Saturday, 21 March 2015 10:49

ያልተጠበቀው ሲሳይ

Written by  አልአዛር ኬ.
Rate this item
(3 votes)

    ባለፈው ረቡዕ ረፋዱ ላይ የእስራኤል የምርጫ ቦርድ የምርጫውን ውጤት ይፋ አደረገ፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የሚመራው የሊኩድ ፓርቲ 30 መቀመጫዎች አግኝቶ ማሸነፉና በይስሀቅ ሔርዞግ የሚመራው የጽዮናውያን ህብረት ፓርቲ ደግሞ 24 መቀመጫዎች በማግኘት ሁለተኛ መውጣቱ ተረጋገጠ፡፡
የፓርቲያቸውን የምርጫ ውጤት ለማወቅ ገና በጠዋቱ በፓርቲያቸው ጽ/ቤት ደጅ ላይ የተሰባሰቡት የሊኩድ ፓርቲ ደጋፊዎች የሰሙትን ማመን አልቻሉም፡፡ በእየሩሳሌም ምስራቅ የወረዳ ሶስት የሊኩድ ፓርቲ የቅስቀሳ አስተባባሪ የነበረው የ24 ዓመቱ ዳን ሞርዶካይ በሰሙት የምርጫ ውጤት ተገርመው አፋቸውን ይዘው የቆሙትን ጓደኞቹን በከፍተኛ የደስታ ስሜት እያቀፈ፤ “ይህ የማይታመን ነገር ነው! ይህ ከአምላክ የወረደልን ያልተጠበቀ ሲሳይ ነው!” በማለት ጮክ ብሎ ተናገረ፡
እንደ እውነቱ ከሆነ የሊኩድ ፓርቲ ደጋፊዎች የፓርቲያቸውን የምርጫ ውጤት ማመን ቢያቅታቸውም ሆነ ዳን ሞርዶካይ ውጤቱ ያልጠበቁት ሲሳይ መሆኑን በመግለፅ በደስታ አቅሉን ስቶ ጮቤ ቢረግጥ ፈጽሞ አይፈረድባቸውም፡፡
ምርጫው ተጀምሮ እስከተጠናቀቀበት ያለፈው ማክሰኞ ድረስ በተለያዩ ጋዜጦች ታትመው የወጡ የህዝብ አስተያየት መመዘኛዎች በቤንያሚን ኔታንያሁ የሚመራው ወግ አጥባቂው የሊኩድ ፓርቲ በምርጫው አብላጫ ድምጽ ማግኘት እንደማይችልና ይስሀቅ ሄርዞግ በሚመሩት የፂዮናውያን ህብረት ፓርቲ እንደሚረታ የተነበዩ ብዙዎች ነበሩ፡፡ በዚህ የተነሳም የአብዛኞቹ የሊኩድ ፓርቲ ደጋፊዎች የእናሸንፋለን ስሜታቸው በእጅጉ የተቀዛቀዘ ነበረ፡፡
የምርጫው ውጤት ግን የቅድሚያ ግምቶችን ሁሉ ከመሰረታቸው ፉርሽ በማድረግ፣ ያ ሁሉ የእስራኤል ጋዜጣ በየእለቱ ያራገበው የህዝብ አስተያየት መመዘኛ ስህተት መሆኑን በድጋሚ ማረጋገጥ ቻለ፡፡
በዚህ የእስራኤል ምርጫ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎችና እውቅ ፖለቲከኞች ተካፍለውበታል፡፡ ከቤንያሚን ኔታንያሁ፣ ይስሀቅ ሄርዞግ፣ ዚፒ ሊቭኒና ከሞሸ ካህሎን ልቆ በምርጫው መድረክ ላይ በዋናነት የተወነ የፖለቲካ መሪ ግን አንድም አልነበረም፡፡
ከምርጫው በፊትም ሆነ በምርጫው ወቅት አብዛኛው የእስራኤል ህዝብ ከፍልስጤማውያን ጋር በሰላምና በትብብር መኖር እንደሚፈልቅ በግልጽ ይነገርለት ነበር፡፡ እናም ይህንን አቋም ለሚያራምደውና በይስሀቅ ሄርዞግና በዋነኛ ተባባሪያቸው ዚፒ ሊቭኒ ለሚመራው የፂዎናውያን ህብረት ፓርቲ የድጋፍ ድምፃቸውን በመስጠት ለአሸናፊነት ያበቁታል ተብሎ በእርግጠኛነት ተገምቶ ነበር፡፡
የማታ ማታ በአሸናፊነት የወጡት ግን ከፂዎናውያን ህብረት ፓርቲ በተቃራኒው በፍልስጤማውያንና በኢራን ላይ ብዙዎች “ጽንፈኛ” በሚል የፈረጁትን አክራሪ አቋም የሚያራምዱት የሊኩዱ መሪ ቤንያሚን ኔታንያሁ ናቸው፡፡
አንድ መቶ ሀያ መቀመጫ ካለው የእስራኤል ክኔሴት (ፓርላማ) ሰላሳውን ያገኘው የሊኩድ ፓርቲ፤ የሱ ቢጤ ከሆኑ የቀኝ ክንፉ ወግ አጥባቂ ፓርቲዎች ጋር በመሆን የጥምር መንግስት የመመስረት እድሉን በእጅጉ ማስገባት ችሏል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ቤንያሚን ኔታንያሁ ለአራተኛ ጊዜ እስራኤልን በጠቅላይ ሚኒስትርነት እንዲመሩ ያስችላቸዋል፡፡ በዚህም የእስራኤል የፖለቲካ የታሪክ መዝገብ፣ ቤንያሚን ኔታንያሁን እስራኤልን ለረጅም ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትርነት የመሩ ብቸኛው ሰው ብሎ በክብር ይመዘግባቸዋል፡፡
ከ15 ዓመታት ወዲህ የመጀመሪያው ነው በተባለለትና ለምርጫው ከተመዘገበው ህዝብ 71.8 በመቶ ያህሉ ድምጽ በሠጠበት በዚህ የእስራኤል ምርጫ ያልተጠበቁ ሌሎች ውጤቶችም ተከስተዋል፡፡ በምርጫው ከተወዳደሩት በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የፓርላማ መቀመጫ ማግኘት የቻሉት አስር ብቻ ናቸው፡፡ ይህም ከ23 ዓመት ወዲህ ዝቅተኛ ቁጥር ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ፓርላማ የገቡበት ምርጫ እንዲሆን አድርጎታል፡
ይህም ብቻ አይደለም፡፡ በእስራኤል የምርጫ ታሪክ 28 ሴቶችና 17 አረብ እስራኤላውያን በየፓርቲያቸው አማካኝነት የፓርላማ መቀመጫ ማሸነፍ የቻሉት በዚህኛው ምርጫ ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ በዚህ ምርጫ ያልታሰበ ሲሳይ እንደወረደላቸው በግልጽ የተረዱት እንደ ዳን ሞርዶካይ አይነቶቹ የሊኩድ ፓርቲ ደጋፊዎች ብቻ አይደሉም፡፡ ቤንያሚን ናታንያሁም የድሉን ብስራት ለመጋራት ለተሰበሰቡ በሺ የሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው ረቡዕ እለት ባደረጉት ንግግር እማኝነታቸውን በግልጽ አነጋገር ፊት ለፊት ገልፀዋል፡፡
ይህ ሁሉ ነገር ከእንግዲህ ታሪክ ነው፡፡ አሁን የእስራኤላውያንንም ሆነ የእስራኤልን ጉዳይ ነገሬ ብለው በጥሞና ለሚከታተሉተ ሁሉ ዋናውና የላቀው ጉዳይ ከዚህ በሁዋላ የሚመጣው ነገር ነው፡፡
የቤንያሚን ኔታንያሁ ለአራተኛ ጊዜ በጠቅላይ ሚኒስትርነት መመረጥ እስራኤልን ከተቀረው ዓለም ጋር ፍጥጫ እንድትገጥም በሚያደርጋት አውራ ጎዳና መሀል ላይ አስቀምጧታል፡፡ ቤንያሚን ኔታንያሁ የጥምር መንግስት የሚያቋቁሙት እንደ ሊኩድ ፓርቲ ሁሉ የፍልስጤምን ነፃ መንግስት መቋቋም ከሚቃወሙ የቀኝ ክንፉ ወግ አጥባቂ ፓርቲዎች ጋር ብቻ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለራሷ ለእስራኤልም ሆነ ለመካከለኛው ምስራቅ አካባቢ ሰላም መጠበቅ ምንም አይነት ፋይዳ የሌለው ይልቁንም የባሰ አደጋና አለመረጋጋት የሚጋብዝ ግብአት ነው፡፡
እንዲህ ያለው ሁኔታ እንዲፈጠር ደግሞ የአብዛኛው የዓለም ህብረተሰብ በተለይ ደግሞ እንደ አሜሪካ ያሉ ሀያል ሀገራት ፍላጎትም ሆነ ምኞት አይደለም፡፡ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት የአይሲስ እስላማዊ ጀሀድ ቡድን በፈጠረባቸው መጠነ ሰፊና አስጨናቂ ስጋት እየተናጡ ባለበትና የምዕራቡ አለምም ይህንን እኩያ የለሽ ጽንፈኛ እስላማዊ መንግስት ለመቋቋም ወዲያ ወዲህ በሚልበት በአሁኑ ወቅት፣ እስራኤል ይህን የመሰለ ግትር አቋም ይዛ ለመቀጠል መፈለጓ በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ መገለልን እንዳያተርፍላት ብዙዎች ገና ከአሁኑ ሰግተዋል፡፡

Read 2444 times