Print this page
Saturday, 21 March 2015 10:44

“ዊንዶውስ 10” በመጪዎቹ 4 ወራት አገልግሎት ላይ ይውላል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ለ20 አመታት ያገለገለው ኢንተርኔት ኤክስፕሎረር በፕሮጀክት ስፓርታን ይተካል
ታዋቂው ማይክሮሶፍት ኩባንያ እጅግ የተራቀቀ የተባለለትን አዲሱ ዊንዶውስ 10 ኦፐሬቲንግ ሲስተም በመጪዎቹ አራት ወራት ጊዜ ውስጥ በይፋ በማስተዋወቅ በስራ ላይ እንደሚያውል ገለጸ፡፡
በአለም ዙሪያ ከ1.5 ቢሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች እንዳሉት የሚነገርለትንና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ  አዳዲስ አሰራሮችን በመላበስ በመቅረብ ላይ የሚገኘውን ዊንዶውስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም የሚያመርተው ማይክሮሶፍት ምክትል ፕሬዚዳንት ቴሪ ሜርሰንን ጠቅሶ ቴሌግራፍ እንደዘገበው፣ ኩባንያው አዲሱን ኦፐሬቲንግ ሲስተም እስከ ግንቦት ወር መጀመሪያ በስራ ላይ ለማዋል አቅዷል፡፡
አዲሱ ኦፐሬቲንግ ሲስተም በ111 የተለያዩ ቋንቋዎች እንደሚዘጋጅና በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ 190 አገራት የኩባንያው ደንበኞች እንደሚዳረስ የጠቆመው ዘገባው፣ ኦፐሬቲንግ ሲስተሙ ነባሮቹን ዊንዶውስ 7፣ 8.1 እና ዊንዶውስ ፎን 8.1 ለሚጠቀሙ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደንበኞች ለአንድ አመት ያህል በነጻ እንደሚሰጥም አስታውቋል፡፡
ዊንዶውስ 10 በዴስክቶፕ እና ላፕቶፕ ኮምፒውተሮች ላይ እንዲሁም የማይክሮሶፍት ኩባንያ ምርቶች በሆኑ ታብሌቶችና የሞባይል ስልኮች ላይ እንደሚሰራ ያስታወቀው ኩባንያው፣ ለ20 አመታት ያህል አገልግሎት ሲሰጥ የቆየውን ነባሩን ሰርች ኢንጂን ኢንተርኔት ኤክስፕሎረርን፣ ፕሮጀክት ስፓርታን በተሰኘ አዲስ ፈጠራው መተካቱንም ጠቁሟል፡፡
ኢንተርኔት ኤክስፕሎረር ምንም እንኳን በመላው አለም የሚገኙ ከ1 ቢሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች ያሉት ታዋቂ ሰርች ኢንጂን ቢሆንም፣ ተሻሽለው ከተሰሩትና ከፈጣኖቹ ፋየርፎክስ እና ጎግል ክሮም ጋር መወዳደር ባለመቻሉ፣ ኩባንያው ፕሮጀክት ስፓርታን የተሰኘውን አዲሱን ሰርች ኢንጂን ለመስራት መወሰኑንም ዘገባው ጨምሮ አመልክቷል፡፡

Read 2046 times
Administrator

Latest from Administrator