Saturday, 21 March 2015 10:24

ሀኮማል በመጪው ወር የገነባቸውን ቤቶች ያስረክባል

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(7 votes)

ባለአክሲዮኖች ሲመዘግብ ከ24 – 3 ወራት ቤት ሰርቼ አስረክባለሁ በማለት ነበር፡፡ ነገር ግን ከአቅም በላይ በሆኑ ተጨባጭ ችግሮች ቃሉን ማክበር እንዳልቻለ ይገልጻል - ሀበሻ ኮንስትራክሽንና ማቴሪያል ልማት (ሀኮማል)፡፡ ስለዚህ ጉዳይ በተለያዩ ጊዜያት ባለአክሲዮኖቼን ጠርቼ ችግሮቹን በማስረዳት ተወያይተናል ብሏል፡፡
ያለፈው ሁለት ዓመት ለቤት ገዢዎችና አልሚዎች ጥሩ ጊዜ አልነበረም፡፡ ቤቶችን በገቡት ቃል ጨርሶ ያለማስረከብና የአንዳንድ አልሚዎች ከአገር መውጣት፣ ህብረተሰቡን በከፍተኛ ስጋት ሲያምሰው ቆይቷል፡፡ አሁን ግን ያ ሁሉ ጭንቀትና ስጋት አልፎ ሀኮማል በመራ ሎቄ ሳይት እያስገነባ ካለው 10 ብሎኮች አራቱን በቅርቡ ለባለቤቶች ለማስረከብ መዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡ “መሪ ሎቄ እየሰራን ካሉት 10 ጂ + 4 ብሎኮች አራቱ እየተጠናቀቁ ስለሆነ በመጪው ሚያዚያ ወር እናስረክባለን” ብለዋል፤ የሀኮማል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጌትነት ኃይሉ፡፡
አቶ ጌትነት በተለያዩ ሳይቶች በመሪ ሎቄ፣ ሲኤምሲ፣ መስቀል አደባባይ፣ ባምቢስ፣ የቀድሞው ግብርና ሚ/ር ፊት ለፊት፣ ሃያ ሁለት፣ አያት፣ ኢሲኤ፣… አካባቢዎች ፕሮጀክቶች እንዳሏቸው ጠቅሰው ፕሮጀክቶቹም በጅምር፣ በመሬት ስራ፣ መዋቅራቸው (ስትራክቸር) ያለቀ፣ ጣራ የለበሱና በመጠናቀቅ ደረጃ ላይ የሚገኙ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በስድስት መስራቾችና በ200ሺህ ብር ካፒታል በ2003 ዓ.ም የተቋቋመው ሀኮማል፤ ካፒታሉን ለማሳደግ አክሲዮን በመሸጡ በአሁኑ ወቅት ከ2000 በላይ ባለአክሲዮኖችና 60 ሚሊዮን ብር ካፒታል መሰብሰቡን፣ ገልጿል፡፡ በሁሉም የንግድ ዘርፎች ለመሰማራት የተቋቋመ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት በሪል እስቴት ዘርፍ ተሰማርቶ እንደሚገኝ  አቶ ጌትነት ተናግረዋል፡፡
ሀኮማል እንደተቋቋመ ያጋጠመው ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ምን እንደሆነ አቶ ጌትነት ሲያስረዱ፣ “መንግስት ለቤት አልሚዎች መሬት በድርድር ወይም በነፃ ይሰጥ ነበር፡፡ የእኛ ድርጅት እንደተቋቋመ መሬት በሊዝ ጨረታ ብቻ እንደሚሸጥ፣ ከዚያ ውጭ ለትላልቅ የመንግስት ፕሮጀክቶች ወይም አገራዊ ጠቀሜታ ላላቸው ብቻ መሬት በድርድር ወይም በነፃ እንደሚሰጥ በማስታወቁ መሬት በድርድር፣ በነፃ ወይም በሊዝ ማግኘት አልቻልንም ብለዋል፡፡
እንዴት በሊዝ መግዛት እንዳልቻሉ ሲገልፁ፣ በሊዝ ጨረታ የሚወጡ ቦታዎች ተሸንሽነው ስለሆነ ለሀኮማል አመቺ አይደለም፡፡ ትልቁ የሊዝ ቦታ 1,000 ካሬ ሜትር ነው፡፡ ሀኮማል ትልቅ ድርጅት  በመሆኑ  ሰፊ ቦታ ይፈልጋል፡ የቢዝነስ ድርጅት ስለሆነም እነዚያን በተለያዩ አካባቢዎች የሚሸጡ ቦታዎች ገዝቶ ትርፋማ መሆን አይቻልም፡፡ ለዚህ ነው በሊዝም መግዛት አልቻልንም ያልኩት፡፡ እኛ በአራት ቦታ በጨረታ ያገኘነው መሬት 1000 ካሬ ያህል ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ በሊዝ ጨረታ የሚገዛ ቦታ ዋጋ እጅግ የጦዘበትና መንግስትም ምክንያቱን ያላወቀበት ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ ዛሬ እንኳ አንድ ጋዜጣ ሳነብ በቦሌ ቡልቡላ ለ1 ካ.ሜ ቦታ 33ሺህ ብር ቀረበ የሚል አይቻለሁ፡፡ በእንዲህ ዓይነት ዋጋ ገዝቶ እንዴት ማትረፍ ይቻላል? በማለት አብራርተዋል፡፡
ድርጅቱ መሬት በድርድር፣ በጨረታ ወይም በሊዝ መግዛት ካልቻለ እንዴት በዘጠኝ ሳይቶች ግንባታ ጀመረ? ችግር ብልሃትን ይወልዳል አይደል የሚባለው? ሌላ መላ ዘየደ፡፡ ይኸውም መሬት በሊዝ ገዝተው ገንዘብ ያጠራቸውን ባለሀብቶች ፈልጎ አብረን እንስራ አላቸው፡ ስለዚህ  እነሱ በመሬት፣ ሀኮማል በገንዘብ በጋራ እየሰሩ ነው፡፡ ከአንዱ ፕሮጀክት በስተቀር ስምንቱ በጋራ የሚያለሟቸው እንደሆኑ ገልፀዋል፡፡
ሀኮማል ሲቋቋም ቤቶችን በባለአክሲዮኖች ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ከባንክ ብድር በመውሰድ ለመስራት አስቦ እንደሆነ የጠቀሱት ስራ አስኪያጁ፣ ባለፉት ሶስትና አራት ዓመታት ቅድሚያ ለመንግስት ትላልቅ ፕሮጀክቶች በመሰጠቱና የግል ባንኮችም እነዚህን ፕሮጀክቶች በገንዘብ እንዲደግፉ ስለተደረገ፣ እንዲሁም ለማኑፋክቸሪንግና ለኤክስፖርት ንግድ ካልሆነ በስተቀር ለሪል እስቴት ፕሮጀክቶች ገንዘብ ማበደር ስላልቻሉ ከባንክ ብድር ማግኘት አለመቻላቸውን ገልፀዋል፡ መጀመሪያ ላይ ደንበኛው 50 በመቶ ከከፈለ ቀሪውን 50 በመቶ ካርታውን በማስያዝ ከባንክ ጋር ብድር እናመቻቻለን ያሉት ባለመሳካቱ ለደንበኞቻቸው አሳውቀውና ተመካክረው ሌላ ዘዴ እንደፈጠሩ ተናግረዋል፡፡
ሌላው ችግር ከሁለት ዓመት በፊት በሪል እስቴት ዘርፍ የተፈጠረው ውዥንብር በእኛም ላይ ተፅዕኖ ፈጥሯል ብለዋል አቶ ጌትነት፡፡ ቀደም ሲል መንግስትም ሪል እስቴቶች በልማት ስም መሬት ወስደው ከማልማት ይልቅ ትንሽ ነገር አስቀምጠው መቸብቸብ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሶ ስለነበር፣ የህዝቡንም ሆነ የመንግስትን አመኔታ ማጣታቸውን፣ እነሱ ስራቸውን በትክክል እየተወጡ ቢሆንም ውዥንብሩ እስኪጣራ ድረስ ባለአክሲዮኖች ገንዘብ በወቅቱ ያለመክፈላቸው በስራቸው ላይ ተፅዕኖ ቢያሳድርም ጠንክሮ በመስራት የደንበኞቻቸውን አመኔታ እንዳገኙ ተናግረዋል፡፡    
ሀኮማል በአሁኑ ወቅት የጀመራቸው ፕሮጀክቶች የ1.5 ሚሊዮን ብር ካፒታል ሲሆን ፕሮጀክቶቹ በተለያዩ ደረጃ የሚገኙና ግንባታቸው በአማካይ ከ40 እስከ 50 በመቶ የተጠናቀቁ መሆናቸውን አቶ ጌትነት ገልጸዋል፡፡
የወደፊት እቅዳቸውንም ሲያስረዱ፣ የመካከለኛ ዕቅዳችን የጀመርናቸውን ፕሮጀክቶች አጠናቀን ለባለቤቶቻቸው ማስረከብ ነው፡፡ አሁን የተጀመሩት ትላልቅ ፕሮጀክቶች ስለሚጠናቀቁ ከባንክ ብድር እናገኛለን የሚል እምነት አለን፡፡ የእኛ ዕቅድ በሁሉም ዘርፍ መሰማራት ስለሆነ የወቅቱን ሁኔታ እያየን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡

Read 3957 times