረግ ገጠመኙን ጀመረ - ከመካከላችን አንዱ፡፡ አንድ ማለዳ ነው፡፡ ይሄው ወዳጃችን የሚሰራው ከእንጦጦ አቅራቢያ አካባቢ ነበርና ወደ ቢሮው ሲያመራ አንድ ከሳ ያለ አትሌት ሩጫውን ገታ አድርጐ ይጠጋዋል፡፡

“ምን ልርዳህ?” አለ ወዳጃችን፡፡

“ይ …ይቅርታ … ካላስቸገርኩህ … በዚህ የሞባይል ቁጥር ሚስኮል ታደርግልኛለህ?” በትህትና ጠየቀ ሯጬ፡፡ በሚሊዮን ዶላር የሚያገኝ ታዋቂ አትሌት ሊሆን የሚችል ሰው፣ እንዴት የ”ሚስኮል ያጣል?” ብሎ አዘነ፡፡ ሊረዳውም ሞባይሉን አወጣ፡፡ አውጥቶ ግን የተጠየቀውን አላደረገም፡፡ አሰበ እንጂ፡፡ ሯጩን እያየ ጥቂት አሰበ፡፡ አሰበና ሞባይሉን መልሶ ወደ ኪሱ ከተተና አትሌቱን በቆመበት ትቶት ጉዞውን ቀጠለ፡፡

“ጥሩ አልሰራህም” አለ ከመካከላችን አንዱ፡፡

“ምን ነካችሁ! … ሚስኮል አድርግልኝ ብሎ ሞባይሌን ይዞ ቢሮጥስ! … በምን አቅሜ ልደርስበት ነው! … ሯጭ እኮ ነው!” የሚል ነበር መልሱ፡፡

በሯጩ ልጅ ቀልድ ያልሳቀው ሯጩ ሚኒባስ ብቻ ነው፡፡ ሯጩ ሚኒባስ … ዳገት ቁልቁለት የማይገደው፣ ድካም የማያዝለው፣ እስኪ ልረፍ የማይለው፣ ሽምጥ የሚጋልበው፣ ቢሮጥ የማያልበው …

ሚኒባሱ ይጋልባል … ሱሉልታን ወደ ኋላው ትቶ፣ ጐርፎን ተሻግሮ፣ ጫንጮን አልፎ፣ ሙከጡሪና ደብረ ፅጌን አቆራርጦ ወደ ፍቼ ይገሰግሳል፡፡ የሰላሌን ሜዳ ሽምጥ የሚጋልበው ሰጋር ሚኒባስ ለካ እሱም ማቆሚያ አለውና ፍቼ ላይ ሲደርስ የብረት ልጓሙ ገታው፡፡

ፍቼ ላይ ቁርስ ቀማምሰን ቀጣዩን ጉዞ ተያይዘነዋል፡፡ ወደ ደገም … ወደ ገርበ ጉራቻ … ወደ ጐሃ ፅዮን፡፡ እዚህ ይሳቃል፣ እዚያ ይቀለዳል፣ ከፊት ቁምነገር … ከኋላ ጨዋታ ደርቷል፡፡

ከረፋዱ 4 ሰዓት ከ20 ደቂቃ፡፡

አሁን የቅድሙ ሳቅ የለም፡፡ ይህ የፍርሃትና የስጋት ክፍለ ጊዜ መጀመሪያ ነው፡፡ አባይ በረሃው አፉን ከፍቶ ከፊታችን ተሰርጉዷል፡፡ ክንፍ አውጥቶ መብረር ሰላሌ ሜዳ ላይ ነው፡፡ ለጥ ያለ ሜዳ አብቅቷል፡፡ ጉዞው የገደል ነው፡፡ ጉዞው በሽምጥ ሳይሆን በምጥ መሆን አለበት፡፡

ሰላሌ ሜዳውን እንጂ አባይ ሸለቆውን ሽምጥ አይጋልቡትም፡፡ እየተጠማዘዘ፣ ጋራ እየታከከ፣ እየጠበበ፣ እየኮረበ ቁልቁል ወደ በረሃው ስምጥ የሚዘልቀውን መንገድ ቀስ ብሎ ነው መውረድ … በመላ …

ለመዘናጊያ የሚሆን ጊዜም ቦታም የለም፡፡ ለአፍታ መዘናጋት አጉል ነገር ያመጣል፡፡ ከሚኒባሱ ጐማዎች በጥቂት ሴንቲ ሜትሮች ርቀት ሞት አፉን ከፍቶ አድፍጧል፡፡ ሞትና ህይወት በሴንቲ ሜትሮች ርቀት ቀጭን ጠመዝማዛ ድንበር አስምረው ቁልቁል ወደ አባይ የሚወርዱበት የጭንቅ ሸለቆ ውስጥ ነው የምንገኘው፡፡

እዚህ መስጋት ይጀመራል፡፡ ቅድም የነበረው ሳቅ ይፈዝዛል፡፡ ቅድም ያልታሰበው ይታሰባል፡፡ “ሚኒባስ… ሾፌር በሚባል ጋላቢ የሚመራ ሰው ሰራሽ ፈረስ ነው” እያሉ ማሰብ ይጀመራል፡፡ ሾፌሩ የሚኒባሱን መሪ ብቻ ሳይሆን የተሳፋሪዎቹን ዕጣ ይዞ የሚጓዝ ወሳኝ ሰው ስለመሆኑ ይታሰባል፡፡

“አይዞን!” ይላል አንዱ ተሳፋሪ ቅድም የዘነጋውን ሾፌር ለማበረታታት፡፡

አባይ በረሃ ውስጥ ነን ….

በግራም በቀኝም ስጋት የሞላበት ጠመዝማዛ የቁልቁለት መንገድ ላይ ነን፡፡ በዚህ ጥቁር ቋጥኝ አይኑን አፍጥጦ “ልመጣ ነው” ይላል፡፡ ከእሱ ለመሸሽ አይንን ሰበር ቢያደርጉ ደሞ በዚያ “ጭልጥ ያለ” ገደል “ልውጥህ ነው” እያለ አፉን እያዛጋ ይጠብቅዎታል፡፡

ቁልቁለቱን በምጥ ወርደው የሸለቆው ወለል ላይ ሲደርሱ የአባይን ወንዝ ተሻግረው ሌላ ፈተና ይጀምራሉ፡፡ የአቀበት፡፡

እኛ ቁልቁለቱን እያገባደድን ነው፡፡ ድልድዩ ላይ ልንደርስ 500 ሜትሮች ያህል ይቀሩናል፡፡ ከግርጌያችን አባይ ብቅ አለ፡ አንዳንዶቹ የአባይን ወንዝ ፎቶ ሊያነሱ ካሜራዎቻቸውን አወጡ፡፡ ወደ ወንዙ አቅጣጫ በወደሯቸው ካሜራዎቻቸው ሌንስ ውስጥ ግን “የደበዘዘ አባይ” ነበር የተመለከቱት፡፡ ጭስ ያጠየመው አባይ፡፡

በረሃው ውስጥ ደማቅ ጭስ ሽቅብ ይትጐለጐላል፡፡ ጭሱ የወትሮውን የአባይ በረሃ ከሰል አክሳዮች የሳሳ የጉልጥምት ጭስ አይመስልም፡፡ ከጠባቧ ኩርባ በታች ካለው ገደል ውስጥ እየተጥመለመለ የሚወጣው ጭስ የከሰል አይመስልም፡፡ የከሰል ጭስ እንዲህ ያለ ሽታ የለውም፡፡ የአክሳዩን አይን ቆጥቁጦ ትንሽ እንባ ቢያስነባ እንጂ ይሄን አገር ሙሉ ሰው ዶፍ እንባ አያስለቅስም፡፡ አባይን ሊሻገር ጥቂት የቀረውም፣ አባይን ተሻግሮ ጥቂት የተጓዘውም … ሂያጁም፣ መጪውም … ከመኪናው ወርዶ እዚህ ገደል አፋፍ ላይ ተሰልፎ ቁልቁል እያየ የሚያለቅሰው በከሰል ጭስ አይደለም፡፡ ሚኒባሱ ውስጥ የነበርን በሙሉ በጥያቄ አይን ወደ ህዝቡ ተመለከትን፡፡ “ፎቶ ሊነሱ ይሆናል” አለ አንደኛው ከመካከላችን፡፡ ህዝቡ ከየመኪናው ወርዶ ከገደሉ አፋፍ የቆመበትን ምክንያት እየገመተ ነበር፡፡

እሱ ጥሩ ገማች አልነበረም፡፡ የእሱም .. የሌሎቻችንም ግምት ትክክለኛ አልነበረም፡፡ ሁላችንም ያልገመትነው ነገር ነው ገደሉ ስርም ከገደሉ አፋፍም የሆነውና እየሆነ ያለው፡፡

ጭሱ ከሚቃጠል እንጨት የሚወጣ አልነበረም፡፡ በእሳት የሚለበለበው፣ ተንጨርጭሮ የሚቃጠለው፣ በረሃው ውስጥ የሚጨሰው እንጨት ሳይሆን አጥንት ነው፡፡

የበረሃው ንፋስ “እፍ” እያለ የሚያቀጣጥለው ፍም የሰው ስጋ ነው፡፡ አዎ፡፡

የገመትነው አይደለም የሆነውና እየሆነ ያለው፡፡ እኛም … ከገደሉ አፋፍ ቆሞ እሪታውን የሚያቀልጠው ህዝብም፤ ከገደሉ ስር ከፍም ተማግዶ በእሳት የሚጋየው ባለ መጥፎ ዕጣ መንገደኛም … ሁላችንም ይህ ይሆናል ብለን አልገመትንም፡፡

ከአዲስ አበባ ተነስቶ 47 ሰዎችን ጭኖ ወደ ጐንደር ጉዞ የጀመረው አውቶቡስ መንገዱን ስቶ ገደል ገብቷል፡፡ ከገደሉ አፋፍ በግምት 80 ሜትር ያህል ወርዶ ከአንዲት የበረሃ ዛፍ ስር ሰፊ ምድጃ ሰርቶ በእሳት ይጋያል፡፡

40 ሰው፣ መውጫ በሌለው እሳት ተማግዶ ይለበለባል፡፡ እጅግ አሰቃቂ ትዕይንት፡፡ ፍፁም ዘግናኝ ነገር፡፡ ከአውቶቡስ ሙሉ ሰው አምስት ያህሉ ብቻ በአሰቃቂ ሁኔታ ቆስለው በህዝቡ ርዳታ ከገደሉ ወጥተዋል፡፡ ወደ ጐሃ ፅዮን ሆስፒታል ተወስደዋል፡፡

ከሚኒባሳችን ወርደን ይህን ዘግናኝ ትዕይንት ቁልቁል እየተመለከትን ዋይታውን ተቀላቀልነው፡፡ አውቶብሱ የብረት አፅሙ እስኪገጥ ተቃጥሏል፡፡ ውስጡ የነበሩ 40 ያህል መንገደኞች ወደ ፍምነት ተለውጠው ፀጥ ብለዋል፡፡

ከእነዚህ እሳት ከበላቸው መንገደኞች መካከል ጭላጭ ትንፋሽ ያለው አንድ ሰው ብቻ ነው፡፡ …ከእግር እስከ ራሱ በእሳት ተለብልቦ ከገደሉ ስር ወጥቶ በቃሬዛ ላይ ሆኖ የሚያቃትተው፡፡ የፖሊስ አባላትና ህዝቡ ተረባርቦ ከምድጃው ያወጣው ይህ ሰው ቃሬዛው ላይ ተዘርሮ ኡኡ ይላል፡፡

“ውሃ … ውሃ … ውሃ ስጡኝ” ይላል፡፡

ህዝቡ በእንባ ይራጫል፡፡ “ከ …ከአውስትራሊያ ነው የመጣሁት … ለጥምቀት ወደ ጐንደር እየሄድኩ ነው …” እየቃተተ ይናገራል፡፡ ህዝቡ ወዬታውን ያስነካዋል፡፡

“በዚህ ስልክ ቁጥር ደውሉና ለጴጥሮስ ንገሩልኝ” አሁንም ይቃትታል፡፡ ህዝቡ የዚህን ሰው ጥያቄ መልስ ከመስጠቱ በፊት … ስልኩ ከመደወሉ በፊት … ሰውዬው ራሱ መልዕክቱን ሩቅ ወዳለው ወንድሙ “ይድረስ” ብሎ ተነፈሰ፡፡

“ቻው ጴጥሮስ! … በቃ … አልተገናኘንም!”

ይህ የሰውዬው የመጨረሻ ቃል ነው፡፡ በዚህች ቅፅበት ፍም የነበረ አካላቱ ወደ በረዶነት ተቀየረ፡፡

 

 

 

 

 

Read 16563 times Last modified on Saturday, 21 January 2012 12:32