Saturday, 21 March 2015 10:23

አካል ሳይከፈት የሚደረግ ምርመራ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(5 votes)

የመሳሪያዎቹ ጠቀሜታና የጎንዮሽ ጉዳቶች
   የሰው ልጅ የሚጠቃባቸውን የተለያዩ አይነት በሽታዎች አካሉ ሳይከፈት (ያለቀዶ ጥገና) ለማየትና ለመመርመር የሚያስችሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ላይ መዋል ከጀመሩ አመታት ተቆጥረዋል፡፡ ከእነዚህ መሣሪያዎች መካከልም ሜሪና ፔሬይኩሪ በተባሉ ተመራማሪዎች የተገኘው የኤክስሬይ (ራጅ) ምርመራ መሣሪያ ቀዳሚ ሲሆን ይህ መሣሪያ አገልግሎት ላይ ከዋለ አንደ መቶ አመታትን አስቆጥሯል፡፡ ቴክኖሎጂ ምስጋና ይግባውና እነዚህ የሰው ልጅ አካል ሳይከፈት ምርመራ ለማድረግ የሚያስችሉ መሣሪያዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየዘመኑና እየተሻሻሉ ሄደው ዛሬ ከፍተኛ መራቀቅ ላይ ደርሰዋል፡፡
እነዚህ ዘመናዊ የህክምና ምርመራ መሣሪያዎች የየራሳቸው ጠቀሜታና ጉዳቶች አላቸው። መሣሪያዎቹ የሚያደርሱት ጉዳት ከሚሰጡት ጠቀሜታ አንፃር ተመዝኖ ጥቅም ላይ ይውላሉ። የህክምና ባለሙያው ለታማሚው ምርመራውን የሚያዘው የታማሚው የጤና ሁኔታ፣ ከምርመራው ሊገኝ የሚችለውን ጠቀሜታና የታማሚውን የሚደርሱትን ችግሮች የመቋቋም አቅም ከግምት ውስጥ በማስገባትና ምርመራው የሚያስከትለውን የጤና ችግር በማመዛዘን ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት በአገራችን በስፋት ጥቅም ላይ እያዋሉ ያሉት አካልን ሳይከፍቱ ምርመራ የማድረግ ቴክኖሎጂዎች የሚያስገኙትን ጥቅሞችና ጉዳቶች በአጭር በአጭሩ ለማየት እንሞክራለን፡፡

አልትራ ሳውንድ (Sonography)
ተግባሩ የድምፅ ሞገድን በመጠቀም በኮምፒዩተር ምስልን ማንሳት ሲሆን ታካሚው የሰውነት አካል ላይ ፈሳሽ በማድረግ ባለሙያው በመሣሪያ በመታገዝ እያንቀሳቀሰ በሚፈልገው ቦታ ረዘም ያለ ጊዜ በመቆየት ምስሉ እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ ዝቅተኛ የድምጽ ሞገድን በመጠቀም የውስጥ አካላትን በዝርዝር ለማየት የሚቻል ሲሆን ከፍተኛው የድምጽ ሞገድ የቆዳ ክፍሎችን፣ ዓይንን እና የቆዳ ካንሰርን ለመለየት ያስችላል፡፡
አልትራሳውንድ ፅንስን ለመመርመር በስፋት ጥቅም ላይ የሚውል ሲሆን የደም ቧንቧ ሁኔታን፣ ልብንና የጡት ካንሰርን ለመመርመርም ያስችላል። ቴክኖሎጂው በቀላሉ የሚገኝ፣ ውድ ያልሆነና የጐንዮሽ ጉዳቱም አነስተኛ ነው፡፡ አልትራ ሳውንድ ፅንስን ለመመርመር ጥቅም ላይ የሚውል ቢሆንም የተደጋገመ ምርመራ ማድረጉ ግን በፅንሱ ህብር ህዋስ ላይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል፡፡

ራጅ (X-ray Radiography)
በአብዛኛው ለአጥንት፣ ለደረት፣ ለጥርስና ለሣምባ ጤና ችግሮች ጥቅም ላይ የሚውል ሲሆን በአጭር የሞገድ ርዝመት ሰውነታችንን በቀላሉ ጥሶ በመግባት ምስልን ለማስቀረት (ለማየት) የሚያስችል ቴክኖሎጂ ነው፡፡
የራጅ የምርመራ መሳሪያ ህመም የለሽ ሲሆን፣ አጠቃቀሙ ቀላል የሆነ ቴክኖሎጂ መሆኑ፣ ውድ አለመሆኑና በተለይመ ከምርመራ በኋላ በሰውነት ውስጥ የሚቀር ጨረር አለመኖሩ ተመራጭ ያደርገዋል፡፡
ይህ የምርመራ ዘዴ ከሚያስከትላቸው የጤና ችግሮች መካከል ወደ ሰውነታችን ውስጥ የሚዘልቀው ጨረር ኃይለኛ በመሆኑ ሣቢያ በህብረ ህዋሳቶቻችን ላይ ጉዳት ሊያስከትል መቻሉ ነው፡፡ እርጉዝ ሴቶች ይህንን የምርመራ ዘዴ መጠቀም የለባቸውም፡፡

ሲቲ ስካን (Computed Jumography) X- ray (ራጅ) መሣሪያ በዘመናዊ መልኩ ተሻሽሎ ጥቅም ላይ እንዲውል ሲደረግ የመጣ ዘመናዊ የምርመራ መሣሪያ ነው፡፡ መሣሪያው ልዩ መልዕክት ተቀባይ (Sensor) ማሽን የተገጠመለት ሲሆን ህመምተኛው በማሽኑ ውስጥ እንዲገባ ተደርጐ 360 ድግሪ በሚሽከረክሩና ብርሃን በሚፈነጥቁ መሣሪያዎች አማካይነት የታማሚውን አጠቃላይ የሰውነት ክፍል ፎቶግራፍ ለማንሣት የሚያስችል መሣሪያ ነው፡፡ መሣሪያው በአብዛኛው ለተለያዩ አይነት የካንሰር ህመሞች፣ ለደረት፣ ለአጥንት፣ ለጭንቅላትና፣ ለሆድ አካባቢ የጤና ችግሮች ምርመራ ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ ሲቲ ስካን ፈጣን፣ ቀላልና ህመም የሌለው የምርመራ መሣሪያ ከመሆኑም በላይ የውስጥ አካላትን ቁልጭ አድርገው የሚያሣዩ ምስሎችን ስለሚያስገኝ ሃኪሙ የበሽታውን ምንነት በቀላሉ ለማወቅ እንዲችልም ያስችለዋል፡፡
በሲቲስካን መሣሪያ ምርመራ ማድረግ የተለያዩ ጉዳቶችም አሉት፡፡ መሣሪያው ከx-ray ማሽንም ላቅ ያለ መጠን ያለው ጨረርን ወደሰውነታችን ውስጥ እንዲገባ ስለሚያደርግ በካንሰር የመጠቃት አደጋን ሊያስከትል ይችላል፡፡ የምስል ጥራቱን ለማሳደግ ተብለው የሚጨመሩት ኬሚካሎች በኩላሊት ላይ ጉዳትን ሊያስከትሉ የሚችሉ ሲሆን የአለርጂ ችግርም የመፍጠር አደጋ አላቸው፡፡ ይህ የመመርመሪያ መሳሪያ ለነፍሰጡር ሴትና ለአጥቢ እናቶች አይመከርም፡፡ አንዲት የምታጠባ እናት አስገዳጅ ሁኔታዎች ተፈጥረው የሲቲስካን ምርመራ ካደረገች ልጇን ቢያንስ ለሃያ አራት ሰዓታት ከማጥባት መቆጠብ ይኖርባታል፡፡
ፔቲስካን (Positron Emission Tomography)
የሰውነታችንን ውስጠኛ አካል አሠራር በምስል በማሳየት ከጤናማው አሠራር ለየት ያሉ ነገሮች መፈጠር አለመፈጠራቸውን በግልጽ ለመለየት ያስችላል፡፡
ይህ መሣሪያ  ውስጣዊ አካላችን በጉዳት ከጥቅም ውጪ ከመሆኑ በፊት ያለበትን ችግር በቅድሚያ አውቆ ለመመርመርና ወደትክክለኛ ተግባሩ ለመመለስ ይጠቅማል፡፡
በፔቲ ስካን መሳሪያ ወደሰውነታችን ውስጥ የሚገባው ጨረር ከሌሎቹ ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን በፅንስ ላይ አደጋን ሊያስከትል ስለሚችል ነፍሰጡሮች ምርመራውን ከማድረግ መቆጠብ አሊያም ለሃኪማቸው ስለእርግዝናቸው በቅድሚያ መናገር ይጠበቅባቸዋል፡፡

ኤምአርአይ (Magnetic Resonance Imaging)   
ከሬዲዮ ሞገድ ጋር ከፍተኛ አቅም ያለው ማግኔቲክ ኃይልን በመጠቀም የውስጥ አካላትን እየከፋፈለ ፎቶ (ምስል) በማውጣት ለመመርመር የሚያስችል ቴክኖሎጂ ነው፡፡ በዚህ ዘመናዊ መመርመሪያ መሣሪያ በመጠቀም ሃኪሙ የታማሚውን ችግር በቀላሉ ለመለየት ይችላል፡፡ ለጭንቅላት (አንጐል) እና የአጥንት መገጣጠሚያዎችን ለመመርመር ተመራጭ መሣሪያ ነው፡፡
በዚህ መሣሪያ ምርመራ በሚደረግበት ክፍል ውስጥ ማንኛውም ብረት ነክ ነገር እንዲኖር አይፈቀድም፡፡ ሰዓት፣ ጌጣጌጦች፣ የፀጉር ጌጦች፣ የብረት ዚፕ፣ ብረት ነክ መነፅሮች መያዝና ማድረግ አይቻልም፡፡ ታካሚው በማሽኑ ውስጥ በሚቆይባቸው ጊዜያት ንቅናቄ ማድረግም አይፈቀድለትም፡፡
መሣሪያው እጅግ ዘመናዊና አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ ጨረሮች የሌሉት በመሆኑ በተለይ ለአንጐል ምርመራ እጅግ ጠቃሚ መሣሪያ ነው። መሣሪያው የሚያወጣው ምስል ጥራት የጤና አክሉን በቀላሉ ለመለየት የሚያስችል ነው፡፡ ለሌሎች መሣሪያዎች የተሰወሩ ችግሮች ከኤም አር አይ ሊያመልጡ አይችሉም፡፡
ምስሉ ጥራት እንዲኖረው ለማድረግ ታስቦ የሚጨመረው ኬሚካል አንዳንድ ጊዜ አለርጂን የመፍጠር አጋጣሚዎች ይኖሩታል፡፡ ከዚያ በቀር ይሄ ነው ተብሎ የሚጠቀስ የጐንዮሽ ጉዳት የለውም፡፡
መሣሪያው ብረት ነክ ነገሮችን ስለማይቀበል በሰውነታቸው ውስጥ ለተለያዩ አካላት ድጋፍ እንዲሆኑ ብረት የተገጠመላቸው ሰዎች ምርመራውን ከማድረጋቸው በፊት ስለጉዳዩ ለሃኪማቸው እንዲነግሩ ይመከራሉ፡፡
እነዚህ ዘመናዊ የህክምና መመርመሪያ መሣሪያዎች ለሃኪሙም ሆነ ለታካሚው የሚሰጡት ጠቀሜታ ከፍ ያለ ቢሆንም በመሣሪያዎቹ በተደጋጋሚ መመርመርና ያለ ባለሙያ ዕውቅናና ፈቃድ ምርመራ ማድረግ ለከፋ የጤና ችግር ሊያጋልጥ እንደሚችል የህክምና ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ፡፡   

Read 6633 times