Saturday, 21 March 2015 11:12

ኖክ በ100 ቢሊዮን ብር የነዳጅ ማጣሪያ ሊገነባ ነው

Written by 
Rate this item
(10 votes)

   ናሽናል ኦይል ኢትዮጵያ (ኖክ) በ100 ቢሊዮን ብር ወጪ በአስር አመት ጊዜ ውስጥ ተሰርቶ የሚጠናቀቅ የነዳጅ ማጣሪያ የመገንባት ዕቅድ እንዳለው ማስታወቁን ሮይተርስ ከኬፕ ታውን ዘገበ፡፡
የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ጥላሁን ለሮይተርስ እንደገለጹት፣ ኩባንያው በኢትዮጵያ ያለው የነዳጅ ፍላጎት እያደገ መምጣቱን በመገንዘብ በቀን ከ200 ሺህ እስከ 300 ሺህ በርሜል ነዳጅ የማምረት አቅም ይኖረዋል ተብሎ የሚጠበቀውን የነዳጅ ማጣሪያ የመገንባት ዕቅድ ይዟል፡፡
በአገሪቱ ያለው የነዳጅ ፍላጎት በየአመቱ በአስር በመቶ እያደገ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ታደሰ፣ በአሁኑ ወቅት ያለው የአገሪቱ የነዳጅ ፍላጎት በመጪዎቹ አስር አመታት በእጥፍ ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅና፣ ኩባንያው የነዳጅ ማጣሪያውን በአስር አመት ውስጥ ገንብቶ እንደሚያጠናቅቅ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡
በደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን ለአምስት ቀናት በተካሄደውና ትናንት በተጠናቀቀው የአፍሪካ የነዳጅ አጣሪ ኩባንያዎች ማህበር ስብሰባ ላይ የተገኙት ዋና ስራ አስፈጻሚው፣ የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ ግንባታውን የፋይናንስ ምንጭ በተመለከተ ያሉት ነገር ባይኖርም፣ ሌሎች ኢንቨስተሮች የፕሮጀክቱ አካል የሚሆኑበት ዕድል እንዳለ ከዚህ ቀደም መናገራቸውን ዘገባው አስታውሷል፡፡

Read 3257 times